ከአፍሪካ ዋንጫ ጋር በተያያዘ ሙስና ሳይፈጸም አልቀረም ሲል የሴኔጋል መንግስት ከሰሰ

ሴኔጋል የአፍሪካ ዋንጫን ስታነሳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

የ2025ቱን የአፍሪካ ዋንጫ ተነጥቃ ለሞሮኮ የተሰጠባት ሴኔጋል፤ ውሳኔው በአፍሪካ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል ላይ "የሙስና ጥርጣሬ" ስለሚያስነሳ "ገለልተኛ ዓለም አቀፍ ምርመራ" እንዲደረግ ጠየቀች።

ሴኔጋል ጥር ላይ በተደረገው የፍፃሜ ጨዋታ ሞሮኮን 1 ለምንም በማሸነፍ ነበር ዋንጫውን ያነሳችው። ይሁን እንጂ የሴኔጋል ተጫዋቾች ባለቀ ሰዓት ለአስተናጋጇ ሞሮኮ የተሰጠውን ፍጽም ቅጣት ምት በመቃወም ሜዳ ለቀው ወጥተው የነበረ በመሆኑ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ማክሰኞ ዕለት ውጤቱን ውድቅ አድርጓል።

ተጫዋቾቹ ከ17 ደቂቃ በኋላ ወደ ሜዳ ተመልሰዋል። የብራሂም ዲያዝ የ'ፓኔንካ' ፍጹም ቅጣት ምትን የሴኔጋሉ ግብ ጠባቂ ያዳነ ሲሆን የሴኔጋሉ ፓፔፕ ጉዬ በተጨማሪ ሰዓት ባስቆጠራት ጎል አገሩን አሸናፊ አድረጓል።

የሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሴኔጋልን አሸናፊነት በመቃወም ለካፍ ይግባኝ አቅርቧል። ጨዋታው እንዲሰረዝ የወሰነው ካፍ፤ የሴኔጋል ዋንጫ በመንጠቅ ሞሮኮን 3-0 በሆነ ውጤት ባለድል መሆኗን አስታውቋል።

ይህንን ተከትሎ የሴኔጋል መንግስት ባወጣው መግለጫ "ታይቶ የማይታወቀው ይህ እጅግ በጣም ከባድ ውሳኔ" የተላለፈው "በደንቦቹ የተሳሳተ ትርጓሜ ላይ በመመስረት" ነው ብሏል።

ይህ ሂደትም "ሕገወጥ እና እጅህ ኢ-ፍትሃዊ ውሳኔ አስከትሏል" ሲል ተቃውሞውን አሰምቷል። "ሴኔጋል ይህንን ፍትሃዊ ያልሆነ ውጤት መቀልበስ ሙከራ በግልፅ ትቃወማለች" ሲል አክሏል።

የሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ የካፍን ውሳኔ እንደሚቀበል አስታውቋል። ውሳኔው "ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ዘላቂነት ወሳኝ የሆኑ ደንቦች መከበር እንዳለባቸው ያረጋግጣል" በለማትም ድጋፉን ሰጥቷል።

"ይህ ውሳኔ ወደፊት ተመሳሳይ አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ ተፈጻሚ የሚሆነውን አካሄድ ከማሳየት ባለፈ የአፍሪካ እግር ኳስ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ወጥነት እና ተዓማኒነት እንዲኖረው አስተዋጽኦ ያደርጋል" ሲል አክሏል።

የካፍ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፓትሪስ ሞትሴፔ በበኩላቸው በፍጻሜው ጨዋታ ወቅት የተፈጠሩ ክስተቶች "የእግር ኳስ ግጥሚ ውጤቶች ሊኖራቸው የሚገባቸውን ታማኝነት፣ መከባበር፣ ሥነ ምግባር፣ አስተዳደር እና ተዓማኒነት" አበላሽተዋል ብለዋል።

"የካፍ የዲሲፕሊን ቦርድ እና የካፍ የይግባኝ ሰሚ ቦርድ ውሳኔዎች በአክብሮት እና በታማኝነት መታየታቸው አስፈላጊ ነው" ሲሉ አክለዋል።

"አፍሪካ ውስጥ አንድም አገር ከሌላው በበለጠ ወይም ባነሰ መልኩ አይስተናገድም።"

ትግሉ ገና አልተጠናቀቀም - የሴኔጋል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሴኔጋል እግር ኳስ ፌዴሬሽን የካፍን ውሳኔ በስፖርት የግልግል ፍርድ ቤት ይግባኝ እንደሚጠይቅበት ረቡዕ ዕለት አስታውቋል። "ኢ-ፍትሃዊ፣ ታይቶ የማይታወቅ እና ተቀባይነት የሌለው ውሳኔ ሲሆን የአፍሪካ እግር ኳስ ክብርንም የሚያጎድፍ ነው" ሲሉም ገልጸውታል።

"ይህ ውሳኔ በማንኛውም የሕግ የበላይነት ላይ ያልተመሠረተ ጥሰት ነው" ሲሉ ዋና ጸሐፊው አብዱላዬ ሴይዱ ሶው ለሴኔጋሉ አርቲኤስ 1 የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

"ግለሰቦቹ እዚያ ያሉት ሕጉን ለማስከበር ሳይሆን ትዕዛዝ ለመፈጸም እንደሆነ ተሰምቶን ነበር" ሲሉም ተደምጠዋል።

"ምንም ነገር አያቆምንም። ሕጉ ከጎናችን ነው። ትግሉ ገና አልተጠናቀቀም። ሴኔጋል መብቷን እስከመጨረሻው ታስጠብቃለች።"

ሞትሴፔ በበኩላቸው ካፍ የግልግል ፍርድ ቤቱ የሚወስደውን ውሳኔ "እንደሚከተል" እና "እንደሚያከብር" ተናግረዋል።

አንዳንድ የሴኔጋል ተጫዋቾች ሜዳሊያቸውን እንደማይመልሱ ጠቁመዋል።

የሴኔጋል እና የኤቨርተን አማካይ የሆነው ኢድሪሳ ጉያዬ፤ "በዚያ ምሽት ራባት ውስያጋጠመንን እናውቃለን። እናም ማንም ይህንን ከእኛ ሊነጥቀን አይችልም" ሲል በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ አስፍሯል።

የሴኔጋል ተጫዋቾች ከሜዳ መውጣት፤ የእግር ኳስ ሕግ አውጪ አካል የሆነው ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ማህበር ቦርድ (ኢፋብ)፤ "ተጫዋቾች ከሜዳ ለመውጣት ሲወስኑ ወይም የቡድን አባላቱ ይህ ዓይነቱን እርምጃ እንዲወሰድ ቢቀሰቅሱ" የሚፈጠሩ ሁኔታዎችን በተመለከተ ምክክር እንዲያካሂድ አድርጎታል።

የዕለቱ የመሃል ዳኛ ዣን ዣክ ንዳላ፤ ኢስማኤላ ሳር ያስቆጠረውን ጎል ከሻሩ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ለሞሮኮ ፍጹም ቅጣት መስጠታቸው ከሳዲዮ ማኔ ውጭ ሁሉም የሴኔጋል ተጫዋቾች ሜዳውን ለቅቀው እንዲወጡ አድርጓል።

የሴኔጋሉ ተከላካይ ኤል ሃጂ ማሊክ ዲዩፍ በሞሮኮው አጥቂ ዳያዝ ላይ በ98ኛው ደቂቃ ፈጽሟል የተባለውን ጥፋት፤ ንዳላ 'ቫር' ከተመለከቱ በኋላ የፍጹም ቅጣት ምቱን ሰጥተዋል።

የፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በበኩላቸው "በዚህ መንገድ ከሜዳ መውጣት ተቀባይነት የለውም" ድርጊቶቹ "መወገዝ እና ፈጽሞ መደገም የለባቸውም" ብለዋል።

በውድድሩ ወቅት በዳኝነት እና በቫር ውሳኔዎች ዙሪያ ብዙ ክርክሮች ከመደረጋቸውም በላይ አንዳንድ ጋዜጠኞች ሞሮኮ በአንዳንድ ዳኞች ድጋፍ እንደተደረገላት ጭምር ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ሴኔጋል ከፍጻሜው ጨዋታ በፊት ተጫዋቾቿ ራባት ሲደርሱ "ከፍተኛ የደኅንነት" ስጋት እንደነበራት አንስታ የነበረ ሲሆን ተጫዋቹ የተስተናገዱበትን መንገድ በተመለከተም ቅሬታ አቅርባ ነበር።

የአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ውዝግብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

'የጨዋታ አሸናፊነት በቦርድ ስብሰባ መገኘት የለበትም'

ካፍ ሞሮኮን የዋንጫ ባለቤት ባደረገበት ውሳኔው፣ በፍጻሜው ጨዋታየኳስ አቀባዮችን በተመለከተ በተፈጠረ ክስተት ዙሪያ የቀረበለትን ይግባኝ "በከፊል አጽድቆ" በሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ላይ የሰጠውን ቅጣት ቀንሷል።

በከባድ ዝናብ በተደረገው የፍጻሜ ጨዋታ የሴኔጋል ግብ ጠባቂ ኤዱዋርድ ሜንዲ ጓንቶቹን የሚያደርቅባቸውን ፎጣዎች ካስቀመጠበት ለመውሰድ በተደጋጋሚ ሲሞከር ታይቷል።

በአንድ አጋጣሚ የሴኔጋል ተጠባባቂ ግብ ጠባቂ የህቫን ዲዮፍ ጣልቃ ለመግባት በሚሞክረበት ወቅት በሦስት የኳስ አቀባዮች ተጠልፎ ከመውደቁም በላይ መሬት ላይ ሲጎተት ነበር።

በሌዘር መብራት ሜዳ ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች ፊት ላይ የሚያበሩ ደጋፊዎችን በተመለከተ የተሰጠውን ቅጣትም ካፍ ቀንሶታል።

የካፍ የቀድሞ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ኃላፊ ሬይመንድ ሃክ የአፍሪካ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል ባደረጋቸው ውሳኔዎች ላይ ጥያቄ አንስተዋል። "የሞሮኮ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት [ፎዚ ሌክጃ] የካፍ ቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት" በመሆናቸው "የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት አለ" የሚል ሃሳብ መኖሩን ጠቁመዋል።

"ሰርከሱ ቀጥሏል" ሲሉ ሃክ ለቢቢሲ ወርልድ ሰርቪስ ተናግረዋል።

"ብዙው ነገር የሚወሰነው በዳኛው የጽሑፍ ሪፖርት ላይ ነው። ነገር ግን ዳኛው ጨዋታው እንዲቀጥል መፍቀዳቸው እና ተጨማሪ ደቂቃዎችን ጨምረው ጨዋታው እንደሚቀጥል ማድረጋቸው በሂደቱ እንደተደሰቱ ያስረዳል።"

"ጨዋታውን ሊያቆም የሚችለው እሱ ብቻ ነው። ባለስልጣናት፣ የአስተዳደር አካላት ሳይሆን ዳኛው ብቻ ሊያስቆም የሚችለው።

"አለበለዚያ ግን የትኛውም ወገን በውሳኔ በማይስማማበት ወቅት ሁሉ ይግባኝ ለማለት ወይም ወደ ፍርድ ቤት የሚሄዱበት አይነት አስቂኝ ነገር በዓለም ዙሪያ ያጋጥማል።"

"የጨዋታው ውጤት መታወቅ ያለበት በቦርድ ውሳኔ ሳይሆን በጨዋታ ሜዳ ላይ ነው።"

ጠበቃ እና የፊፋ የዲሲፕሊን ኮሚቴ አባል የሆኑት ሃክ አክለውም የሞሮኮ ተጫዋቾች ውጤቱን ለመቃወም ካሰቡ በተቃውሞ ውስጥ ሆነው እየተጫወቱ መሆኑን ለዳኛው ማሳወቅ ነበረባቸው ብለዋል።

የግልግል ፍርድ ቤቱ በሴኔጋል ይግባኝ ዙሪያ ውሳኔ ለመስጠት ስድስት ወራት ሊፈጅበት እንደሚችልም ተናግረዋል።

የሞሮኮው ጋዜጠኛ ጃላል ቦናር ለኒውስዴይ እንደተናገሩት የካፍ ውሳኔ "በመላ አገሪቱ በከፍተኛ ደስታ" ተቀባይነት አግኝቷል።

"ሞሮኮ ውሳኔውን ለአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ይግባኝ ያለችው በጨዋታው ወቅት ሴኔጋል ህጎቹን ጥሳለች ብለው ስላመኑ ነው፣ ለዚህም ነው ሞሮኮዎች ደስታቸውን ለመግለጽ የወጡት" ብለዋል።

"[ዋንጫውን] ለሴኔጋል ከሰጡት የዓለም ፍጻሜ አይሆንም። ፍጻሜ በመድረሳችንም ረክተን እንቀበላለን።"

የሰሜን አፍሪካው ጋዜጠኛ ማሄር ሜዛሂ ግን እንዲህ ዓይነቱ ስሜት በመላው አህጉሪቱ እንዳልተፈጠ ተናግረዋል።

"የተቀረው አፍሪካ በዚህ የተበሳጨ ይመስላል ምክንያቱም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ስፖርቱን ሊያዋርደው ተቃርቧል" ሲሉ ለቢቢሲ ሬዲዮ 5 ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት ከሜዳ ለቅቆ መውጣት ያጋጠመባቸው ክስተቶች

የሴኔጋል ተጫዋቾች ከሜዳ በመውጣታቸው የተሰጠው ቅጣት ታይቶ የማይታወቅ ቢሆንም፣ ተጫዋቾች ከሜዳ ሲወጡ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ አልነበረም።

ቼኮዝሎቫኪያ ከቤልጂየም (1920)

በ1920 አንትወርፕ ኦሊምፒክ ላይ ለወርቅ ሜዳሊያ ከቤልጂየም ጋር ባደረጉት ጨዋታ እንግሊዛዊው ዳኛ ጆን ሉዊስ ለአስተናጋጆቹ የፍጹም ቅጣት ምት ሰጥተው የቼኮዝሎቫኪያን የግራ ተከላካይ ካረል ስቴይነርን በቀይ በማስወጣታቸው የቼኮዝሎቫኪያ ተጫዋቾች ሜዳ ለቀው ወጠዋል።

ቤልጂየም የወርቅ ሜዳሊያ ሲሰጣት ቼኮዝሎቫኪያ ደግሞ ከውድድሩ ሙሉ በሙሉ ተባራለች።

ሊል ከ ማንቸስተር ዩናይትድ (2007)

ማንቸስተር ዩናይትድ ያገኘውን የቅጣት ምት የሊል ተጫዋቾች የመከላከል ግድግዳቸውን አስተካክለው ሳይጨርሱ ራያን ጊግስ ኳሳን መትቶ በማስቆጠሩ የፈረንሳዩ ቡድን ተጫዋቾች የቻምፒየንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታን እንዲያቋርጡ ምክንያት ሆኗል።

ተሰብስበው ከመከሩ በኋላም ጨዋታውን ለማጠናቀቅ ተመልሰዋል።

ኤሲ ሚላን ከፕሮ ፓትሪያ (2013)

የኤሲ ሚላኑ አማካይ ኬቨን-ፕሪንስ ቦአቴንግ ከፕሮ ፓትሪያ ጋር በተደረገው የወዳጅነት ጨዋታ በተመልካቾች የዘር ጥቃት ከተፈጸመበት በኋላ የቡድን አጋሮቹን ከሜዳ አስወጥቷቸዋል።

ፊፋ የቦአቴንግን መርሆዎች አድንቆ የዘር መድልዎ ግብረ ኃይሉ የመጀመሪያ አባል አድርጎታል። ነገር ግን ከሜዳ ለመልቀቅ ያደረገውን ውሳኔ እንደማይደግፍ ተናግሯል።

ፒኤስጂ ከኢስታንቡል ባሳክሼር (2020)

አራተኛው ዳኛ ሴባስቲያን ኮልቴስኩ በኢስታንቡል ባሳክሼር ረዳት አሰልጣኝ ፒየር ዌቦ ላይ የዘረኝነት ቃል እንደተጠቀሙ መነገሩን ተከትሎ ከሁለቱም ቡድኖች የተውጣጡ ተጫዋቾች የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታውን አቋርጠው ሜዳውን ለቀው ወጥተዋል።

የባሳክሼር ተጫዋቾች ለመመለስ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ጨዋታው በማግስቱ እንደገና ተደግሟል። ኮልቴስኩ እስከ ውድድሩ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ታግደው የቆዩ ሲሆን ስልጠና እንዲወስዱም ተደርገዋል።

ፌነርባቼ ከጋላታሳራይ (2024)

ፌነርባቼ ከ19 ዓመት በታች ቡድኑን በማሰለፍ ከተቀናቃኙ ጋላታሳራይ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ለአንድ ደቂቃ ሜዳ ላይ ቆይተው ጨዋታው አቋርጠዋል። ይህንን ያደረጉት ከአራት ቀናት በኋላ በአውሮፓ ሊግ ሩብ ፍጻሜ ከኦሎምፒያኮስ ጋር ላለባቸው ፍልሚያ የአገር ውስጥ ጨዋታው እንዲራዘም ጥያቄ አቅርበው ጥያቄያቸው ውድቅ ከተደረገ በኋላ ነው።

ፌነርባቼ 115 ሲቀጣ፤ ጋላታሳራይ 3 ለምንም እንዲያሸንፍ ተደርጓል።

ኮሎምቤ ስፖርትቭ ዱ ሱድ ከፓንቴሬ ዱ ንዴ (2026)

በየካቲት ወር በካሜሩን ሱፐር ካፕ ከፓንቴሬ ዱ ንዴ ጋር በነበረው ጨዋታ በ69ኛው ደቂቃ አምበሉ ራንዲ ንቱሜ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተባሮ ፍጹም ቅጣት ምት የተሰጠበትን አወዛጋቢ ውሳኔ ተከትሎ ኮሎምቤ ስፖርትቭ ዱ ሱድ ተጫዋቾእ ሜዳ ለቀው ወጠዋል።

ጨዋታው የተሰረዘ ሲሆን የመጨረሻው ውጤት በካሜሩን የእግር ኳስ ፌደሬሽን በኩል እንደሚሰጥበት ይጠበቃል።