በሱዳን ሆስፒታል ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት 64 ሰዎች መገደላቸውን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, WHO
በሱዳን ኤል-ዳይን የማስተማሪያ ሆስፒታል ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት 13 ህጻናት፣ ሁለት ነርሶች እና አንድ ዶክተርን ጨምሮ 64 ሰዎች ሲገደሉ 89 ሰዎች መቁሰላቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ገለጹ።
የሱዳን ጦር አርብ፤ በአገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል ውስጥ በምትገኘው እና በተቀናቃኙ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) በተያዘችው ከተማ ውስጥ ትልቅ ሆስፒታል ላይ ጥቃት ፈጽሟል መባሉ አስተባብሏል።
ዶ/ር ቴድሮስ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ "በቂ ደም ፈስሷል" ያሉ ሲሆን ሁሉም ወገኖች ከሦስት ዓመት ገደማ በፊት የተጀመረውን ግጭት እንዲያቆሙ አሳስበዋል።
አርኤስኤፍ እንደሚገልጸው፤ በምስራቅ ዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ ኤል-ዳይን በሚገኘው ሆስፒታል በድሮን የተመታው ሙስሊሞች የኢድ በዓልን ባከበሩበት ዕለት ነው።
ሱዳን በአውሮፓውያኑ ሚያዝያ 2023 ወደ የእርስ በርስ ጦርነት የገባችው በወታደራዊ ኃይል እና አርኤስኤፍ መካከል በተፈጠረው የስልጣን የበላይነት የመያዝ ሽኩቻ ነው። ሁለቱም ቡድኖች በ2021 መፈንቅለ መንግሥት በጋራ ወደ ስልጣን መምጣታቸው ይታወሳል።
በግጭቱ ምክንያት ከ150 ሺህ በላይ ሰዎች ሞተዋል፤ ከ12 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ከቤታቸው ተፈናቅለዋል።
ኤል-ዳይን የማስተማሪያ ሆስፒታል አርብ ምሽቱ ጥቃት በኋላ ከአሁን ከሥራ ውጭ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ቴድሮስ፤ ተፋላሚ ኃይሎች የሕክምና ተቋማትን በተደጋጋሚ ዒላማ ማረድጋቸውን አውግዘዋል።
ዶ/ር ቴድሮስ፤ "አርብ ምሽት የተፈጸመውን ጥቃት ጨምሮ ለሦስት ዓመታት ያህል በቆየው ግጭት ውስጥ በጤና ተቋማት ላይ በደረሱ 213 ጥቃቶች 2,036 ሰዎች መሞታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት አረጋግጧል" ብለዋል።
"በሱዳን የተከሰተውን ግጭት በማርገብ የሲቪሎችን፣ የጤና ባለሙያዎችን እና የሰብአዊ መብቶችን ለመጠበቅ ጊዜው ደርሷል" ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
"የጤና ተቋማት በፍፁም ዒላማ መሆን የለባቸውም። ሰላም ምርጡ መድኃኒት ነው።"
አርኤስኤፍ ባወጣው መግለጫ ጥቃቱ የሆስፒታሉን የላይኛው ክፍል ሙሉ በሙሉ እንዳወደመ እና በድንገተኛ ክፍል ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰ ገልጿል። ወሳኝ የሕክምና መሳሪያዎችንም አውድሟል ብሏል።
የሱዳን ጦር በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፤ ከጥቃቱ ጀርባ አለ በሚል በቀረበበት ክስ እንደተገረመ ገልጿል። ጦሩ "ዓለም አቀፍ ደንቦችን እና ህጎችን" እንደሚያከብር አክሏል።
የአደጋ ጊዜ ጠበቆች ቡድን ገለልተኛ እና ግልጽ ምርመራ እንዲደረግ እና ተጠያቂዎቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ ጥሪ አቅርቧል።
በጦርነቱ ወቅት በጦሩ እና በአርኤስኤፍ የተፈጸሙ ወንጀሎችን የሚመዘግበው የአካባቢው የመብት ተሟጋች ድርጅት፣ በኤል-ዳይን የሚገኘው ሆስፒታል ለከተማው እና ለአካባቢው መንደሮች ለሚገኙ በሺህዎች ለሚቆጠሩ ሲቪሎች ወሳኝ የጤና ተቋም እንደነበር ገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ምስራቅ ዳርፉር የኮርዶፋንን ክልል የሚዋሰን ሲሆን በጦርነቱ ውስጥ አዲስ ግንባር ከመሆን ባለፈ በየቀኑ በሚባል ደረጃ የድሮን ጥቃቶች ይፈጸማሉ።
አካባቢው በአርኤስኤፍ ቁጥጥር ስር የሚገኘውን የምዕራብ ዳርፉር ክልልን በአገሪቱ ጦር ስር ከምትገኘው ከዋና ከተማዋ ካርቱም ጋር የሚያገናኝ ዋና መስመር ነው።
በአሜሪካ መሪነት የሰላም ጥረቶች ቢደረጉም ጦርነቱን ለማስቆም አልተቻለም።












