የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር የአገሪቱ ከፍተኛ የጦር አዛዥ ከሥልጣን እንዲለቅቁ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ጦር አዛዥ ራንዲ ጆርጅ
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት አገራቸው በኢራን ጦርነት እያደረገች ባለችበት ወቅት የጦር አዛዡን ራንዲ ጆርጅን ከሥልጣናቸው እንዲለቁ መጠየቃቸውን የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ዘገበ።

የፔንታጎን ዋና ቃል አቀባይ ሺን ፓርኔል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሰጡት መግለጫ ጆርጅ "ከጦር ኃይሉ 41ኛ ዋና አዛዥነታቸው ከአሁን ጀምሮ ከሥልጣናቸው በጡረታ ይሰናበታሉ" ብለዋል።

የጦር አዛዡ በተለምዶ ለአራት ዓመታት ያህል ያገለግላል። ከዌስት ፖይንት ወታደራዊ አካዳሚ በወታደራዊ መኮንንነት የተመረቁት እና ለረዥም ጊዜ በጦሩ ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች ውስጥ ያገለገሉት ጆርጅ እአአ በ2023 በቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ነበር ወደዚህ ኃላፊነት የመጡት።

በጦሩ ውስጥ ይህ ዜና የተሰማው ትራምፕ በቅርቡ ባደረጉት ንግግር አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር የሚያደርጉት ጦርነት "በቅርቡ" እንደሚጠናቀቅ ከተናገሩ በኋላ ነው ።

ጆርጅ በመጀመሪያው የባህረ ሰላጤ ጦርነት እና በቅርብ ጊዜ በኢራቅ እና አፍጋኒስታን በተካሄዱ ውጊያዎች የእግረኛ ጦር መኮንን በመሆን አገልግለዋል።

ጄነራሉ ለምን ከሥልጣናቸው እንዲለቅቁ እንደተጠየቁ ግልጽ የሆነ ነገር የለም።

ስማቸው ያልተገለጸ አንድ ከፍተኛ የመከላከያ ባለሥልጣን "ለነበራቸው አገልግሎት አመስጋኞች ነን፤ ነገር ግን በሠራዊቱ ውስጥ የአመራር ለውጥ የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ነን" ሲሉ ለሲቢኤስ ተናግረዋል።

የፔንታጎን ቃል አቀባይ ፓርኔል "የጦር ሚኒስቴሩ ጄኔራል ጆርጅ ለአስርት ዓመታት ለአገራቸው ላበረከቱት አገልግሎት አመስጋኝ ነው። በጡረታቸው ወቅት መልካም ዕድል እንመኝላቸዋለን" ብለዋል።

የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን የጦር ኃይሉ ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ጄኔራል ክሪስቶፈር ላኔቭ ተጠባባቂ የጦሩ አዛዥ በመሆን እንደሚተኳቸው ዘገበዋል።

ፓርኔል እንዳሉት ላኔቭ "ለአስርት ዓመታት የሥራ ልምድ ያላቸው እና በጦርነት የተፈተኑ መሪ ሲሆኑ በሚኒስትር ሄግሴት የዚህን አስተዳደር ራዕይ ያለ እንከን እንደሚፈጽሙ ሙሉ በሙሉ ይታመናሉ" ብለዋል።

በዌስት ፖይንት የሚገኘው የአሜሪካ ወታደራዊ አካዳሚ ረቡዕ ዕለት ጆርጅ ከወታደሮች ጋር ሲገናኙ የሚያሳይ ፎቶግራፍ ይፋ አድርጓል።

ከምስሉ ጋር "ለመሪነት ለሚዘጋጁ ካዴቶች በልምድ ላይ የተመሠረተ መመሪያ ሰጥተዋል" ብሏል።

ሄግሴት ወደ ፔንታጎን ከመጡ ጊዜ አንስቶ የባሕር ኃይል ኦፕሬሽን ዋና አዛዥ እና የአየር ኃይል ምክትል ዋና አዛዥን ጨምሮ ከአስራ ሁለት በላይ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን አሰናብተዋል።