የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ አዛዥ ከ 20 ሚሊዮን ዶላር የኮንትራት ስምምነት ጋር በተያየዘ ታገዱ
የፎቶው ባለመብት, Gallo Images via Getty Images
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ማክሰኞ ዕለት በፍርድ ቤት ክስ የቀረበባቸውን የአገሪቱን ፖሊስ አዛዥ ላይ "ጊዜያዊ እገዳ" እንደጣሉባቸው ተገለጸ።
የ62 ዓመቱ ጄኔራል ፋኒ ማሴሞላ አወዛጋቢ የሆነውን 21 ሚሊዮን ዶላር የኮንትራት ውል ከመስጠት ጋር በተያያዘ ኃላፊነታቸውን በሚገባ እንዳልተወጡ ተዘግቧል።
የኮንትራት ስምምነቱ የወንጀል ምርመራ እየተደረገበት ሲሆን መሰረዙም ታውቋል።
የፖሊስ አዛዡ የደቡብ አፍሪካን የመንግሥት ፋይናንስ አስተዳደር ሕግ በከፊል በመጣስ ተከስሰዋል።
ሕጉ የግብር ከፋዮች ገንዘብ እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውል የሚደነግግ ነው።
ማሴሞላ ሐሙስ ዕለት በነበረው የፍርድ ቤት ውሎ የቀረበባቸውን ክስ ክደው የተከራከሩ ሲሆን ለጋዜጠኞችም "ጥፋተኛ አለመሆኔን አውቃለሁ፤ ስህተት አልሠራሁም፤ ነገር ግን ሕጉ የራሱን ሂደት መሄድ አለበት" ብለዋል።
ማሴሞላ በሥልጣን ላይ እያሉ የወንጀል ምርመራ የተካሄደባቸው ሦስተኛው የደቡብ አፍሪካ የፖሊስ አዛዥ ናቸው።
ራማፎሳ የፖሊስ አዛዡን ለማገድ የወሰኑት "የክሶቹን ክብደት እና የፖሊስ ብሔራዊ ኮሚሽነር በወንጀል ላይ በሚደረገው ትግል ውስጥ በሚጫወተው ወሳኝ ሚና" ምክንያት ነው።
ማሴሞላ የፍርድ ቤቱ ጉዳይ እስኪጠናቀቅ ድረስ ይታገዳል ሲሉም ተናግረዋል።
በፖሊስ አባላት የሚፈጸም ሙስናን ለማስወገድ እርምጃ እንዲወስዱ ከሚጠይቁ ወገኖች እየጨመረ በመጣው ጫና ውስጥ የቆዩት ራማፎሳ የሕግ አስከባሪ ተቋማት "ብቃት ያላቸው፣ ሥነ ምግባራቸውን የጠበቁ እና ውጤታማ" መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል።
አክለውም የደቡብ አፍሪካ ሕዝብ እምነት እንደሚጥልባቸውም ገልጸዋል።
የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፕሬዝዳንቱ ይህንን የገለጹት በዋና ከተማዋ ፕሪቶሪያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ማሴሞላን የተኩት ሌተናንት ጄኔራል ፑሌንግ ዲምፓኔ ከጎናቸው ቆመው ባሉበት ወቅት ነው።
ግለሰቧ እአአ ከ2018 ጀምሮ የፖሊስ አገልግሎት ዋና የፋይናንስ ኃላፊ ሆነው የሠሩ ሲሆን ለ20 ዓመታት ያህል በሥልጣን ላይ ቆይተዋል።
ነገር ግን ሙስና በተፈፀመበት ወቅት የፖሊስን የፋይናንስ አስተዳደር በበላይነት ይቆጣጣሩ ስለነበር ሹመታቸው ጥያቄ ተነስቶበታል። ከዚህ በፊት በሙስና ውስጥ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንደሌላቸው በመግለጽ የሚቀርብባቸውን ውንጀላ አስተባብለዋል።
ማሴሞላ የተከሰሱት 21.7 ሚሊዮን ዶላር በሚያወጣ ከፖሊስ የጤና አገልግሎት ጨረታ ጋር በተያያዘ የመንግሥት ንብረት ግዢ ሕግን ሆን ብሎ ችላ በማለት ነው።
ጨረታው የተሰጠው ቩሲሙዚ 'ካት" ማትላላ በመባል ለሚታወቁ ነጋዴ ባለቤትነት በተያዘ ሜዲኬር24 ለተባለ ድርጅት ሲሆን ግለሰቡ በተደራጀ ወንጀል ውስጥ እጃቸው አለበት በሚል ይወነጀላሉ።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በርካታ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖች በኮንትራቱ አሰጣጥ ውስጥ ባላቸው ሚና ክስ ተመስርቶባቸዋል።
አቃቤ ሕጎች ሜዲኬር24 ከፖሊስ ባለሥልጣናት ጋር በመመሳጠር ጨረታውን እንዲያሸንፍ እና ለአባላቱ የጤና አገልሎት እንዲሰጥ ተደርጓል ሲሉ ይወነጅሉታል።
ማትላላ ኮንትራቱ ከመሰረዙ በፊ 3.03 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ተቀብሏል።
ከነጋዴው ጋር በመተባበር የተከሰሱት የፖሊስ ባለሥልጣናት እንዲሁም ነጋዴው በሙስና ተወንጅለዋል። አንዳቸውም በግን ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ አልተደረጉም።
ማሴሞላም እንዲሁ በሙስና የክስ መዝገብ አልተከፈተባቸውም። የመንግሥትን የፋይናንስ ሕግ በመጣስ ግን አራት ክሶች ቀርቦባቸዋል።
በመስከረም ወር ራማፎሳ በፖሊስ ውስጥ ያለውን ሙስና ለመመርመር ኮሚሽን ካቋቋሙ በኋላ በተካሄደ ምርመራ ለጤና ስራ በወጣ የኮንትራት ጨረታ ላይ የተፈጠሙ የፋይናንስ ስህተቶችን በሚመለከት ክስ ተመስርቷል።
እንዳያመልጥዎ
ከየፈርጁ
በስፋት የተነበቡ
የሚፈልጉት ይዘት የለም