በቀን ለምን ያህል ሰዓት እንቀመጣለን? በጤናችን ላይ የሚያደርሰው ጉዳትስ ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በሥራ ቦታ፣ በትራንስፖርት ላይ፣ በቤት ውስጥ… ብዙዎቻችን በቀን ለረዥም ሰዓታት በመቀመጥ እናሳልፋለን።

ነገር ግን ለረጅም ጊዜ ተቀምጦ መቆየት እንደ የልብ የደም ቧንቧ እና ዓይነት ሁለት የስኳር በሽታ ያሉ ከባድ የጤና እክሎች የመፈጠር ዕድልን ይጨምራል።

በአውሮፓውያኑ 1953 የሕብረተሰብ ጤና ባለሙያ የሆኑት ጄረሚ ሞሪስ የለንደን አውቶቡስ አሽከርካሪዎች ከረዳቶቻቸው አንጻር በልብ ሕመም የመያዝ ዕድላቸው ከእጥፍ ይበልጣል ብለው ነበር።

በዕድሜ፣ በፆታ እና በገቢ ሁለቱም ተመሳሳይ ቢሆኑም ለምን ትልቅ ልዩነት ተፈጠረ?

የአውቶቡስ ረዳቶች በእግራቸው እንዲቆሙ እና ትኬት ለመሸጥ ደግሞ የለንደንን ባለ ሁለት ፎቅ አውቶቡሶች ደረጃዎችን መውጣት እና መውረድ ይጠበቅባቸዋል።

አሽከርካሪዎቹ ግን ለረጅም ጊዜ ለመቀመጥ ይገደዳሉ፤ ይህ አስደናቂ ጥናት በአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና በልብ ጤና መካከል ያለውን ግንኙነት ለመመርመር መሠረት ጥሏል።

የለንደን አውቶቡስ ረዳቶች አሁን ባይኖሩም የሞሪስ የጥናት ውጤት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጠቃሚ ሆኗል። ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወዲህ ከቤት መሥራት በመጨመሩ የምንቀመጥበትን ጊዜ ሊጨምር ይችላል።

የቢሮ ባህል በ1980ዎቹ የሥራ ሕይወታችንን በእጅጉ ስለለወጠው አንዳንድ ተመራማሪዎች የእኛ ዝርያ ከሆሞ ሳፒየንስ ይልቅ ሆሞ ሴደንስ “የተቀመጠው ሰው” ሆኗል ሲሉ እንዲቀልዱ አርጓቸዋል።

ረዘም ላለ ጊዜ መቀመጥ የምናወጣውን ጉልበት ይቀንሳል። ቴሌቪዥን መመልከት፣ ጌም መጫወት፣ መኪና መንዳት እና ከጠረጴዛ ጋር የተያያዘ ሥራን ጨምሮ የተለያዩ ተቀምጠን የምናከውናቸው ነገሮች ናቸው።

የመቀመጥ ባህል ለከፍተኛ የልብ እና የደም ቧንቧ ሕመም፣ ለዓይነት ሁለት የስኳር በሽታ እና ያለጊዜው ሞትን የማስከተል ዕድሉ ከፍተኛ ሲሆን፣ በተለይ ቁጭ ብለን የምናሳልፈው ጊዜ ለተለያዩ የጤና እክሎች አስተዋጽኦ እንዳለው ተለይቷል።

በአውሮፓውያኑ 2020 የዓለም ጤና ድርጅት ያለመንቀሳቀስ ባህሪን ለመቀነስ የሚረዱ እርምጃዎችን ጠቁሟል።

ከ2010 ጀምሮ ተመራማሪዎች ያለመንቀሳቀስ ባህሪ ከአካላዊ እንቅስቃሴ ካለማድረግ የተለየ መሆኑን ለመጠቆም ይፈልጋሉ። ቁጭ ብለውም በቀን በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ይችላሉ። ነገር ግን በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማያደርጉ ሰዎች የአደጋው ስጋት ይጨምራል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ያለመንቀሳቀስ ለምን በልብ እና በደም ሥር (ካርዲዮቫስኩላር) በሽታዎች የመጋለጥ ዕድልን ይጨምራል? ዋናው መላምት በተለይ በእግሮች ላይ የደም ሥር (ቧንቧ) ያለመሥራት ችግር መጨመር ነው። የደም ሥር ለደም እና ለፈሳሽ ዝውውር ዋና ኃላፊነት አለበት።

በአውስትራሊያ በሚገኘው የዴኪን ዩኒቨርሲቲ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና የሥነ ምግብ ተቋም የፊዚዮሎጂ ባለሙያ የሆኑት ዴቪድ ዳንስታን ረዥም ጊዜ መቀመጥ የሚያስከትለውን ውጤት እና ሊደረጉ የሚችሉ መፍትሔዎችን በሰፊው መርምረዋል።

“መቀመጥ የሚታወቀው በጡንቻ እንቅስቃሴ መቀነስ ነው። ወንበር ላይ ከሆንኩ ወንበሩ ኃላፊነቱን ሁሉ ይወስዳል” ብለዋል ዱንስታን።

የጡንቻ እንቅስቃሴ መቀነስ፣ ዝቅተኛ የሜታቦሊክ ፍላጐት እና የስበት ኃይሎች ጥምር ውጤት ወደ እግር ጡንቻዎች አካባቢ ያለውን የደም ፍሰት ይቀንሳል። ይህም ጡንቻዎች ውስጥ ደም እንዲሰበሰብ ያደርጋል። ብዙውን ጊዜ እግሮቹን በማጠፍ መቀመጥ የደም ፍሰትን ሊቀንስ ይችላል።

የእግር ጡንቻዎች እንቅስቃሴ መቀነስ የሜታቦሊክ ፍላጎትን ይቀንሳል። የሜታቦሊክ ፍላጐት የደም ዝውውርን በዋነኛነት የሚወስን ነው። ስለዚህ በእግሮች ውስጥ ያለው የደም ፍሰትም ይቀንሳል። ይህ ደግሞ የደም ዝውውርን ሊቀንስ ይችላል።

በመደበኛ የደም ዝውውር ወቅት በደም ሥሮች ግድግዳ ላይ ባሉት የኢንዶቴልየም ሴሎች እና በደም መካከል ፍትጊያ ይፈጥራል። ይህም እንቅስቃሴዎች በመደበኛነት እንዲከወኑ ይረዳል።

የደም ዝውውር መቀነስ በተቃራኒው የደም ስሮች ጠባብ እንዲሆኑ ያደርጋል። ይህም የደም ፍሰትን የበለጠ ይቀንሳል። ደም እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ በሚል ደግሞ የደም ግፊት ይጨምራል። ከፍተኛ የደም ግፊት ለልብ እና ለደም ስር በሽታዎች ከሚያጋልጡ ምክንያቶች አንዱ ነው።

16 ዓመት ወጣት እና ጤናማ ወንዶች ላይ የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው ከሆነ ለሦስት ሰዓታት መቀመጥ በእግሮች ላይ የደም ክምችት፣ የደም ቧንቧን የመቋቋም ችሎታ፣ ዲያስቶሊክ የደም ግፊት እና የእግሮች ክብነትን ይጨምራል።

ሌላ ጥናት እንዳመለከተው ደግሞ ያለማቋረጥ መቀመጥ የደም ግፊትን ይጨምራል። ከ120 እስከ 180 ደቂቃዎች መቀመጥ በጣም ረጅም ጊዜ የመቀመጥ ጣራ እንደሆነ ተመራማሪዎች ይጠቁማሉ። የደም ቧንቧ ችግርም በተቀመጡት ጊዜያት ይጨምራል።

ከፍተኛ ቅባት ያለው ምግብ ከተመገብን በኋላ ለረዥም ጊዜ መቀመጥ ደግሞ የበለጠ ጎጂ ነው ተብሎ ይታሰባል።

የጡንቻዎች ሥርዓትም ሊጎዳ ይችላል። ረዘም ላለ ጊዜ መቀመጥ የጡንቻዎችን ጥንካሬ መቀነስ፣ የአጥንት ጥንካሬ መቀነስ እና ስብ እንዲጨምር አስተዋጽኦ ያደርጋል።

በተጨማሪም ረዘም ላለ ጊዜ መቀመጥ ከአካላዊ ምቾት ማጣት፣ በሥራ ላይ ከሚፈጠር ጫና እና ከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት ጋር የተቆራኘ ነው። አልፎ ተርፎም ቁስለት ሊያስከትል ይችላል።

ዓይነት ሁለት የስኳር በሽታን በመመርመር ላይ ያተኮሩት ዱንስታን ከምግብ በኋላ ለረዥም ሰዓት መቀመጥ በደም ውስጥ ያለው የግሉኮስ እና የኢንሱሊን መጠን ይጨምራል።

የተዳከመ የኢንሱሊን እና የተዳከመ የደም ቧንቧ ሥራ የልብ እና ለደም ቧንቧ በሽታ እንዲሁም ለዓይነት ሁለት የስኳር በሽታ ተጋላጭነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

እነዚህ ሁሉ ችግሮች ካሉ ለምን ለረጅም ጊዜ እንቀመጣለን? ልማዱን መስበር እንችላለን?

“እኔ እንደማስበው ሰዎች ይበልጥ መቀመጥን ይመርጣሉ። ሕብረተሰቡም የሚያበረታታው ይህንኑ ነው” ይላል።

ሰዎች ለምን ለረጅም ጊዜ እንደሚቀመጡ ሲመረምሩ የቆዩት በሰሪ ዩኒቨርሲቲ ሳይኮሎጂስት የሆኑት ቤንጃሚን ጋርድነር “ማንም ሰው ሆን ብሎ ያደረገው አይደለም። ነገሮች ይበልጥ የተመቹ እየሆኑ ሲሄዱ ብዙ አንቀሳቀስም” ብለዋል።

በአውሮፓውያኑ 2018 ጋርድነር እና ባልደረቦቻቸው በስብሰባዎች ላይ መቆም የሚያበረታቱ ሰዎች ልዩ ማኅበራዊ እንቅፋቶችን እንደሚፈጠር ተገንዝበዋል።

“ሰዎች በሦስት የተለያዩ ስብሰባዎች ላይ [መቆምን] እንዲሞክሩ አበረታተናል። እንዴት እንዳገኙት ለማወቅ ከእያንዳንዱ ስብሰባ ኋላ ቃለ መጠይቅ አደረግንላቸው። ግኝቶቹም አስደናቂ ነበሩ” ሲሉ ጋርድነር ተናግረዋል። “በመደበኛ ስብሰባ ላይ መቆም ተገቢ እንዳልሆነ ተሰምቷቸዋል።”

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሌሎቹ እንደመፍትሔ የሚቀርቡት ደግሞ የሥራ ቦታዎች ላይ ከቁመት ጋር የሚስተካከሉ በመቆም ለመሥራት የሚያስችሉ ወንበሮች እና የእግር ማስቀመጫ መጠቀም የደም ፍሰትን ይጨምራል።

ደጋግሞ ከወንበር መነሳት እና ቀላል የእግር ጉዞ ማድረግ ወይም ደረጃዎችን መውጣት እና መውረድ ጠቃሚ እንደሆነ ታይቷል።

በእጅ ወይም በሌላ አካል ላይ የሚጠለቁ ቴክኖሎጂዎችም ሊረዱን ይችላሉ። ተስፋ ሰጪ በሆነ አዲስ ጥናት መሠረት አክስሌሮሜትሮች የሚባሉ የሚጠለቁ መሳሪያዎች የ24 ሰዓታት የግላዊ ባህሪያትን ማለትም የመቀመጥ፣ የመቆም፣ የመኝታ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በተመለከተ መረጃ ሰጥተዋል።

መሳሪያዎቹ በጣም ረዥም ጊዜ በተቀመጥን ቁጥር መነሳት እንዳለብን ያስታውሳል። ቴክኖሎጂ ግን ጎንዮሽ ጉዳትም አለው። ምክንያቱም አንዳንዶች በመልዕክቱ ሊበሳጩ ወይም ሊነኩ ይችላሉ።

ጋርድነር እና ባልደረቦቻቸው በተቀመጥን እና በቆምን ቁጥር በየመሃሉ መንቀሳቀስን ያበረታታሉ። በተለይ ዝቅተኛ እንቅስቃሴ ላላቸው ግለሰቦች በየመሃሉ መቆም ብቻ ከፍተኛ የጤና ጠቀሜታ አለው።

ለዊልቸር ተጠቃሚዎች ወይም ሌሎች የመንቀሳቀስ ውስንነት ላላቸው ደግሞ የተለዩ ልምምዶች ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ።

ለብዙዎቻችን መቀመጥ የማይቀር የዘመናዊ ሕይወት እና ሥራ አካል ሊመስለን ይችላል። ነገር ግን በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን መካከል መንጠራራት ወይም ሻይ ለመጠጣት መነሳት ከመቀመጥ ልማድ ለማላቀቅ ይረዳሉ።