የኢራንን ዩራኒየም ለመቆጣጠር የአሜሪካ ልዩ ኃይልን ማሰማራት የሚጠይቀው አደገኛው ተልዕኮ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

የአሜሪካ ወታደሮች ከመሬት በታች የተከማቸውን የኢራንን የበለፀገ ዩራኒየም ለመቆጣጠር የሚያስችል ዘመቻ የማካሄዳቸው ነገር የማይሆን ነገር ቢመስልም አንደኛው አማራጭ ነው።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጦርነቱ ውስጥ ዋና ዓላማቸው የሆነውን የቴህራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ማበልጸግን ለመግታት አንደኛው አማራጭ ነው።

እንዲህ ዓይነቱ ዘመቻ እጅግ ፈታኝ እና በአደጋ የተሞላ ሊሆን እንደሚችል ለቢቢሲ ሃሳባቸውን የገለጹ ወታደራዊ ባለሙያዎች እና የቀድሞ የአሜሪካ የመከላከያ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

እግረኛ ወታደሮችን ማሰማራት እንደሚያስፈልግ እና ንጥረ ነገሩን አንቀሳቅሶ ለማጠናቀቅም በርካታ ቀናትን ወይም ሳምንታትን ሊወስድ እንደሚችል ተናግረዋል።

የዩራኒየም ክምችትን ማስወገድ "በታሪክ ውስጥ እጅግ ውስብስብ ከሆኑ ተግባራት አንዱ ነው" ሲሉ በአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምሥራቅ ምክትል ሚኒስትር የነበሩት ማይክ ሙልሮይ ገልጸዋል።

ይህ እርምጃም ትራምፕ በኢራን ውስጥ ሊወስዷቸው ከሚችሏቸው በርካታ ወታደራዊ አማራጮች መካከል አንዱ ነው።

ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ሙሉ በሙሉ እንድትከፍት ጫና ለማድረግ አሜሪካ የኻርግ ደሴትን ልትቆጣጠር መቻሏ ሌላኛው አማራጭ ነው። ኢራንን ወደ ክብ ጠረጴዛ ለማምጣት አዳዲስ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን በመጠቀምም ሊያስገድዱ ይችላሉ።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት ከቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ ጋር በስልክ ባደረጉት ቃለ ምልልስ የኢራንን የበለፀገ ዩራኒየም ሳያስወግዱ ወይም ሳያጠፉ በጦርነቱ ማሸነፋቸውን ማወጅ ይቻል እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ከለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ባለፈው ሰኔ ወር በአሜሪካ እና በእስራኤል ጥቃቶች ምክንያት የተከሰተውን ጉዳት በመጠቆም ክምችቱ ያለውን ስጋት ለመቀነስም ሞክረዋል። "ይህ በጣም በጥልቀት የተቀበረ በመሆኑ ለማንም በጣም ከባድ ይሆናል። በጣም ጥልቅ ነው። ስለዚህ… ደኅንነቱ በጣም የተጠበቀ ነው" ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል።

ዎል ስትሪት ጆርናል አሜሪካ ዩራኒየሙን ለማውጣት ዘመቻ እያሰበች መሆኑን ከዘገበ በኋላ ነው ፕሬዝዳንቱ አስተያየታቸውን የሰጡት። ዋይት ሐውስ በበኩሉ ትራምፕ በጉዳዩ ዙሪያ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ እንዳልደረሱ አስታውቋል።

የኢራንን ክምችት ዒላማ ማድረግ በርካታ የሎጂስቲክስ ተግዳሮቶች ይኖሩታል ሲሉ ባለሙያዎች ተናግረዋል።

እንደ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ገለጻ ኢራን ወደ 60 በመቶ የበለጸገ 440 ኪሎ ግራም ዩራኒየም ነበራት። ዩራኒየሙ ለጦር መሳሪያ ወደ ሚያስፈልገው 90 በመቶ በፍጥነት ሊበለጽግ ይችላል።

ኢራን ወደ 20 በመቶ የበለጸገ አንድ ሺህ ኪሎ ግራም የሚጠጋ ዩራኒየም እና ለሕክምና ምርምር ተቀባይነት ያለው እና 3.6 በመቶ ገደማ የበለፀገ 8,500 ኪሎ ግራም ዩራኒየ አላት።

በቀላሉ ለቦምብ ወይም ለሚሳዔል ቁሳቁስነት ሊውል የሚችል በጣም የበለጸገ ዩራኒየም በአብዛኛው በኢስፋሃን እንደተከማቸ ይታመናል።

ተቋሙ ባለፈው ዓመት በአሜሪካ እና በእስራኤል የአየር ድብደባ ዒላማ ከተደረጉት ሦስት ከመሬት በታች የሚገኙ የኒውክሌር ጣቢያዎች አንደኛው ነው።

በከፍተኛ ደረጃ የበለጸገው ዩራኒየም በሌሎች ቦታዎች ምን ያህል እንደተከማቸ ግን ግልጽ አይደለም።

አሜሪካ ክምችቱ የት እንዳለ በትክክል ብታውቅ ዩራኒየሙን ለማውጣት የሚደረገው ወታደራዊ ዘመቻ ቀላል ይሆን ነበር ሲሉ በኦባማ እና በትራምፕ አስተዳደር ውስጥ ከፍተኛ የመከላከያ ባለሥልጣን የነበሩት ጄሰን ካምቤል ተናግረዋል።

"በጣም ጥሩው ነገር የት እንዳለ በትክክል ማወቅ ነው። ወደ አራት የተለያዩ ቦታዎች ከተበተነ ግን ጉዳዩ ሙሉ ለሙሉ የተለየ ይሆናል" ሲሉ ካምቤል የውስብስብነት ደረጃውን ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በቅርቡ ጥቃት የደረሰበት የዩራኒየም ማከማቻ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከኢስፋሃን በተጨማሪ በከፍተኛ ደረጃ የበለፀገ ዩራኒየም በፎርዶ እና ናታንዝ ሊከማች ይችላል። ሁለቱም ቦታዎች ባለፈው ዓመት ዒላማ ተደርገው ነበር።

የዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኤነርጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ ባለፈው ወር እንደተናገሩት አብዛኛው የኢራን ከፍተኛ የበለፀገ ዩራኒየም በኢስፋሃን ውስጥ ተከማችቷል። በናታንዝም ተጨማሪ ክምችቶች አሉ።

በ2025 ሰኔ ወር ላይ የአሜሪካ እና የእስራኤል የአየር ጥቃት ዘመቻ ከተደረገ በኋላ ተቆጣጣሪዎቻቸው ከኢራን ስለተባረሩ ቦታዎቹን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ አለመገኘቱን ጠቅሰዋል።

"መመለስ ስንችል ብቻ የምናብራራቸው ብዙ ጥያቄዎች አሉ" ሲሉ ግሮስሲ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

አሜሪካ የት እንዳለ ታውቃለች ተብሎ ተገምቶም ቢሆን፤ በከፍተኛ ደረጃ የበለፀገው ዩራኒየም ሌላ ተግዳሮቶች አሉ።

ኢራን በአሜሪካ እና በእስራኤል ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት ከኒውክሌር ተቋሞቿ በአንዱ አቅራቢያ የነበረውን የመሬት ውስጥ ማከማቻ መከላከያን አጠናክራለች።

ለምሳሌ ያህል በየካቲት ወር የሳተላይት ምሥሎች እንዳሳዩት ከሆነ በኢስፋሃን ወደ ዋሻው የሚገቡ ሁሉም መግቢያዎች በአፈር የተዘጉ ይመስላሉ። ይህ ደግሞ ማንኛውንም ዘመቻ የበለጠ አስቸጋሪ ያደርገዋል።

አሜሪካ እና እስራኤል ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የኢራንን የባሕር ኃይል ለማውደም፣ የባለስቲክ ሚሳዔሎቿን ለማዳከም እና የኢንዱስትሪ መሠረቷን ለማኮላሸት የአየር ጥቃቶችን ብቻ መጠቀም ችለዋል።

ከሌሎች ወታደራዊ ዓላማዎች በተለየ ሁኔታ የኢራንን የበለፀገ ዩራኒየም ለማግኘት እግረኛ ጦር ሳይጠቀሙ ማከናወን እንደማይችል ባለሙያዎች ተናግረዋል።

አሜሪካ ኢስፋሃንን፣ ናታንዝን እና በዙሪያው ያሉትን አካባቢዎች ለመጠበቅ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የተሰማሩትን የ82ኛው የአየር ወለድ ብርጌድ መጠቀም ትችላለች።

ከዚያም የኒውክሌር ቁሳቁሶችን ለማንቀሳቀስ የሰለጠኑ ልዩ የዘመቻ ኃይሎች የበለፀገውን ዩራኒየም ለማምጣት ይገባሉ። ዩራኒየሙ በጋዝ መልክ የሚገኝ ሲሆን፣ በትላልቅ የብረት ኮንቴይነሮች ውስጥ እንደሚከማች ይታመናል።

የሳተላይት ምሥሎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ወደ ኢስፋሃን እና ናታንዝ የሚያስገቡ መግቢያዎች በአሜሪካ የአየር ድብደባ ክፉኛ ተጎድተዋል።

የአሜሪካ ኃይሎች የበለፀገውን ዩራኒየም ለማግኘት በአየር ኃይል የወደመውን ፍርስራሽ ለመቆፈር ከባድ ማሽኖች ያስፈልጋቸው ይሆናል፥ ይህም ደግሞ ለኢራን የመልሶ ማጥቃት የሚያጋልጣቸው ነው።

"በመጀመሪያ ቦታውን መቆፈር እና [የበለፀገውን ዩራኒየም] መኖሩን መለየት ያስፈልጋል። እንዲህ ደግሞ ያለማቋረጥ ስጋት ውስጥ የሚያስገባ ይችላል" ብለዋል ካምቤል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የናንትዝ የኒውክሌር ጣቢያ

ኢራን እንዴት ምላሽ ልትሰጥ ትችላለች? ወይም የአገሪቱን ዋና ዋና የኒውክሌር ተቋማትን ዒላማ ለሚያደርጉ የአሜሪካ ወታደሮች ምን ያህል ስጋት ልትሆን ትችላለች? የሚለው ትልቅ ጥያቄ ነው።

አሜሪካ እና እስራኤል "አስፈላጊ ከሆነ ይህንን ዓይነት ዘመቻ ለማከናወን እንዲረዳቸው የኢራን የመከላከያ አቅምን እያዳከሙ ነው" ሲሉ የቀድሞ የአሜሪካ የመከላከያ ባለሥልጣን እና በስኮውክሮፍት የመካከለኛው ምሥራቅ የደኅንነት አማካሪው አሌክስ ፕሊትሳስ ተናግረዋል። ይህም ሆኖ ግን አሁንም "ከፍተኛ አደጋ" የሚያስከትል ዘመቻ እንደሚሆን አስታውቀዋል።

የአሜሪካ እግረኛ ወታደሮች ከኢራን ሦስተኛዋ ትልቅ ከተማ በግምት 482 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በምትገኘው ኢስፋሃን ተገልለው ይቆያሉ።

"ርቀቱን ከግምት በማስገባት የሕክምና ድጋፍን አስቸጋሪ ያደርገዋል። የአሜሪካ ወታደሮች ለፀረ-አውሮፕላን ተኩሶች እንዲሁም በኒውክሌር ጣቢያው ውስጥ እያሉ ለሚሰነዘሩ ጥቃቶች ተጋላጭ ይሆናሉ" ሲሉ ፕሊትሳስ ተናግረዋል።

ምንም እንኳን ዘመቻው የተለያዩ አካሄዶች ቢኖሩትም፤ የአሜሪካ ወታደሮች ሊንቀሳቀሱ የሚችሉበትን የአየር ማረፊያ ወይም ዞን መያዝን ሊያካትት እንደሚችል ባለሙያዎች ተናግረዋል። ከኢራን የበለፀገውን ዩራኒየም ለማስወገድ የሚጠቀሙበት የአየር ማረፊያም ሆኖ ያገለግላል።

የአየር ማረፊያዎችን እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ለመጠበቅ የሰለጠነው 82ኛው የአየር ወለድ ክፍል ከሌሎች የአሜሪካ ኃይሎች ጋር ለተልዕኮው መሳካት ሊሠማራ ይችላል ሲሉ ወታደራዊ ባለሙያዎች ተናግረዋል።

ዩራኒየም ከተገኘ በኋላ ደግሞ አሜሪካ ከኢራን ማስወጣት ወይም ባለበት ቦታ የማስወገድ ጥያቄ ይጠብቃታል።

በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ አሜሪካ የኢራንን የበለፀገ ዩራኒየም ከአገሪቱ ከማስወጣት ይልቅ በቦታው ላይ ማስወገድን ልታስብበት እንደምትችል ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ነገር ይህ ግን ትልቅ፣ ውስብስብ እና ጊዜ የሚወስድ ተግባር ይሆናል ሲሉ በአይሁድ የብሔራዊ ደኅንነት ተቋም የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ባለሙያ የሆኑት ጆናታን ሩሄ ተናግረዋል።

ዩራኒየሙን ከኢራን ማስወጣት ፈጣን አማራጭ ሲሆን፣ አሜሪካም በቀላሉ ከጥቅም ውጪ እንድታደርገው ያስችላታል ሲሉ ሩሄ ተናግረዋል። ዘመቻው ምንም ይሁን ምን በጣም አደገኛ ይሆናል ሲሉም አክለዋል።

"ግማሽ ቶን የሚሆን ለጦር መሳሪያ ማዘጋጃነት የደረሰ የዩራኒየም ንጥረ ነገርን ማውጣት ሊኖርባቸው ይችላል" ሲሉ ሩሄ ተናግረዋል።

"በዚህ ወቅት ግን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስህተቶች ሊፈጸሙ ይችላሉ" በማለት ስጋታቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።