ኢንዶኔዥያ 'ከ22 ዓመታት ትግል' በኋላ ለቤት ሠራተኞች ሕጋዊ እውቅና ሰጠች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የኢንዶኔዥያ ፓርላማ ከ20 ዓመታት በላይ የፈጀውን እና የቤት ሠራተኞችን መብት የሚያስጠበቅ ሕግ አወጣ።

አገሪቱ ወደ 4.2 ሚሊዮን የሚጠጉ የቤት ሠራተኞች ያላት ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ወደ 90 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። ቀደም ሲል በሕጋዊ መንገድ እንደ ሠራተኛ አይቆጠሩም ነበር።

በአዲሱ ሕግ መሠረት የጤና መድህን፣ የእረፍት ቀናት እና የጡረታ ክፍያ የማግኘት መብት ይኖራቸዋል። ኤጀንሲዎች የደመወዝ ቅነሳዎችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ የማይፈቀድላቸው ሲሆን ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆችን እንደ የቤት ሠራተኞች መቅጠርም ሕገወጥ ይሆናል።

አንዳንዶች ሕጉ መጽደቁን ሲሰሙ ሲያለቅሱ የታዩ ሲሆን አንድ ሠራተኛ "እዚህ ለመድረስ የ22 ዓመታት ትግል" መጨረሻ መሆኑን ተናግረዋል።

የቤት ውስጥ ሠራተኞች ጥበቃ ሕግ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበው እአአ በ2004 ቢሆንም በተደጋጋሚ እንቅፋቶችን አስተናግዷል። በረቂቁ ላይ የተደረጉ ውይይቶች ለዓመታት ተቋርጠው በ2020 በፓርላማ እንደገና መታየት ጀምረዋል።

ተቆጣጣሪዎች ዝርዝር የአፈጻጸም ፖሊሲዎችን ለማዘጋጀት አንድ ዓመት ይኖራቸዋል።

በኢኮኖሚው ውስጥ ወሳኝ ሚና ቢኖራቸውም በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኢንዶኔዥያ የቤት ሠራተኞች በሠራተኛ ሕጎች መሠረት ጥበቃ አልተደረገላቸውም።

ብዙዎቹ ያለ ምንም የሕግ ውል መደበኛ ባልሆነ መንገድ የሚቀጠሩ ናቸው። አንዳንዶቹ ለረዥም ሰዓታት በትንሽ ክፍያ የሚሠሩ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ከ12 ዓመታቸው ጀምሮ ወደ ሥራ ይገባሉ።

"እንደ ሕልም ሆኖ ይሰማኛል" ሲሉ የቤት ሠራተኛ የሆኑት አጄንግ አስቱቲ ለቢቢሲ ኢንዶኔዥያ ተናግረዋል። "ይህ ለተገለሉ ሴቶች ጥበቃ ለማግኘት የተደረገ የ22 ዓመታት ትግላችን ነው።"

ጁሚዬም የተባሉ የቤት ሠራተኛ በበኩላቸው "ይህንን [ሕግ] ናፍቀነዋል" ብለዋል።

አንዳንድ የመብት ተሟጋቾች ደግሞ ሕጉን አድንቀው፤ ነገር ግን "ትግሉ አላበቃም" ሲሉ አክለዋል።

የጃላ ፒአርቲ የመብት ተሟጋች አባል የሆኑት ሊታ አንግራኒ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት አሠሪዎችን ስለ ኃላፊነቶቻቸው ለማሳወቅ የትምህርት ዘመቻ ያስፈልጋል።

ቡድኑ ከ2021 እስከ 2024 ባሉት ዓመታት ውስጥ ከ3 ሺህ 300 በላይ የቤት ሠራተኞች ላይ ጥቃት ስለመፈጸማቸው ሪፖርት መደረጉን እና ከእነዚህም ውስጥ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃት እንደሚገኝበት አስታውቋል።