አሜሪካ እና እስራኤል፤ በኢራን ላይ ምን ዓይነት ሳይበር ጥቃቶች ፈጸሙ? ኢራንስ?

የፎቶው ባለመብት, Josef Cole, ALSSA
ወታደራዊ ጥቃት የመፈጸም ኃይልን የተመለከቱ ውይይቶች በሚነሱባቸው ወቅቶች አሜሪካ እና እስራኤል እንዴት ኢራንን እያጠቁ እንደሆነ በምሥል ጭምር ከማሳየት ወደ ኋላ አይሉም።
በባለሙያ የተዘጋጁ ፎቶዎች እና ቪዲዮዎችን የሚጠቀመው የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ፤ ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ የመሣሪያ፣ የጄት እና የመርከብ ዓይነቶችን የሚያሳዩ ልጥፎችን በየአጭር ሰዓት ልዩነት ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ይለጥፋል።
አሜሪካ እና እስራኤል በበይነ መረብ (ሳይበር) ምኅዳሩ ላይ እየተካሄደ ያለውን ነገር ለማሳየት ግን ይህንን ያህል ፍላጎት ያላቸው አይመስልም።
ለሰዓታት በሚቆዩት ጋዜጣዊ መግለጫዎች፣ በባለሥልጣናት ንግግሮች እንዲሁም በበርካታዎቹ የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፎች ላይ የሳይበር ዘመቻን የተመለከተ ገለጻ የለም ማለት ይቻላል።
ኢራናውያን የሳይበር መንታፊዎች (ሀከሮች) ግን ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በአሜሪካ ኩባንያ ላይ የሳይበር ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጸዋል። ጥቃት ተፈጽሞበታል የተባለው 'ስትራይከር' የተባለ የሕክምና ቴክኖሎጂ ኩባንያ ነው።
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ አድሚራል ብራድ ኩፐር በቅርቡ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደጠቆሙት፤ በዚህ ጦርነት ውስጥ የሳይበር ጥቃት ከፍተኛ ሚና አለው።
"ከባሕር ወለል እስከ ጠፈር እና የሳይበር ምኅዳር፤ ኢራን ላይ ጥቃት መፈጸማችንን እንቀጥላለን" ሲሉ ተናግረዋል።
በጦርነቱ ውስጥ ምን ዓይነት የሳይበር ዘመቻዎች እየተካሄዱ ስለመሆኑ የምናውቀው እንዲሁም ዘመቻዎቹ ስለ ዘመናዊ ውጊያ ምን እንደሚነግሩን በዚህ ዘገባ ቀርቧል።
ሚሳዔሎች ከመወንጨፋቸው አስቀድሞ
በጦርነት "ቅድመ ዝግጅት" ውስጥ የሳይበር ስለላ ወይም ምንተፋ ትልቅ ሚና ይጫወታል።
የፔንታጎን የጋራ ወታደራዊ አዛዦች ሊቀ መንበር የሆኑት ጄነራል ዳን ኬን፤ የጦርነቱ አካሄድ በተመለከተ ለወራት፤ አንዳንድ ጉዳዮች ላይም ለዓመታት ዕቅድ ሲዘጋጅለት እንደነበር ተናግረዋል።
ጥቃት የሚፈጸምባቸውን "የዒላማዎች ስብስብ" መለየት የዕቅዱ አካል እንደነበረም ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አብራርተዋል።
የጥቃት ዕቅድ ከመዘጋጀቱ አስቀድሞ የአሜሪካ እና የእስራኤል የሳይበር መንታፊዎች ወሳኝ ወደሆኑ የኢራን የኮምፒውተር ኔትዎርኮች ውስጥ ሰርገው ገብተው ሊሆን ይችላል።
ከአየር መከላከያ እና ወታደራዊ ኮሚዩኒኬሽን ጀርባ ያሉ የኮምፒውተር ኔትዎርኮች የሳይበር መንታፊዎች ዋነኛ ዒላማ መሆናቸው አይቀሬ ነው።
የብሪታኒያው ፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ ስማቸው ያልተጠቀሰ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው፤ እስራኤል ግዙፍ የክትትል መረብ ለመገንባት እንዲያስችላት በኢራን ጎዳናዎች የሚገኙ የደኅንነት እና የትራፊክ ካሜራዎችን ጠልፋ ነበር።
በእነዚህ ካሜራዎች አማካኝነት ኋላ ላይ ጥቃት የተፈጸመባቸው አያቶላህ አሊ ኻሜኒ እና ወታደራዊ አዛዦቻቸው "የዘውትር የውሎ ልምድ" ምን እንደሚመስል እንደተጠና በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ከኢንተርኔት ጋር የተገናኙ ካሜራዎች "በአነስተኛ ወጪ የመንገዶች፣ የተቋማት እና የእንቅስቃሴዎችን ሁኔታ የተመለከተ የትክክለኛ ጊዜ መረጃ ስለሚያስገኙ" በሳይበር ውጊያ ውስጥ ዒላማ እየሆኑ መምጣታቸውን 'ቼክ ፖይንት' የተሰኘው የሳይበር ደኅንነት ኩባንያ የስጋት ስለላ ባለሙያ የሆኑት ሰርጌ ሻይኬቪች ያስረዳሉ።
ይህ ዓይነቱ መረጃ ሰላዮችን እንደማሰማራት ባሉ መደበኛ የስለላ ተግባራት ከሚገኘው መረጃ ጋር ተዳምሮ ጥቅም ላይ እንደሚውል አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።
በእስራኤል ጦር የሳይበር መከላከል ባለሙያ የነበሩት ታል ኮሌንደር በበኩላቸው፤ "ብዙውን ጊዜ የሳይበር ዓለም ባለቤትነቱ የእኛ የሆነ ወሳኝ መሣሪያ አይደለም። የመረጃ ከባቢውን ለመቅረጽ የሚደግፍ እና በምድር ላይ ለሚከናወኑ ዘመቻዎችን የሚያግዝ አቅም መጨመሪያ መሣሪያ ነው" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢራን ላይ የመጀመሪያዎቹ ጥቃቶች ከተፈጸሙ በኋላ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጄነራል ኬን፤ የአሜሪካ የሳይበር እና የጠፈር ዕዞችን "የመጀመሪያዎቹ እርምጃ ፈጻሚዎች" ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
እነዚህም "የኢራንን የመመልከት፣ ግንኙነት የማድረግ እና ምላሽ የመስጠት አቅሞችን እንደገደቡ" እና እንዳስተጓጎሉም በማንሳትም አሞካሽተዋቸዋል።
ለምሳሌ፤ የአያቶላህ ኻሜኒ የደኅንነት ቡድን ወደ ስፍራው እየመጣ ያለን ተዋጊ ጄት በተመለከተ ማስጠንቀቂያ እንዳይደርሰው ሲባል የሞባይል ስልክ ማማዎች እንዲጠለፉ ወይም እንዲጠፉ ተደርገው ሊሆን እንደሚችል አስተያየት ሰጪዎች ይጠቁማሉ።
ይህ ዓይነቱ ድርጊት ስለመፈጸሙ ማረጋገጫ አልተገኘም። ነገር ግን እንደ የዩክሬን ጦርነት ባሉ የተለያዩ ግጭቶች ውስጥ መሰል እርምጃዎች ተወስደው ተመልክተናል።
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴትም በቅርቡ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኢራን ጦር አባላት "መቀናጀት እና ቀጣይነት ያለው ጥቃት መፈጸም ቀርቶ መነጋገር ወይም ግንኙነት መፍጠር አይችሉም ነበር" በማለት በኩራት ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ይህ አስተያየት ፕሬዝዳንት ትራምፕ የቬንዙዌላውን ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን ከአገራቸው ስለወሰዱበት ዘመቻ ስኬት ከተናገሯቸው ቃላት ጋር ይመሳሰላል።
ትራምፕ "እኛ ባለን የሆነ ብቃት የተነሳ የካራካስ (የቬንዙዌላ ዋና ከተማ) መብራቶች በአብዛኛው ጠፍተው ነበር" ሲሉ ከዘመቻው በኋላ መናገራቸው ይታወሳል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዝዳንቱ በዚህ ንግግራቸው እያመለከቱ የነበረው የሳይበር ጥቃት ስለመፈጸሙ ይሁን አይሁን አልተረጋገጠም።
ይሁን እንጂ ትራምፕ በቅርቡ የታተመ የአሜሪካ የሳይበር ስትራቴጂ ሰነድ ላይ የአገሪቱ የሳይበር ኃይሎች "እንከን የለሽ በሆነው በዚህ ወታደራዊ ዘመቻ ወቅት ጠላቶቻችን ማየት እና መረዳት እንዳይችሉ" አድርገዋል ሲሉ አሞካሽተዋል።
በተጨማሪም እስራኤል 'ባዴሳባ' የተባለውን እና ከአምስት ሚሊዮን በላይ በሆኑ ሰዎች ዳውንሎድ የተደረገውን ታዋቂውን የኢራን የጸሎት ሰዓት መሙያ አፕሊኬሽን ጠልፋለች የሚል ክስ ይቀርብባታል።
ኢራን ላይ ቦንብ መዝነብ እንደጀመረ የአፕሊኬሽኑ ተጠቃሚዎች "እርዳታ ደርሷል" የሚል መልዕክት (ኖቲፊኬሽን) እንደደረሳቸው ሮይተርስ ዘግቧል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ሄግሴት "ግድያ የሚፈጸምባቸው ሲስተሞችን የማደን" ዘመቻ መቀጠሉን በተመለከተ በዚህ ሳምንት ባደረጉት ንግግር፤ ጦርነቱ በደረሰበት በዚህ ደረጃ ሳይበር ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ኢራን ውስጥ የሚገኙ ወታደራዊ ዒላማዎችን ለመለየት እንዲቻል የኦፕን ሶርስ ኢንተለጀንስ (ለማንም ክፍት የሆኑ መረጃዎች)፣ የሳተላይት ምሥል ትንተና እና የሳይበር ስለላ ጥቅም ላይ እንደሚውልም አስረድተዋል።
የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) መገልገያዎችም በከፍተኛ ደረጃ ጥቅም ላይ እየዋሉ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። ይህንን በተመለከተም ፍንጭ የተገኘው ሥራ ላይ የተመለከቷቸውን መኮንኖች ሲያመሰግኑ ከነበሩት የመከላከያ ሚኒስትሩ ሄግሴት ነው።
ሚኒስትሩ "ኢራናውያን ለማከናውን የሚሞክሯቸውን የተለያዩ ነገሮች ዒላማ የምናደርበትን፣ የምናገኝበትን እና የምናስተካክልበትን መንገድ ለማዘመን ከሚሠራ ወጣት ኮሎኔል ጋር ተነጋግሬ ነበር" ሲሉ ብዙ መረጃ ላለመስጠት በሚጠነቀቅ አኳኋን ተናግረዋል።
የሳይበር ጦርነት ደመና
አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ ከፍተኛ የሳይበር ጥቃቶችን የማድረስ የረጅም ጊዜ ታሪክ አላቸው። ይህንን ተግባራቸውን የሚይዙት በምሥጢር እንደሆነ ይታወቃል።
ለምሳሌ፤ በአውሮፓውያኑ 2010 የኢራን ዩራኒያም ማበልጸጊያ ተቋም ላይ የፈጸሙትን አውዳሚ የ'ስቱክስኔት' ጠለፋ በተመለከተ ባለሥልጣናት አሁንም ድረስ በዝርዝር ከመናገር ይቆጠባሉ።
በ2022 ደግሞ እስራኤል 'ፕሬዳቶሪ ስፓሮው' በተሰኘው የእስራኤል ደጋፊ የሳይበር ጠላፊዎች ቡድን ስም ኢራን ውስጥ የሚገኝ የብረት ፋብሪካ ላይ ጉዳት አድርሳለች የሚል ክስ ይቀርብባታል።
የቀድሞው የእስራኤል ጦር የሳይበር መከላከል ባለሙያ ኮሌንደር፤ "አንድ አገር ያለውን አቅም ወይም አንድ ዘመቻን በተመለከተ በይፋ የሚናገር ከሆነ ቴክኒኮችን፣ የመግቢያ ነጥቦችን ወይም የስለላ ምንጮችን የማጋለጥ አደጋ ይጋረጥበታል። ይህም ጠላት [እነዚህን መንገዶች] በፍጥነት እንዲዘጋ ሊያደርግ ይችላል" ይላሉ።
"በሳይበር ዓለም ውስጥ ብዙውን ጊዜ አንድ እርምጃን የመውሰድ አቅም ዋጋው የሚለካው ተቃራኒው ወገን ነገርየው እንዴት እንደሚሠራ በትክክል አለማወቁ ላይ ነው" ሲሉም ባለሙያዋ ያክላሉ።
'የሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት' ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ሉዊስ ማሪ ሁሬል በበኩላቸው አሜሪካ ይፋ ባደረገቻቸው መረጃዎች መገረማቸውን ይናገራሉ።
የጦርነት ሕጎች መከበራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል ልክ እንደ መደበኛ ውጊያ ሁሉ የሳይበር ጥቃትም ንግግር ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ይህ ጦርነት ማሳየቱን ያስረዳሉ።
"የአሁኑ ሁኔታ በሰፊ ወታደራዊ ዘመቻዎች እና በቀውስ ወቅት ሳይበር የሚያቀርበውን እገዛ እና ስትራቴጂክ ጥቅም በተመለከተ ይበልጥ በይፋ ለመከራከር ዕድል ይፈጥርልናል" ይላሉ።
"ሳይበር የጥቃት ዝርዝሩ አካል እንደሆነ በግልጽ እውቅና የሚሰጥ ከሆነ፤ የትጥቅ ግጭት ሕጎች፣ ተመጣጣኝነት እንዲሁም አቅምን መጠቀም ተብለው የሚወሰዱ ጉዳዮችን በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎችን በደንብ ቅርጽ ለማስያዝ ያግዘናል" ሲሉም ያብራራሉ።
በሳይበር ጥቃት ኢራን የቱ ጋ ነች?
እየተካሄደ ባለው ጦርነት ውስጥ እንቆቅልሽ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ኢራን በሳይበር መስክ ላይ ያንን ያህል የምትታይ ያለመሆኗ ነገር ነው።
እስካሁን ከኢራን ጋር በተያያዘ የሚጠቀሰው የሳይበር ጥቃት በአሜሪካው የቴክኖሎጂ ኩባንያ 'ስትራይከር' ላይ የደረሰው ምንተፋ ነው።
ለረጅም ጊዜ ኢራን የሳይበር ጥቃት የማድረስ አቅም ያላት አገር ተደርጋ ስትቆጠር ቆይታለች። የምዕራባውያን ሳይበር ደኅንነት ዓለም በመንግሥትም ይሁን ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ባላቸው መንታፊዎች የሚፈጸም ጥቃትን ለመከላከል ዝግጁ ቢሆንም እስካሁን ድረስ በኢራን በኩል የጎላ እንቅስቃሴ አልታየም።
ስትራከር ላይ ምንተፋ ከተፈጸመ በኋላ ሠራተኞች ወደ ኩባንያው ሲስተም ለመግባት (ሎግ ኢን ለማለት) ተቸግረው ነበር።
በኢራን በሚደገፍ የጠላፊዎች ቡድን በተፈጸመ የ'ዋይፐር' ጥቃት የኩባንያው መረጃዎች ሙሉ ለሙሉ እንደተደመሰሰ የሚገለጽ መልዕክት ለሠራተኞች ታይቷቸዋል። የኢራን መንግሥት ቴሌቪዥንም ይህንኑ ገልጿል።
ኩባንያው በማግሥቱ ባወጣው መረጃ መስተጓጎሉ እንዲቋጭ ለማድረግ እየሠራ እንደሆነ እና የሚያቀርባቸው ምርቶችን መጠቀም የደኅንነት ስጋት እንደማይፈጥር ገልጿል።
በዚህ ጦርነት ሌሎች የሳይበር ጥቃቶች ያልታዩት ኢራን ራሷን እያቀበች ስለሆነ ነው ብሎ ማሰብ የማይዋጥ ነው። ስለዚህ በእስራኤል ተፈጽሟል በተባለው ጥቃት የኢራን የሳይበር አቅም ተሽመድምዷል አልያም ቀድሞውንም ያልሆነ ቦታ ነበር የተሰጣት ማለት ነው።
የኢራን የሳይበር አቅም ዝናውን ያገኘው ከዚህ ቀደም በፈጸመቻቸው ጥቃቶች መጠነ ሰፊነት ነው። ከእነዚህ ጥቃቶች አንዱ በአውሮፓውያኑ 2012 ንብረትነቱ የተቀናቃኟ የሳዑዲ አረቢያ በሆነው ግዙፉ 'አራምኮ' የነዳጅ ኩባንያ ላይ የተፈጸመው ነው።
በዋይፐር ማልዌር አማካኝነት በተፈጸመው ጥቃት የተነሳ 30 ሺህ ኮምፒውተሮች ከጥቅም ውጪ ሆነዋል።
'ሃንዳላ' የተባለው ከኢራን ጋር ግንኙነት ያለው የጠላፊዎች ቡድን የአሜሪካው የሜዲካል ቴክኖሎጂ ኩባንያ 'ስትራይከር' ላይ የፈጸመውም የዋይፐር ማልዌር ጥቃት እንደሆነ ተዘግቧል።
ኢራን ከዋይፐር ጥቃቶች በተጨማሪ ወሳኝ ብሔራዊ መሠረተ ልማቶች ላይ አካላዊ ጉዳት ለማድረስ ትሞክራለች የሚል ክስ ይቀርብባታል።
'የሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት' ባልደረባዋ ዶ/ር ሉዊስ ማሪ ሁሬል፤ ኢራን በቀጥታም ሆነ በጠላፊ ቡድኖች አማካኝነት የአጸፋ እርምጃ የመውሰድ አቅሟን አቃልሎ መመልከት እንደማይገባ ያሳስባሉ።















