በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ባለው ጦርነት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምን ያህል ገቢ አጣ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በመካከለኛው ምሥራቅ አሜሪካ እና እስራኤል ቅዳሜ ዕለት በኢራን ላይ የከፈቱትን ጦርነት ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስር መዳረሻዎች የሚያደርጋቸውን በረራዎች መሰረዙን ለቢቢሲ ገለፀ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት በሳምንት እስከ 13.5 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ገቢ እንደሚያጣ ለቢቢሲ ተናግሯል።
የአየር መንገዱ የንግድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ለማ ያዴቻ ስድስተኛ ቀኑን በያዘው አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር የሚያደርጉት ጦርነት በአየር መንገዱ ላይ ትልቅ ጉዳት እንደሚያስከትል ተናግረዋል።
ኃላፊው ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ መጀመሪያ ላይ 135 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያጣ ከተናገሩ ከአንድ ቀን በኋላ፣ ቀድመው በተናገሩት አሃዝ ላይ ስህተት እንዳለ በመግለጽ ማስተካከያ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
በዚህም መሠረት አየር መንገዱ በስድስት ቀናት ውስጥ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ያደርጋቸው በነበሩ በረራዎች መሰረዝ ምክንያት ያጣው ገቢ 135 ሚሊዮን ዶላር ሳይሆን 13.5 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት መንገደኞችን እንዲሁም ጭነቶችን ያመላልሳል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ከመቀስቀሱ አስቀድሞ ወደ ዱባይ በቀን ሦስቴ በረራ የነበረው ሲሆን ወደ ሻርጃ ደግሞ አንዴ ይበር ነበር።
ወደ እስራኤል በቀን ሦስቴ፣ አቡዳቢ ደግሞ አንዴ በረራ የሚያደርገው አየር መንገዱ ወደ አማን በቀን ሁለቴ መንገደኞችን ያመላልሳል።
በዚህም የተነሳ "በአማካኝ በየዕለቱ 15 በረራዎችን እንሰርዛለን ማለት ነው" ሲሉ የድርጅቱ ኃላፊ ለቢበሲ ተናግረዋል።
ይህም ማለት ይላሉ ኃላፊው "በሳምንት የመንገደኞችን ብቻ ወደ 101 በላይ በረራዎችን እየሰረዝን ያለው።"
የጭነት ማመላለሻዎችን በተመለከተ ሲናገሩ ደግሞ በየቀኑ ወደ እያንዳንዱ መዳረሻ አንድ አንድ በረራዎች እንደሚኖር አስታውሰው የመንገደኞች እና የእቃ ጭነት በአንድ ላይ ተደምሮ "ወደ 160 በረራዎችን ለመሰረዝ እንገደዳለን ማለት ነው" ብለዋል።
አየር መንገዱ በቀጠናው ከፍተኛ ቁጥር ያለው መንገደኞችን እንደሚያመላልስ የጠቀሱት ኃላፊው "በሳምንት ከ45 እስከ 50 ሺህ መንገደኛ እናጓጉዛለን። እንግዲህ የእነዚህ መንገደኞች መቅረት በገቢ ደረጃ ትልቅ ጉዳት ያደርስብናል" ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ ለማ ያዴቻ በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰተው ጦርነት በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ አየር መንገዱ ከመንገደኞች ጉዞ "13.5 ሚሊዮን ዶላር ገደማ" በሳምንት እንደሚያጣ የተናገሩት ኃላፊው ከጭነት አገልግሎት ደግሞ "ወደ 2 ሚሊዮን ዶላር ልናጣ እንችላለን" ብለው አንደሚያስቡ ተናግረዋል።
በአማካኝ ከዚህ መስመር "ከ13 እስከ 13.7 ሚሊዮን ዶላር ልናጣ እንችላለን" ብለዋል።
አቶ ለማ አክለውም ይህ ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ያን ያህል ኪሳራ ያደርሳል ማለት አለመሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።
ይህንንም ሲያብራሩ በዚህ መስመር ላይ እየሰሩ የነበሩ አውሮፕላኖችን በጊዜያዊነት በሌሎች መስመሮች ላይ መድበው እያሰሩ መሆኑን ጠቅሰው ከዚህ መስመር የምናጣቸውን አብዛኞቹን ነገሮች ከሌላ መስመር ማግኘት እንችላለን ሲሉ ተናግረዋል።
በመካከለኛው ምሥራቅ በተቀሰቀሰው ጦርነት የትራንስፖርት ኢንዱስትሪው በጣም ይጎዳል የሚሉት ኃላፊው "መንገደኞችን እና እቃ እያጓጓዝን ነበር ገቢ የምናገኘው ያ በሚቀርበት ጊዜ የገቢ ጉዳት ያጋጥማል" ሲሉ ተጽዕኖውን ያብራራሉ።
በወጪም ደረጃ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ከፍተኛ የነዳጅ አምራች በመሆናቸው እና ቀጠናው ሰላም አለመሆኑ በነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳርፍ አስታውሰዋል።
ይህም የኢትዮጵያን ጨምሮ ማንኛውም አየር መንገድ የነዳጅ ዋጋ ከጨመረ ለከፍተኛ ወጪ ስለሚዳርገው ኢንዱስትሪውን ይጎዳዋል ሲሉ ግጭቱ ያለውን ተጽዕኖ አስረድተዋል።
ችግሩ በቶሎ ተፈትቶ ወደ ሥራ በቶሎ እንመለሳለን የሚል ተስፋ አለን ያሉት ኃላፊው፣ ያ እስኪሆን ድረስ ግን መስመሩ በመዘጋቱ የሚመጣውን ወጪው ለማካካስ አውሮፕላኖቹን ወደ ሌሎች መስመሮች በማሰማራት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
አሜሪካ እና የእስራኤል ከኢራን ጋር የሚያደርጉት ጦርነት በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን የአየር ጉዞ አስተጓጉሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እንዳይንቀሳቀሱ አድርጓል።
በቀጣዮቸ ቀናት በእነዚህ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ስለሚኖር የበረራ ሁኔታ እርግጠኛ ሆኖ መናገርም አይቻልም።
ኤኤፍፒ ያናገራቸው ባለሙያዎች በሚቀጥሉት ቀናትና ሳምንታት የሚደረጉ በረራዎች መስተጓጎላቸውን ሊቀጥሉ እንደሚችሉ አፅንዖት ያስረዳሉ።
በተለይም የባህረ ሰላጤው አገሮች የአጸፋ እርምጃ የሚወስዱ ከሆነ ጦርነቱ እየሰፋ እንደሚሄድ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ በረራዎች ላይ ተጽዕኖዎችን ያስከትላል።
የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት የአየር ክልላቸውን ዘግተው የሚቆዩ ከሆነ እና ጦርነቱ ካልቆመ ከባህረ ሰላጤው አገራት ወደ አውሮፓ፣ አፍሪካ እና እስያ የሚሄዱ ተጓዦች ተጨማሪ ተግዳሮቶች ይገጥማቸዋል።
____
በዚህ ዘገባ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመጀመሪያ ላይ ሰጥቶ የነበረውን የኪሳራ አሃዝ እንዲስተካከል በጠየቀው መሠረት ማስተካከያ ተደርጎበታል።















