ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በፈረንሳይ ባለቤትነት የተያዘ የእቃ ጫኝ መርከብ በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በኩል ማለፉ ተሰማ
አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር ጦርነት ከከፈቱ ከአንድ ወር በኋላ ባለቤትነቷ የፈረንሳይ የሆነች መርከብ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል አለፈች።
የማልታን ሰንደቅ ዓላማ የምታውለበለብ እና ባለቤትነቷ የፈረንሳዩ ሲኤምኤ ሲጂኤም ድርጅት የሆነች ዕቃ ጫኝ መርከብ የሆርሙዝ ወሽመጥን ማቋረጧን የማጓጓዣ ድርጅት የሚያስተዳድረው ቢኤፍኤም ቲቭ የተባለ ሚዲያ አርብ ዕለት አረጋግጧል።
የመርከቧ ባለቤት የሆነው ድርጅት ግን በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።
ጦርነቱ ከጀመረ ወዲህ በምዕራብ አውሮፓ ኩባንያ የምትተዳደር መርከብ ወሽመጡን አቋርጣ በማለፍ የመጀመሪያዋ እንደሆነች የመርከቦችን እንቅስቃሴ የሚተነትነው ክፕለር አረጋግጧል።
ምንም እንኳን ኢራን " የጠላት ያልሆኑ መርከቦች" የውሃ መስመሩን መጠቀም እንደሚችሉ ብታስታውቅም በበርካታ መርከቦች ላይ ጥቃት መድረሱ እና እየተካሄደ ያለው ጦርነት በወሽመጡ በኩል ያለውን መደበኛ እንቅስቃሴ አስቁሞታል።
የክትትል መረጃ እንደሚያሳየው ባለቤትነቷ የፈረንሳይ የሆነችው ዕቃ ጫኝ መርከብ ወሽመጡን ያለፈችው ወደ ኢራን ከሚወስደው የውሃ መስመር በተቃራኒ በኩል ባለው እና በኦማን ባሕር ዳርቻ አጠገብ ነው። መርከቧ የጫነችው ምን እንደሆነ አልታወቀም።
የተፈጥሮ ጋዝ የጫነች የጃፓን መርከብም በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ማለፏን የአገሪቷ ግዙፍ የመርከብ ኩባንያ ኤምኦኤል አረጋግጧል።
" የመርከቧ እንዲሁም የሁሉም የመርከበኞች ቡድን አባላት ደኅንነት ተረጋግጧል" ብሏል ድርጅቱ ። የሠራተኞቻችንን፣ የጭነት እና የመርከብ ደኅንነት ላይ ቅድሚያ ሰጥተን መስራታችንን እንቀጥላለን " ሲልም አክሏል።
እንደ የባሕር ኃይል መረጃዎች እና የደኅንነት አገልግሎት ሊሎይድ ሊስት ከሆነ ሐሙስ እለት በሆርሙዝ ወሽመጥ ያለፉ በርካታ መርከቦች ባልተለመደ መልኩ በኦማን ባሕር ዳርቻ ተጠግተው ነበር ያለፉት።
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ የሆርሙዝ ወሽመጥን ልትከፍት እንደምትችል ቢናገሩን አጋሮቻቸው ይህንን ለማድረግ ድጋፍ ባለመስጠታቸው ብስጭታቸውን ገልጸዋል።
" ከትንሽ ጊዜ በኋላ የሆርሙዝ ወሽመጥን በቀላሉ እንከፍታለን ፤ ነዳጁን እንወስዳለን፤ ከዚያ ሃብት እንፈጥራለን፤ ይህ ለዓለም ትልቅ ደስታ ይሆናል" ሲሉ ትራምፕ በትሩዝ የማኅበራዊ ሚዲያ ገፃቸው አጋርተዋል።
አንድ አምስተኛ የሚሆነው የዓለም ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ከባሕረ ሰላጤው አገራት የሚጓጓዘው በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ነው።
ሆኖም ይህ ወሳኝ መስመር የካቲት ወር መጨረሻ ላይ ጦርነቱ ከጀመረ በኋላ የታገደ ሲሆን ወደ 200 የሚሆኑ መርከቦች እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ ውሃ ላይ መቅረታቸውን የደኅንነት ድርጅቱ - ሊሎይድ ሊስት መረጃ ያሳያል።
በወሽመጡ በኩል የሚደረገው እንቅስቃሴ በመስተጓጎሉም የዓለም የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት ይከሰታል የሚል ስጋትንም ፈጥሯል።
ከግጭቱ በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲነፃፀርም በወሽመጡ በኩል የሚደረገው ጉዞ ሙሉ በሙሉ ባይቆምም የትራፊክ እንቅስቃሴ ወደ 95 በመቶ ያህል ቀንሷል።
ቢቢሲ ቬሪፋይ መጋቢት ወር ላይ በሰራው ትንታኔ ወደ 100 የሚጠጉ መርከቦች ማለትም በቀን ከአምስት እስከ ስድስት መርከቦች በሆስርሙዝ ወሽመጥ በኩል ማለፍ ችለዋል።
ከእነዚህ መርከቦች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ከኢራን ጋር ግንኙነት ያላቸው መሆናቸውን ቢቢሲ ቬሪፋይ ያረጋገጠ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ እንደ ፓኪስታን እና ሕንድ ካሉ አገራት ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው።