በሊባኖስ የእስራኤል ወታደር የኢየሱስ ክርስቶስን ሐውልት ሲያፈርስ መታየቱ ቁጣን ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ጦር ክስተቱን "አክብዶ" እንደሚያይ ተናግሯል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በደቡባዊ ሊባኖስ አንድ የእስራኤል ወታደር በመዶሻ የኢየሱስ ክርስቶስን ሐውልት ሲያወድም የሚያሳያ ምሥል በማኅበራዊ ትስስር ገፆች ከተሰራጨ በኋላ ሰፊ ውግዘት አስከተለ።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በተፈጠረው ሁኔታ "ድንጋጤ እና ሐዘን" እንደተሰማቸው ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳር በበኩላቸው "ስሜቱ ለተጎዳው ለሁሉም ክርስቲያን ስለክስተቱ ይቅርታ እንጠይቃለን" ብለዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ሐውልቱ ደብል በተባለ አካባቢ ወጣ ብሎ በአንድ ቤት በር ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎ የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል። አካባቢው በእስራኤል እና ሄዝቦላህ ጦርነት ምክንያት ነዋሪዎቹ ቀያቸውን ጥለው ካልሸሹባቸው ጥቂት መንደሮች ውስጥ አንዱ ነው።

የደብል አካባቢ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ኃላፊ አባ ፋዲ ፍላፍለ ለቢቢሲ "መስቀላችን፣ ቅድስት ምልክታችን እና የኃይማኖቱ ምልክት መዋረዱን ሙሉ ለሙሉ እንቃወማለን" ብለዋል።

"ከሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ጋር የሚቃረን እና ጨዋነትን የማያንፀባርቅ ነው።"

ተመሳሳይ ውድመቶች ከዚህ በፊትም ደርሰው እንደሚያውቁም ገልፀዋል።

የእስራኤል ጦር በማኅበራዊ ትስስር ገፆች የተሰራጨው ምሥል ትክክል መሆኑን ያረጋገጠ ሲሆን፤ ክስተቱን "አክብዶ" እንደሚያይ እና "የወታደሩ እርምጃ ከሚጠበቅባቸው እሴቶች ጋር የማይገናኝ ነው" ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በጥቃቱ ላይ የተሳተፉ ሁሉ አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ያሳወቀው የእስራኤል መከላከያ ኃይል (አይዲኤፍ)፤ ሐውልቱን ወደነበረበት ቦታ ለመመለስ" ከክርስቲያን ማኅበረሰቦች ጋር እየሰራ መሆኑን አክሎ ተናግሯል።

ባለፈው አርብ በአሜሪካ አሸማጋይነት በእስራኤል እና ሊባኖስ የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት ተከትሎም በሺህዎች የሚቆጠሩ የእስራኤል ወታደሮች ደቡባዊ ሊባኖስን መውረራቸውን ቀጥለዋል።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ በእስራኤል ጦር እና በሺአ ሙስሊም ታጣቂው ሄዝቦላህ መካከል ለስድስት ሳምንታት ሲደረግ የነበረውን ጦርነት የገታ ቢሆንም ሁለቱም ወገኖች ስምምነቱን በመጣስ ተካስሰዋል።

ሐውልቱ ላይ የተፈፀመው የጥቃት ዜና በእስራኤል የአሜሪካ አምባሳደር እና የመጥምቃውያን አጥቢያ መጋቢ የሆኑት መጋቢ በኤክስ ገፃቸው "ፈጣን፣ ጠንካራ እና ይፋዊ እርምጃ አስፈላጊ ነው" ብለዋል።

ቀኝ ዘመም የአሜሪካ የፖለቲካ ተንታኞችም ጥቃቱን "አስደንጋጭ" በማለት አገራቸው ለእስራኤል የምታደርገውን ድጋፍ በማንሳት ተቃውመውታል።

በቅርብ የተሰበሰቡ የሕዝብ ድምፆች በአሜሪካ ለእስራኤል የነበረው ድጋፍ ማሽቆልቆሉን ያሳያሉ።

ባለፈው ወር የእስራኤል ፖሊስ በአገሪቱ የሚገኙት የሮማ ካቶሊክ መሪ ለሆሳእና በዓል በጥንታዊቷ እየሩሳሌም የሚገኝ ቤተ ክርስቲያን እንዳይገቡ መከልከሉ ሕዝባዊ ቁጣ ቀስቅሷል። ፖሊስ በኢራን ጦርነት የተደቀነው የደኅንነት ስጋት ለክልከላው ምክንያት መሆኑን ተናግሯል።

ሮሊንግ ሴንተር የተባለ መቀመጫውን በእየሩሳሌም ያደረገ እና የኃይማኖቶች መቀራረብ ላይ የሚሰራ ድርጅት በ2025 ባወጣው ሪፖርት "ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ክርስቲያኖች ላይ ያለው ጥላቻ እየጨመረ ነው" ብሏል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ሐውልት ጥቃትን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ "ከመካከለኛው ምሥራቅ በተለየ በእስራኤል የሚገኘው ሕዝበ ክርስቲያን እያበበ ነው" ብለዋል።