ኢራን የበለጸገ የዩራኒየም ክምችት አላት? የኒውክሌር ጦር መሣሪያ መገንባት ትችላለች?
የፎቶው ባለመብት, Getty Images/BBC
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቴህራን ጦርነቱን ለማቆም በተደረገው ስምምነት የዩራኒየም ክምችቷን ለማስረከብ መስማማቷን ከተናገሩ በኋላ የኢራን የበለፀገ ዩራኒየም ክምችት ትኩረትን ስቧል።
ይሁን እንጂ ሰኞ ዕለት የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳኢድ ካቲብዛዴህ ይህንን አባባል ውድቅ አድርገው ለኤፒ የዜና ወኪል እንዲህ ዓይነቱ ሀሳብ "የማይታሰብ" እንደሆነ ተናግረዋል።
ሁለቱ ወገኖች ለተጨማሪ የሰላም ድርድር እየተዘጋጁ ባለበት ወቅት፣ የዚህ ክምችት የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለውይይት ቁልፍ ርዕስ እንደሚሆን እርግጠኛ መሆን ይቻላል።
ግን በትክክል የበለፀገ ዩራኒየም ምንድን ነው? ለምንስ በጣም አስፈላጊ ሆነ?
የበለጸገ ዩራኒየም ምንድን ነው?
ዩራኒየም በመሬት ውስጥ የሚገኝ በተፈጥሮ የሚገኝ ማዕድን ነው።
በአብዛኛው ዩ-238 እና ዩ-235 ከተባሉ ከሁለት አይዞቶፖች የተሰራ ነው።
ከ99 በመቶ በላይ የሚሆነው የተፈጥሮ ዩራኒየም ዩ-238 ሲሆን በቀላሉ ኃይል መፍጠር አይችልም። ዩ-235 በቀላሉ ሊከፋፈል የሚችል እና የኒውክክሌር ፊሽን (nuclear fission) በመባል በሚታወቀው ሂደት ውስጥ ኃይልን የሚለቅ አይሶቶፕ 0.7 በመቶ ብቻ ነው።
ዩራኒየም ጠቃሚ እንዲሆን፣ የዩ-235 መጠን ማበልጸግ በሚባል ሂደት መጨመር አለበት።
በመጀመሪያ ዩራኒየም ወደ ጋዝ ይቀየራል። ይህ ጋዝ እጅግ በጣም በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ሚሽከረከሩ ማሽኖች እንዲገባ ይደረጋል።
ሲሽከረከሩ፣ ክብደቱ የሚጨምረው ዩ-238 በትንሹ ወደ ላይ ከፍ እያለ ይሄዳል፤ ቀላል የሆነው ዩ-235 ደግሞ ለመካከሉ ቅርብ ሆኖ ይቀመጣል።
ይህም ዩ-235 ብርቅዬ እና ጠቃሚ የሆነው የዩራኒየም ዓይነት እንዲሁም እና ቀስ በቀስ ከተለመደው ዩ-238 እንዲለይ ያስችለዋል።
ይህ የበለጠ እንዲብላላ የተደረገ ዩራኒየም የሚወጣው በማብላያው አንድ ጫፍ በኩል ነው።
በኒውክሌር ኃይል ማመንጫዎች እና በጦር መሳሪያዎች ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውለው ዩራኒየም መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?
የተለያዩ የማበልጸግ ደረጃዎችን የሚያልፍ ዩራኒየም ለተለያዩ ጥቅሞች ተስማሚ ይሆናል።
በዝቅተኛ ደረጃ የበለፀገ ዩራኒየም፣ በተለምዶ ከ3-5 በመቶ ዩ-235 የያዘ፣ በንግድ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫዎች ውስጥ እንደ ነዳጅ ያገለግላል። ይህ ቁጥጥር የሚደረግበት ኃይል ለማመንጨት በቂ ነው፣ ነገር ግን ለጦር መሣሪያ ከሚያስፈልገው ደረጃ በጣም ያነሰ ነው።
በከፍተኛ ደረጃ የበለፀገ ዩራኒየም፣ 20 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ መጠን ያለው ሲሆን በምርምር ማዕከሎች ውስጥ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል።
የጦር መሣሪያ ለማምረት የሚያስችለው ዩራኒየም ብዙውን ጊዜ ወደ 90 በመቶ አካባቢ የበለፀገ ነው።
በዚያ ደረጃ የተብላላ ዩራኒየም በቀላሉ የኒውክሌር ምላሽ ፍንዳታዎችን ለማድረስ ተስማሚ ነው። በቂ የሆነ የተብላላ ዩራኒየም ሲሰባሰብ፣ አቶሞች በጣም በፍጥነት መከፋፈል ይጀምራሉ፤ በሰከንድ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ኃይል ይለቃሉ።
ይህ ነው ዩራኒየምን ለሰላማዊ አገልግሎት እና ለወታደራዊ አገልግሎት በመዋል መካከል የሚኖረው ልዩነት።
በማብላያው ውስጥ ለነዳጅ የሚሆነው በትንሹ የበለጸገ ሲሆን መብላላቱም ሆን ተብሎ ዝግ እንዲል እንዲሁም በጥንቃቄ ቁጥጥር ይደረግበታል። ይህም ኃይሉን ለወራት ወይም ለዓመታት ቀስ በቀስ እንዲለቀቅ ያስችለዋል። ቦምብ ለመስራት ግን የሚደረገው ከዚህ በተቃራኒው ነው፤ የመብላላት ፍጥነቱን በፍጥነት እና በአንድ ጊዜ አንዲሆን ይደረጋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2015 ከስድስት የዓለም ኃያላን መንግሥታት ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ሩሲያ፣ አሜሪካ እና ዩኬ ጋር በተደረገ ስምምነት መሠረት ኢራን ያላትን ዩራኒየም ከ3.67 በመቶ ባልበለጠ ሁኔታ እንድታበለጽግ ገደብ ተቀምጦ ነበር።
በዚህ ስምምነት መሠረት የሚኖራት ክምችትም ከ300 ኪሎ ግራም እንዳይበልጥ ተወስኗል። የማብላያዎቿን ቁጥር የወሰነው ይህ ስምምነት በተራሮች ውስጥ ባለው ፎርዶ የኒውክሌር ተቋም እንዳታበለጽግ ይከለክላል።
ይሁን እንጂ እአአ በግንቦት ወር 2018 ዶናልድ ትራምፕ በመጀመርያው የሥልጣን ዘመናቸው አሜሪካ ከሥምምነቱ እንድትወጣ አድርገዋል።
የማበልጸግ ደረጃው ለምን ይጠቅማል?
ከፍ ባለ ደረጃ የበለጸገ ዩራኒየም የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ለማምረት ሊያገለግል ይችላል።
20 በመቶ የበለጸገ ዩራኒየም ወሳኝ የሚባለው ምዕራፍ ላይ ደርሷል ማለት ነው። ምክንያቱም የጦር መሣሪያ ለማምረት የሚያስፈልገው አብዛኛው መሠረታዊ ነገር እስከዚያ ጊዜ ድረስ ይሟላል።
ተፈጥሯዊ ዩራኒየምን ወደ 20 በመቶ ለማበልጸግ በሺዎች የሚቆጠሩ ተደጋጋሚ ደረጃዎችን እና ብዙ ጊዜ እና ኃይል ይጠይቃል።
በንጽጽር ዩራኒየምን ከ20 ወደ 90 በመቶ አካባቢ፤ ማበልጸግ በጣም ጥቂት ተጨማሪ እርምጃዎችን ብቻ ይወስዳል።
ይህ ማለት በከፍተኛ ደረጃ የበለፀገው ዩራኒየም በአንጻራዊ ሁኔታ በፍጥነት ጦር መሳሪያ ለማምረት ወደሚያስችል ደረጃ ሊለወጥ ይችላል ማለት ነው።
ኢራን ምን ያህል የዩራኒየም ክምችት አላት?
አሁኑ ባለው ድርድር ውስጥ ዋነኛው መነጋገሪያ የኢራን የበለፀገ የዩራኒየም ክምችት ምን መሆን አለበት የሚለው ነው።
ጦርነቱ ሲጀመር ኢራን 440 ኪሎ ግራም ዩራኒየም እንዳላት እና ይህም 60 በመቶ የበለጸገ መሆኑን አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ተናግረው ነበር።
ይህም ጦር መሣሪያ ለማምረት ወደሚያስችለው 90 በመቶ የበለጸገ ዩራኒየም በአንፃራዊነት በፍጥነት ሊያድግ ይችላል።
ኢራን በተጨማሪም 20 በመቶ ድረስ የበለጸገ 1,000 ኪሎ ግራም፣ እንዲሁም 3.6 በመቶ ገደማ የበለጸገ 8,500 ኪሎ ግራም ዩራኒየም አላት።
ይህም በተለምዶ ለሰላማዊ አገልግሎት ማለትም ለኃይል ማመንጨት ወይም ለሕክምና ምርምር ይውላል።
ወደ ኒውክሌር ጦር መሣሪያነት ሊቀየር የሚችለው በከፍተኛ ደረጃ የበለፀገ ዩራኒየም በአብዛኛው በኢስፋሃን እንደተከማቸ ይታመናል። ተቋሙ ባለፈው ዓመት በአሜሪካ እና በእስራኤል የአየር ድብደባ ዒላማ ከተደረጉት የኢራን ሦስት የመሬት ውስጥ የኒውክሌር ጣቢያዎች አንዱ ነው።
ይሁን እንጂ በከፍተኛ ደረጃ ከበለፀገው ዩራኒየም ምን ያህል በሌሎች ቦታዎች እንደተከማቸ ግልጽ አይደለም።
ምንጮች እንደሚሉት ቴህራን ለ20 ዓመት ኒውክሌር እንዳታበለጽግ የተቀመጠውን እገዳ ውድቅ አድርጋለች። በምትኩ ጦርነቱ ከመፈንዳቱ በፊት ያቀረበችውን የአምስት ዓመት ገደብ ለድርድር አቅርባለች።
በተጨማሪም 440 ኪሎ ግራም የበለፀገውን የዩራኒየም ክምችት እንድታስረክብ የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አድርጋለች።
ይህም ቀደም ሲል 60 በመቶ የበለፀገውን ዩራኒየሟን ለማዳከም በሚለው አቀወማ ጸንታለች።
የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ኃላፊ ራፋኤል ግሮስ ባለፈው ዓመት በጥቅምት ወር ለኤፒ እንደተናገሩት ይህ መጠን የበለጠ ቢበለጽግ 10 የኒውክሌር ቦምቦች ለማምረት በቂ ይሆናል።
ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እያመረተች ነው?
ኢራን የኒውክሌር ማዕከሎቿ ሙሉ በሙሉ ለሰላማዊ አገልግሎት የሚውሉ መሆናቸውን አጥብቃ ትከራከራለች። የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኤነርጂ ኤጀንሲ በበኩሉ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ፕሮግራም መኖሩን የሚያሳይ ማስረጃ አላየሁም ብሏል።
የጦር መሣሪያ ለመስራት የሚያስችል ዩራኒየም ማምረት የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመገንባት አንድ እርምጃ ብቻ ነው።
ቦምቡን ለማምረት ንድፉን መስራት እና ተተኳሽ አረሩን መገጣጠም እንዲሁም ወደሚፈለግበት ስፍራ ለማድረስ የሚያስፈልጉ ውስብስብ ስርዓቶችን ማለፍ ይጠይቃል።
"ኢራን ፕሮግራሙን እስክታቆም እስከ 2003 ድረስ የተተኳሽ አረር ንድፍ ላይ የተወሰነ አቅም አዳብራ ነበር" ትላለች ገለልተኛ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ባለሙያ የሆነችው ፓትሪሺያ ሌዊስ።
ይሁን እንጂ "የ2015ቱ የኒውክሌር ስምምነት ከፈረሰ እና አዲስ ስምምነት ለማድረግ የተደረጉት ውይይቶች ከከሸፉ በኋላ ኢራን የመሣሪያውን አረር አቅምን እንደገና ለማዳበር ወስና ይሆናል" በማለት አክላለች።
እንደ አውሮፓውያኑ በግንቦት 2025 የአሜሪካ የመከላከያ መረጃ ኤጀንሲ ባደረገው ግምገማ ኢራን "ምናልባት ከአንድ ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ" አንድ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ መስራት የሚያስችላት ዩራኒየም ማምረት ትችላለች ብሏል።
ኢራን ምንም ለማምረት የሚያስችሏትን እርምጃዎች ብትወስድም ኢራን "በእርግጥ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ አታመርትም" ሲል አስታውቋል።
እስራኤል ግን ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያን ለማምረት የሚያስችል "ተጨባጭ እድገት" እንዳሳየች የሚጠቁም መረጃ እንዳላት ትገልጻለች።
እንዳያመልጥዎ
ከየፈርጁ
በስፋት የተነበቡ
የሚፈልጉት ይዘት የለም