በደቡብ ጎንደር ዞን በተፈጸመ ጥቃት የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን ጨምሮ ሰባት ሠዎች መገደላቸውን እማኞች ተናገሩ
የፎቶው ባለመብት, Nefas Mewcha city communication affairs
በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ላይ ጋይንት ወረዳ ባለፈው አርብ ሚያዚያ 9/2018 ዓ.ም. ሳሊ በተባለች አነስተኛ ከተማ የመንግሥት ወታደሮች በፈፀሙት ጥቃት ሰባት ሠዎች መገደላቸውን እና ቤተ ክርስቲያን ላይ ጉዳት መድረሱን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ምንጮች ገለፁ።
ሟቾቹ ሁለት የቤተ ክርስቲያን ዲያቆናት፣ አንድ መርጌታ (የድጓ መምህር)፣ የእንስሳት ሐኪም እና ሦስት አርሶ አደሮች መሆናቸውን ተናግረዋል።
አገልጋዮቹ ቀድሰው ሲወጡ ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ሲገደሉ፤ ሦስቱ ሰዎች በቤታቸው እና አንድ ሰው ደግሞ መንገድ ላይ መገደሉን ቢቢሲ ያሰባሰባቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ጥቃቱ የተፈፀመው በአካባቢው "የምርጫ ካርድ ውሰዱ" በሚል ሕዝባዊ ጥሪ መቅረቡን ተከትሎ በአካባቢው በሚንቀሳቁ የፋኖ ኃይሎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ውጊያ ከተቀሰቀሰ በኋላ መሆኑን እማኞች ተናግረዋል።
ቢቢሲ ከላይ ጋይንት ወረዳ እና ከደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪዎች ምላሽ ለማግኘት ጉዳዩን ቢያስረዳም የሥራ ኃላፊዎቹ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመባት ሳሊ ከተማ ከወረዳው ዋና ከተማ ነፋስ መውጫ በ25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ አነስተኛ ከተማ ስትሆን በፋኖ ኃይሎች ቁጥጥር ስር እንደሆነች ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
"አርብ ዕለት ለምርጫ ስብሰባ ብለው መጡ። 'የምን ምርጫ ነው' ብሎ ፋኖ ሲንቀሳቀስ፤ ሲተኩስባቸው ከዚያ በኋላ ሲተኮስ ዋለ" ሲሉ በከተማዋ ከጥቃቱ በፊት የነበረውን ግጭት አንድ ነዋሪ ገልፀዋል።
'የደብረ ብርሃን ሳሊ ባለእግዚአብሔር' ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ከቅዳሴ በኋላ ለክርስትና የተዘጋጀ ፀበል ፃዲቅ እየቀመሱ እያለ ውጊያው መቀስቀሱን ለቢቢሲ አስረድተዋል። ቁጥራቸው በርከት ያሉ የመንግሥት ወታደሮች ወደ ቤተ ክርስቲያኒቷ መግባታቸውንም የዓይን እማኞች ተናግረዋል።
ወታደሮቹ ሁለት የቤተ ክርስቲያኗ ጥበቃዎችን ከደበደቡ በኋላ ወደ ቅጥር ግቢው ዘልቀው መግባታቸውን ከጥቃቱ ያመለጡ አገልጋዮች ለቢቢሲ ተናግረዋል። ከደጀ ሰላሙ እንዲወጡ ተደርገው በመጀመሪያ በመሣሪያ አፈሙዝ እና ሰደፍ እንደተደበደቡም አክለዋል።
ሰባት የሚሆኑ አገልጋዮች በደረታቸው እንዲተኙ እና እንዲንበረከኩ ከተደረጉ በኋላ፤ ተኩስ መከፈቱን ተናግረዋል።
"እነሱን ሲመታ ቀድመን ወደቅን" በማለት ከጥቃቱ የተረፉ አንድ አገልጋይ ሲናገሩ፤ ሌላኛው ደግሞ ከጥይቱ "በታቦቱ ኃይል" መትረፋቸውን ገልፀዋል።
ሦስቱ አገልጋዮች በተመቱ በኋላ፤ "አለቃው 'እንዴት ንፁሃን ትገድላለህ? እንዳትመታ' አለው። 'የተረፋችሁ ሩጡ' ተባልን" ሲሉ እንዴት በሕይወት እንደተረፉ ተናግረዋል።
እንደሚሞቱ እርግጠኛ እንደነበሩ ለቢቢሲ የተናገሩት እማኙ፤ እርሳቸው እና የቤተ ክርስቲያኗን አስተዳዳሪ ጨምሮ አራት አገልጋዮች "በደመ ነፍስ" ሮጠው እንዳመለጡ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።
ከሟቾቹ መካከል ዲያቆን የሆነው የ21 ዓመት ልጃቸው እንደሚገኝበት ለቢቢሲ የተናገሩ አንድ አባት፤ "'ወድቆልኃል፤ ድረስ' ተባልኩ። እየተፈጠፈጥኩ መጣሁ" ሲሉ የልጃቸውን ሞት የተረዱበትን ቅፅበት ተናግረዋል።
ቤተ ክርስቲያን ደርሰው የልጃቸውን እና የሌሎች አገልጋዮችን አስከሬን ሲመለከቱም "መፈጠር ያስጠላል" በማለት አገልጋዮቹ በተደጋጋሚ ጥይት እንደተደበደቡ ተናግረዋል።
"ሰማዩ ተደፋብኝ" ሲሉ ስሜታቸውን የሚገልጹት አባት፤ "እኔማ ምን ኑሮ አለኝ?. . .እንደ ልጄ ሄጄ ልሙት። ከዚህ በኋላ እኔ ኖሬ አልረባም። ንሰሀ ገብቼ ልሙት። ለቤተ ክርስቲያን ያልኩት ልጄ በከፋ አሟሟት፤ በጨካኝ [ነው]፤ እኔ ከእንግዲህ መንኘ እሞታለሁ እንጂ አርሼ አልበላም" ብለዋል።
"ቀጥታ ቤተ ክርስቲያን ግቢ ገብቶ ነው የመታቸው" ያሉት የሟች አባት፤ አስከሬኑ ላይ የደረሰውን ጉዳት በመግለጽ ግድያውን "ርሸና ነው" ብለውታል።
ሦስቱ ሟቾች "ተበርብረው" ከቤታቸው እንዲወጡ ተደርገው እንደተገደሉ የተናገሩት ነዋሪዎቹ፤ የእንስሳት ሐኪሙ ደግሞ "መሣሪያ ተገኝቶበታል" በሚል እንደተጠረጠረ እና ወደ ዋና መስመር "ፀደይ ባንክ" አካባቢ እንዲወጣ ተደርጎ መንገድ ላይ መገደሉን ተናግረዋል።
ሟቾቹ በእርሻ እና እንስሳት እርባታ ሥራ የተሰማሩ ቤተሰብ አስተዳዳሪዎች እንደሆኑም ተናግረዋል።
ከጥቃቱ ያመለጡት ሁለቱም የዓይን እማኞች ግድያውን የፈፀሙት "መከላከያ" ያሏቸው የመንግሥት ወታደሮች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሦስቱም ምንጮች ግድያውን ለምን እንደፈፀመ እንደማያውቁ እና የመንግሥት ኃይሎች ምን ፈልገው ወደ ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ እንደገቡ እንዳልተናገሩ ገልፀዋል።
የሟቾቹ ሥርዓተ ቀብር አስከሬኑ ላይ በደረሰው ጉዳት እንዲሁም በስጋት ምክንያት በምሽት እና በጅምላ መፈፀሙንም ተናግረዋል።
"[ተኩሱ] በረድ ሲል በስጋጃ እየጠቀለልን፤ ለቀብርም ሠውነታቸው ፈራርሶ አስቸግሮ [ነበር]" ሲሉ አራተኛ ልጃቸውን የቀበሩት አባት ተናግረዋል።
"መራራ ሀዘን" ደረሰብን ያሉ ከጥቃቱ የተረፉ አገልጋይም ሟቾቹ በሁለት ጉድጓድ በጅምላ መቀበራቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።
"ማኅበረሰቡ በጣም ሀዘን ላይ ነው። ሕዝቡ በጣም እያለቀሰ ነው፤ እያማረረ ነው። ከአቅም በላይ ከፍቶታል" ብለዋል።
ግድያው በአካባቢው ከባድ ድንጋጤ መፍጠሩን ነዋሪዎቹ ገልፀዋል።
ቤተ ክርስቲያኗ በመሣሪያ ተደብድባ ጉዳት እንደደረሰባት አገልጋዮች ተናገሩ ሲሆን፤ "የመቅደሱ ላይኛው ቆርቆሮ በሙሉ ተመትቷል፤ ግድግዳው ተመትቷል፤ ፈርሷል። በጣም ከባድ ጉዳት ነው የደረሰብን" ብለዋል።
ግድያውን ተከትሎ ቤተ ክርስቲያኒቷ መዘጋቷንም ሦስቱም ምንጮች ለቢቢሲ የተናገሩ ሲሆን፤ በሕይወት የተረፉ አገልጋዮች በስጋት ምክንያት ወደ ቤተ ክርስቲያን አለመመለሳቸውን ተናግረዋል።
ትናንት ሠኞ ሚያዚያ 12 የቅዱስ ሚካኤል ወርሃዊ በዓል የሚዘክር መርሃ ግብር እንዳልተደረገ እና የተወሰኑ አገልጋዮች "ኪዳን ብቻ" እንዳደረሱ ገልፀዋል።
በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ለመቀደስ እንዳልቻሉ ሲገልፁ፤ "ጓደኞቻችን ስለሞቱ አንሟላም" ብለዋል።
"የዕለቱን አምልጫለሁ፤ የነገውን እንዴት ያደርገኝ ይሆን እያልኩ እየፀለይኩ ነው። ኅብረተሰቡም ወጥቶ ለመመለስ ስጋት ገብቶታል" ሲሉ ያሉበትን ሁኔታ ገልፀዋል።
ደቡብ ጎንደር ዞን ባለፉት ወራት በፋኖ ኃይሎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ከፍተኛ ውጊያ እየተደረገበት ያለ አካባቢ ነው።
እንዳያመልጥዎ
ከየፈርጁ
በስፋት የተነበቡ
የሚፈልጉት ይዘት የለም