ሶማሊያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከባሕር ላይ ነዳጅ ለማውጣት ቁፋሮ ልትጀምር ነው
የፎቶው ባለመብት, Anatolia
ሶማሊያ ከቱርክ መንግሥት የነዳጅ ቆፋሮ ኩባንያ ጋር በመሆን የመጀመሪያዋን በባሕር ላይ የነዳጅ ቁፋሮ ልትጀምር መሆኑን አስታወቀች።
ሶማሊያ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ባለፈው ዓመት የተደረገው የነዳጅ ፍለጋ ውጤታማ መሆኑን ተከትሎ ነው።
የቱርክ ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን ነዳጅ ቆፋሪ መርከብ የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ ተልዕኮ ለመጀመር በአረቢያን ባሕር ላይ ወደ ሚገኘው የሶማሊያ ግዛት አምርቷል።
በቅርቡ በተደረገው የነዳጅ አሰሳ የተለዩ የውሃው አካባቢዎች ላይ ጥልቅ ቁፋሮው እንደሚጀመር ተገልጿል።
ሶማሊያ እና ቱርክ ባለፈው ዓመት የምርት መጋራት ስምምነት ተፈራርመዋል።
የሞቃዲሾ ባለሥልጣናት ቁፋሮው የሚሳካ ከሆነ ሰፊውን የተከማቸ እምቅ ሃብት የሚከፍት እና የሶማሊያ ምጣኔ ሃብት እንዲያንሰራራ ያደርጋል ብለዋል።
ተመራማሪዎች ሶማሊያ በቢሊዮኖች በርሜል የሚቆጠር የነዳጅ ክምችት እንዳላት ይገምታሉ።
ቱርክ በሶማሊያ የባሕር ክልል ውስጥ ነዳጅ ለማውጣት ቁፋሮ እንደምትጀምር የተናገረችው ከወራት በፊት ታኅሣሥ ወር ላይ ነበር።
ረሲፕ ታይብ ኤርዶዋን ይህንን የተናገሩት እስራኤል ለሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅና መስጠቷን ተከትሎ ድጋፍ ለማሰባሰብ ወደ ቱርክ አምርተው ከነበሩት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሼክ ሐሰን ሞሐሙድ ጋር ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው።
ከአንድ ዓመት በፊት በሶማሊያ እና በቱርክ መካከል የተደረሰውን ዘርፈ ብዙ የትብብር ስምምነት ተከትሎ ቱርክ ግዙፍ ነዳጅ አሳሽ መርከቦችን በሶማሊያ የባሕር ክልል ውስጥ አሰማርታ ፍለጋ ስታካሂድ ቆይታለች።
የቱርክ ፕሬዝዳንት ባለፈው ዓመት ለዘጠኝ ወራት የተካሄደው የነዳጅ አሰሳ ተጠናቅቆ በዚህ ዓመት ነዳጅ ለማውጣት ቁፋሮ ይጀመራል ሲሉ ተናግረው ነበር።
በሕንድ ውቅያኖስ ላይ በሚገኘው የሶማሊያ የባሕር ጠረፍ ላይ ሰፊ ቦታን የቱርክ ነዳጅ ፈላጊ አሳሾች ፍለጋ ማካሄዳቸውን የጠቀሱት ኤርዶዋን "ይህ ዓይነቱ ሥራ ለቱርክ አዲስ ነው" ሲሉ በወቅቱ ተናግረዋል።
ቱርክ በ2024 መጀመሪያ ላይ ከሶማሊያ ጋር የመከላከያ እና የምጣኔ ሀብት ስምምነት የተፈራረመች ሲሆን፣ ይህም የነዳጅ እና የተፈጥሮ ሀብት ፍለጋን ያካተተ ነበር።
በነዳጅ ፍለጋው ስምምነቱ መሠረት ቱርክ የነዳጅ ፍለጋን፣ ምዘናን፣ ነዳጅ ዘይትን ከባሕር ዳርቻ ስፍራዎች የማልማት እና የማምረት ሥራዎችን እንደምታከናውን ተገልጿል።
እንዳያመልጥዎ
ከየፈርጁ
በስፋት የተነበቡ
የሚፈልጉት ይዘት የለም