በኮሎምቢያ ወታደራዊ አውሮፕላን ተከስክሶ 66 ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኮሎምቢያ የጦር አውሮፕላን በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል በረራ ማድረግ በጀመረ በተወሰነ ደቂቃ ውስጥ ባጋጠመው አደጋ ተከስክሶ ቢያንስ 66 ሰዎች መሞታቸውን ባለሥልጣናት አረጋግጠዋል።
በአደጋው ከሟቾቹ በተጨማሪ በርካቶች መቁሰላቸውም ተነግሯል።
የኮሎምቢያ አየር ኃይል አዛዥ ካርሎስ ፈርናንዶ ሲልቫ ሩኤዳ እንደተናገሩት የጦር አውሮፕላኑ 114 የሠራዊት አባላትን እና 11 የበረራ አስተናጋጆችን አሳፍሮ ነበር።
አሜሪካ ሠራሹ ሲ-130 ሄርኩልስ የተሰኘው ይህ አውሮፕላን ወታደሮችን ለማጓጓዝ የሚያገለግል ሲሆን፣ አደጋው የደረሰበት ፑቱማዮ ግዛት ውስጥ ፑኤርቶ ሌጉይዛሞ በተባለ ስፍራ ነው።
ወደ አካባቢው የተላኩ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በሕይወት የተረፉ ሰዎችን ከአውሮፕላኑ ስብርባሪ ውስጥ ሲፈልጉ ታይተዋል።
የአደጋው መንስኤ ገና በመጠራት ላይ ነው።
አደጋውን ተከትሎ የኮሎምቢያ መከላከያ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ "የጦር አውሮፕላኑ ሠራዊታችንን ለማጓጓዝ ከፑኤርቶ ሌጉይዛሞ ሲነሳ አሰቃቂ አደጋ አጋጥሞታል" ብለዋል።
ከጎረቤት አገር ፔሩ አቅራቢያ የደረሰውን ይህ አደጋ "በእጅጉ የሚያሳዝን" ብለውታል መከላከያ ሚኒስትሩ።
ሚኒስትሩ አውሮፕላኑ አደጋ ደርሶበት በእሳት ሲያያዝ በውስጦ ተጭነው የነበሩ ተተኳሾች መፈንዳታቸውንም አክለዋል።
ሁለት ወታደራዊ ምንጮች ለሮተይተርስ በሰጡት መረጃ መሠረት 66 ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጠዋል።
አደጋው በኮሎምቢያ አየር ኃይል የቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ እጅግ ዘግናኝ የሚባለው ነው።
በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን የተጋሩ ምስሎች እንደሚያሳዩት በስፍራው ከፍተኛ የሆነ ጭስ እና የወታደሮች ስምሪት ታይቷል።
በተጨማሪም የአካባቢው ሰዎች የተጎዱ የሠራዊት አባላትን በሞተር ሳይክል እየጫኑ ወደ ሆስፒታል ሲያመላልሱ ተስተውለዋል።
የኮሎምቢያ ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔትሮ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት "ይህ አሰቃቂ አደጋ መከሰት አልነበረበትም" ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ባጋሩት ረዥም ጽሑፍ አየር ኃይሉን ለማዘመን ጥረት ቢያደርጉም "የቢሮክራሲ ችግር" እቅዳቸውን እንዳስተጓጎለባቸው ተናግረዋል።
"የወጣት ሕዝባችን ሕይወት አደጋ ተጋርጦበት ምንም ዓይነት የዕቅድ መዘግየት አልፈልግም" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ። ቢሆንም ግን አደጋውን ያስከተለውን ምክንያት ከማብራራት ተቆጥበዋል።
ባለፈው ወር ተመሳሳይ ሥሪት ያለው የቦሊቪያ የጦር አውሮፕላን ተከስክሶ 20 ሰዎች ሞተዋል።















