የዓለማችን ቀዳሚ ባለሀብት ኢላን መስክ ኢንቨስተሮችን በማሳሳት ጥፋተኛ ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኢላን መስክ ትዊተርን በገዛበት ወሳኝ ወቅት ለሕዝብ ባደረገው ንገግር ለኢንቨርስተሮች የተሳሳተ መረጃ ሰጥቷል በሚል ጥፋተኛ ተባለ።
ቲዊተር ላይ መዋዕለ ነዋያቸውን ያፈሰሱ ባለሀብቶች መስክ አሳስቶናል በሚል ያቀረቡትን ክስ ለሁለት ቀናት የተመለከቱት የሳን ፍራንሲስኮ የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኞች፤ የግዙፍ ቴክኖሎጂ ተቋማት ባለቤት በሆነው መስክ ላይ በአንድ ድምጽ ብይን ሰጥተዋል።
መስክ፤ ከሁለት ሳምንት በፊት በፍርድ ቤት ቃሉን በሰጠበት ወቅት፤ ኢንቨስተሮችን እንዳላሳሳተ ገልጿል። ሰዎች በአደባባይ የሚሰጣቸውን አስተያየቶች እና ትዊቶቹን ከሚገባው በላይ ትርጉም ሰጥተው እያነበቡ እንደሆነ በመጥቀስ ተከራክሯል።
ነገር ግን ዳኞቹ የትዊተር የተጠቃሚ መለኪያዎች (ሜትሪክስ) ላይ አሉ በሚል የጠቀሳቸው ችግሮች እንዲሁም ከ44 ቢሊዮን ዶላር የግዢ ስምምነቱ ሊያፈርስ እንደሚችል በይፋ መናገሩን ሆነ ተብሎ የተደረገ አሳሳች ድርጊት ሆኖ እንዳገኙት ገልጸዋል።
ኢላን መስክ እና ክሱን ያቀረቡት ኢንቨስተሮች በውሳኔው ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ቢጠየቁም ፈቃደኛ አልሆኑም።
ኢላን መስክ ትዊተር ላይ በሚጽፋቸው አስተያየቶቹ ምክንያት ክስ ሲቀርብበት ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
በአውሮፓውያኑ 2023 የቴሰላ ባለአክሲዮኖች ስለመኪና አምራቹ ኩባንያ ትዊተር ላይ ባወጣው ጽሁፍ አሳስቶናል በሚል ክስ ቢያቀርቡበትም ለማሸነፍ ችሎ ነበር።
ጉዳዩን የተመለከተው የዳኞች ቡድን አርብ ዕለት በሰጠው ውሳኔ መስክ ለሕዝብ ባሠጨራው መልዕክት ምክንያት በስድስት ወራት ውስጥ የትዊተር የአክሲዮን ዋጋ እንዲቀንስ አድርጓል።
በዚህ ውሳኔ መሠረትም ትዊተር ላይ መዋዕለ ነዋይ ያፈሰሱ ሰዎች ለደረሰባቸው ኪሳራ ማካካሻ በሺዎች የሚቆጠር ዶላር ካሳ ይከፈላቸዋል።
ውሳኔው ለመስክ "ግልጽ መልዕክት ያስተላለፈ ነው" ያሉት የሕግ ባለሙያ ሞንቴ ማን፤ "በንግግርህ በገበያው ተጽእኖ ካደረስክ፤ ዋጋውን ተከፍላለህ" ሲሉ የዳኞቹ ውሳኔን ደግፈዋል።
መስክ ከግንቦት 2022 ጀምሮ ከትዊተር የውሸት አካውንቶች ወይም "ቦቶች" ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በትዊተር ላይ ይጽፍ ነበር። ከግዢ ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ መውጣት እንደሚፈልግ እና ስምምነቱ መቋረጡንም ሲገልጽ ነበር።
ቢሊየነሩ ስምምነቱን እንዲያከብሩ ለማስገደድ ትዊተር መስክን ፍርድ ቤት ያቀረበው ሲሆን፣ ከዚያም በኋላ በመጀመሪያው የስምምነት ዋጋ ትዊተርን በመግዛት የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኩን ስያሜ ወደ "ኤክስ/X" ቀይሮታል።
ነገር ግን መስክ የትዊተርን ግዢ እንደተወው በመናገሩ ምክንያት አክሲዮኖችን በመግዛት የሚሸጡ የትዊተር ኢንቨስተሮች በሺዎች የሚቆጠሩ ድርሻዎቻቸውን በቅናሽ በመሸጥ ለኪሳራ እንደተዳረጉ በክሳቸው ገልጸዋል።
መስክ ከወራት በኋላ ትዊተርን በገዛበት ጊዜ በስምምነቱ መሠረት የከፈለው ገንዘብ ከፍተኛ ስለነበረ በባለድርሻዎች ላይ ኪሳራ መድረሱን በመጥቀስ ነው ክስ የመሠረቱት።
በዳኞች ፊት ቃሉን የሰጠው መስክ፣ የከሰሱትን ባለሀብቶች ወክለው ከቀረቡት ጠበቆች ጋር አጥብቆ ተከራክሯል።
መስክ የከሳሽ ጠበቆች ዳኞችን ለማሳሳት እየሞከሩ እንደሆነ በተደጋጋሚ በመናገር የተሟገተ ሲሆን፣ ለቀረቡለት ጥያቄዎች ቀላል "አዎ" ወይም "አይደለም" በማለት ለመመለስ ፈቃደኛ አልነበረም።
በመጨረሻም "ይህ ችሎት በትዊተር ላይ የማይረቡ ነገሮችን ስለጻፍኩ ከሆነ፣ ጥፋተኛ ነኝ እላለሁ" ሲል መስክ የቀረበበትን ክስ አምኗል።















