ሜታ ለኤአይ ከፍተኛ ገንዘብ በመመደቡ ከ8000 በላይ ሠራተኞችን ሊያሰናብት ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ሜታ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ የሚያወጣውን ወጪ በከፍተኛ መጠን በመጨመሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን ሊያሰናብት መሆኑን አስታወቀ።

ኩባንያው ሐሙስ ዕለት ለሠራተኞቹ በላከው የውስጥ ማስታወሻ ላይ የሠው ኃይሉን በ10 በመቶ ለመቀነስ ማቀዱን አስታውቋል።

በዚህም 8000 ያህል ሠራተኞች ሥራቸውን ሊያጡ ይችላሉ ተብሏል።

ኩባንያው በሺህዎች የሚቆጠሩ አዲስ ቅጥሮችንም ላለማከናወን መወሰኑን ይፋ አድርጓል።

ሜታ ሠራተኞቹን ለመቀነስ የወሰነበት ቁልፍ ምክንያት ሰው ሰሠራሽ አስተውሎትን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች ላይ የሚያወጣውን ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ እንደሆነ ተገልጿል።

ሜታ በዚህ ዓመት ብቻ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ135 ቢሊዮን ዶላር መመደቡን አስታውቋል።

ይህ ገንዘብ ኩባንያው ለሰው ሠራሽ አስተውሎት ብቻ ባለፉት ሦስት ዓመታት ያወጣውን እንደሚስተካከል የውስጥ ማስታወሻውን የተመለከተ ግለሰብ ተናግሯል።

የሜታ ቃል አቀባይ ኩባንያው ሥራዎችን ለማቋረጥ መወሰኑን አረጋግጠው ተጨማሪ አስተያየት ግን ከመስጠት ተቆጥበዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከሜታ መስራቾች መካከል አንዱ የሆነው እና የበላይ ሃላፊው ማርክ ዙከርበርግ በጥር ወር በዚህ ዓመት በርካታ ሠራተኞችን እንደሚቀንስ ተናግሮ ነበር።

የሜታ ሃላፊ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚደገፉ ሠራተኞች ምን ያህል ውጤታማ መሆናቸውን ማስተዋሉን ጠቅሶ ከዚህ በፊት በርካታ የሰው ኃይል ይጠይቁ የነበሩ ፕሮጀክቶች አሁን በአንድ ሰው እንደሚከናወን አብራርቷል።

"እንደሚመሰለኝ በ2026 የሰው ሠራሽ አስውሎት በአስገራሚ ሁኔታ ሰዎች የሚሰሩበትን መንገድ የሚቀይርበት ዓመት ይሆናል" ሲል ዙከርበርግ ተናግሯል።

ባለፈው ሳምንት ሮይተርስ የዜና ወኪል ሜታ በዚህ ዓመት ብቻ 1000 ሠራተኞችን ለመቀነስ ማቀዱን ዘግቦ ነበር።

ሐሙስ ዕለት ሠራተኞች የተመለከቱት የውሰጥ ማስታወሻ መጀመርያ የተዘገበው በብሉምበርግ ነው።

ሜታ ባለፉት አራት ወራት ብቻ 2000 ሠራተኞችን ያሰናበተ ሲሆን የድርጅቱ ሠራተኞች ተጨማሪ ቅነሳ እንደሚኖር እየጠበቁ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከቅርብ ወራት ወዲህ ሜታ ወጪዎቹ እና ውሰጣዊ ትኩረቱ የተቀየረው ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ሞዴሎች እና መሣሪያዎች ዕድገት ጋር ራሱን ለማስተካከል በሚያደርገው ጥረት መሆኑ ተገልጿል።

ኩባንያው በዚህ ሳምንት ሠራተኞቹ ከኮምፒውተራቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት መከታተል እንደሚጀመር እና ይህም የሰው ሠራሽ ሞዴሎችን ለማሰልጠን እና ለማሻሻል መሆኑን የገለጸ ሲሆን ሠራተኞቹ ግን እርምጃውን "ጨቋኝ" ሲሉ ገልጸውታል።

"ይህ ኩባንያ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ፍቅር ወድቋል" ሲሉ አንድ የድርጅቱ ሠራተኛ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እአአ ከ2022 ጀምሮ ሜታ በርካታ የሠራተኞች ቅነሳ በማድረግ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን አሰናብቷል።

ነገር ግን ዳግም መቅጠር ጀምሮ የነበረ ሲሆን ባለፈው ዓመት የሠራተኞቹ ቁጥር ማሰናበት ከመጀመሩ በፊት የነበረበት ቁጥር ላይ ደርሶ ነበር።

አሁን የሚያደርገው የሠራተኞች ቅነሳ ከ2023 ጀምሮ ካካሄደው ሁሉ ግዙፉ መሆኑ ተገልጿል።

ሌሎች የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችም አብዛኛዎቹ ለኤአይ ቴክኖሎጂ ግንባታ መሣሪያዎች እና መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣታቸው በርካታ ሠራተኞቻቸውን ቀንሰዋል።

አማዞን ከ30,000 በላይ ሠራተኞችን ሲያሰናብት ኦራክል ደግሞ ከ10,000 በላይ የሚሆኑትን መቀነሱን አስታውቋል።