ናይጄሪያ በመፈንቅለ መንግሥት ሴራ ተሳትፈዋል ያለቻቸውን ስድስት ሰዎች በአገር ክህደት ከሰሰች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በናይጄሪያ ጡረታ የወጡ ሜጀር ጄኔራል እና የፖሊስ ኢንስፔክተርን ጨምሮ ስድስት ሰዎች ባለፈው ዓመት የፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቢንን አስተዳደር ለመገልበጥ ሞክረዋል በሚል በአገር ክህደት ወንጀል ክስ ተመሰረተችባቸው።

ሰዎቹ የተከሰሱት በዋና ከተማዋ አቡጃ በሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆን ተከሳሾቹ ረቡዕ ዕለት በዳኛ ጆይስ አብዱልማሊክ ፊት ይቀርባሉ።

የቀድሞ ገዥ እና የአንድ ጊዜ የነዳጅ ሚኒስትር የነበሩት ቲምፕሬ ሲልቫ ስማቸው ቢጠቀስም በቁጥጥር ሥር አለመዋላቸውን የፍርድ ቤቱ ሰነዶች አመልክተዋል።

የመፈንቅለ መንግሥቱ ሴራ ለመጀመሪያ ጊዜ የወጣው እአአ በጥቅምት 2025 ሲሆን መንግሥት የናይጄሪያን 65ኛ የነፃነት በዓል ለማክበር ያሰናዳውን ወታደራዊ ሠልፍ በድንገት በመሰረዙ ነው።

በወቅቱ ባለሥልጣናት የደህንነት ስጋቶችን ቢጠቅሱም ሰልፉ የተሰረዘው ከመፈንቅለ መንግሥት ሴራ ጋር በተያያዘ መሆኑን መላምቶች ሲሰጡ ቆይተዋል።

የአገሪቱ ጦር ሃሳቡን ውድቅ ቢያደርገውም በጥር ወር ፕሬዚዳንቱን ከሥልጣን ለማውረድ በመሞከራቸው 16 መኮንኖች በወታደራዊ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ አስታውቋል።

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረቡት ክሶች ሽብርተኝነትን እና ሕጋዊ ያልሆነን ገንዘብ ወደ መደበኛ ዝውውር ማስገባትን ያካተቱ ሲሆን ከወታደራዊ ክሶች በተጨማሪነት ስለመቅረባቸው ግልጽ አይደለም።

በቀድሞው ፕሬዝዳንት ሙሃሙዱ ቡሃሪ ዘመን እአአ ከ2019 እስከ 2023 የነዳጅ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት እና ከ2007 እስከ 2012 ደግሞ በነዳጅ የበለጸገችው የቤሴላ ግዛት ገዥ የነበሩት ሲልቫ፣ ቤታቸው ባለፈው ጥቅምት ወር በመርማሪዎች መበርበሩን ተከትሎ ከመፈንቅለ መንግሥት ሴራ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው አስታውቀዋል።

በቀጣዩ ወር ከአገሪቱ ጸረ-ሙስና ቢሮ የተለየ ክስ ላይ የእስር ማዘዣ ወጥቶባቸዋል። በወቅቱ ቃል አቀባያቸው የቀድሞው ሚኒስትር ለሕክምና ምርመራ የዑኬ እንዳሉ እና ክሶቹ ፖለቲካዊ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በጠቅላይ አቃቤ ሕግ ክስ ውስጥ የተጠቀሱት፡

  • መሐመድ ኢብራሂም ጋና፣ የጡረታ የወጡ ሜጀር ጄኔራል
  • ኤራስመስ ኦቼጎቢያ ቪክተር፣ የጡረታ የባህር ኃይል ካፒቴን
  • አህመድ ኢብራሂም፣ የፖሊስ ኢንስፔክተር
  • ዘከሪ ኡሞሩ፣ በፕሬዚዳንታዊ ቪላ ውስጥ የሚሠራ የኤሌክትሪክ ባለሙያ
  • ቡካር ካሺም ጎኒ፣ ሲቪል
  • አብዱልቃዲር ሳኒ፣ የእስልምና መሪ

በክስ ወረቀቱ መሠረት እስካሁን በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ያልሰጡት ስድስቱ ተከሳሾች "ፕሬዚዳንቱን ከመጠን በላይ ለማስፈራራት በመንግሥት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር እርስ በእርስ ተባብረዋል" ይላል።

በፍርድ ቤቱ መረጃዎች መሠረት የመፈንቅለ መንግሥት ሴራው የተመራው ኮሎኔል መሐመድ አልሃሳን ማጂ እንደሆነ ይጠቁማሉ። ኮሎኔሉ እና ሌሎች ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል።

አቃቤ ህግ ተከሳሾቹ ስለኮሎኔል ማጂ "የክህደት ድርጊት" ቀደም ብለው መረጃ ቢኖራቸውም ለባለስልጣናት አላሳወቁም።

በናይጄሪያ ህግ መሰረት አገር ክህደት በጣም ከባድ ከሆኑ ወንጀሎች አንዱ ሲሆን የዕድሜ ልክ እስራትን ጨምሮ ከባድ ቅጣት ሊያስከትል ይችላል።

ናይጄሪያ እአአ ከ1999 ጀምሮ በሲቪል አገዛዝ ስር ትገኛለች። የጦር ኃይሉ ለሲቪል ባለሥልጣናት ያለውን ታማኝነት በተደጋጋሚ አጽንኦት ሲሰጥ ቆይቷል። ለዲሞክራሲ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጡ የህዝብ መግለጫዎችን አውጥቷል።