በኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ መኪኖች ላይ የታየው 'የተጋነነ' የዋጋ መናር ከኢራን ጦርነት ጋር ይገናኛል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

አሜሪካ እና እስራኤል በጥምረት ኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት በዋነኛነት ዓለም አቀፍ የነዳጅ እና የማዳበሪያ አቅርቦትን አስተጓጉሏል።

ኢራን የዓለም ዋነኛ የነዳጅ እና ጋዝ መተላለፊያ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥ መዝጋቷን ተከትሎ የተለያዩ ሸቀጦች አቅርቦት መቀነስ እንዲሁም የዋጋ ንረት ተከስቷል።

በኢትዮጵያ የተፈጠረውን የነዳጅ እጥረት ተከትሎም የአንዳንድ መንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች የዓመት እረፍት እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሠራተኞች ገልጸዋል።

የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ መተላለፊያ የሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ የተከሰተው የነዳጅ እጥረት በኢትዮጵያ ዋና ዋና ከተሞች የትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ጫና ማሳደሩን ቢቢሲ ከነዋሪዎች እና ከአሽከርካሪዎች ተረድቷል።

ማኅበረሰቡ እና ተቋማት ነዳጅን "በከፍተኛ ቁጠባ" እንዲጠቀሙ ከወጣው ማሳሰቢያ በተጨማሪ ነዳጅ ለፀጥታ ተቋማት እና ለሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች በቅድሚያ እንዲሰጥ ትዕዛዝ ተላልፏል።

ከሰሞኑ ደግሞ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ መኪና ዋጋ እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር ድረስ መጨመሩ ተሰምቷል። ይህ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ከኢራን ጦርነት ጋር ይያያዝ እንደሆነ ቢቢሲ ከዘርፉ ባለሙያዎች ጠይቋል።

የኤሌክትሪክ መኪና ዋጋ ለምን ጨመረ?

የአውቶሞቲቭ ጉዳዮች ተንታኝ አቶ ብሩክ አወቀ እንደሚሉት፤ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ የታየው ከጦርነቱ ቀደም ብሎ ነው።

ከሁለት ወር ቀደም ብሎ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ከጦርነቱ ወዲህ ደግሞ እንደተባባሰ ይናገራሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ከትንንሽ መኪኖች ብንነሳ ከ400 ሺህ ብር ጀምሮ እስከ 1 ሚሊዮን ብር ዋጋቸው የጨመረ አሉ። ለጭማሪው ዋነኛ ምክንያት የማጓጓዣ (Shipping) ዋጋ መጨመሩ ነው" ብለዋል።

በጦርነቱ ምክንያት በተፈጠረው የባሕር ላይ እንቅስቃሴ መስተጓጎል ምክንያት በመርከብ በአንድ ኮንቴነር ከ2500 እስከ 4000 ዶላር ጭማሪ እንዳለ አቶ ብሩክ ጠቅሰዋል።

ጭማሪው በተጋነነ መልኩ በኤሌክትሪክ ተሽከሪካሪዎች ላይ ቢታይም በነዳጅ የሚሠሩ "አነስተኛ የበጀት መኪኖች" ላይም ጭማሪ እንደተስተዋለ ይናገራሉ።

ለምሳሌ ሱዙኪ ዲዛየር መኪና ከዚህ ቀደም ይሸጥ የነበረው 3 ሚሊዮን 300 ሺህ ሲሆን፤ አሁን ዋጋው ከ4 ሚሊዮን 300 ሺህ በላይ ደርሷል።

የኢትዮጵያ የመኪና ገበያ ላይ ጭማሪ ሲደረግ አዳዲሶች ብቻ ሳይሆን አገልግሎት የሰጡም ዋጋቸው እንደሚወደድ ባለሙያው ይናገራሉ።

ከውጭ ከሚገቡ የኤሌክትሪክ እና የነዳጅ መኪኖች በተጨማሪ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ወይም የሚገጣጠሙ ተሽከርካሪዎች ላይም ጭማሪው ይስተዋላል።

አቶ ብሩክ ለውጡን ሲያብራሩ "ጭማሪው የታየው የኤሌክትሪክ መኪና ስለጨመረ ወይም ሰው ነዳጅን ትቶ ወደ ኤሌክትሪክ ስለዞረ አይደለም። ሰዎች የነዳጅ ዋጋ ጨመረ ወይም እጥረት ተከሰተ ሲባል በቀላሉ ይደነግጣሉ፤ የኤሌክትሪክ መኪና ፍላጎት መጨመር ከዚህ በፊትም የታየ ነው" ይላሉ።

ከነዳጅ አቅርቦት እና ዋጋ ጋር በተያያዘ የሚፈጠው ስጋት ተጠቃሚዎች ወደተሻለው አማራጭ እንዲያዘነብሉ ገፊ ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ።

በኢትዮጵያ አብዛኛው የመኪና ግዢ የሚያከናውነው መካከለኛ ገቢ ያለው የማኅበረሰብ ክፍል መሆኑን በመጥቀስ በብዛት የሚሸጡት "በዋጋቸው አነስ ያሉት የቢዋይዲ ተሽከርካሪዎች" መሆናቸውን የአውቶሞቲቭ ጉዳዮች ተንታኙ ይናገራሉ።

አንድ ጊዜ ቻርጅ ተደርጎ እስከ 400 ኪሎ ሜትር የሚጓዘው የቢዋይዲ መኪና ዓይነት ከኢራን ጦርነት በፊት ወደ 3 ሚሊዮን 300 ሺህ ይሸጥ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ዋጋው እስከ 3 ሚሊዮን 800 ሺህ ደርሷል።

ይህ መኪና "የበጀት መኪና" በሚል በተመጣጣኝ ዋጋ ገበያ ላይ ይገኝ የነበረ እና በ10ሺህ ዶላር የሚሸጥ መኪና ከመሆኑ አንጻር "ለምን ኢትዮጵያ ውስጥ 4 ሚሊዮን ብር ድረስ ያወጣል?" በሚል ገዢዎች እንደሚጠይቁ ተንታኙ ያብራራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የተሽከርካሪ ገበያው ከኢራን ጦርነት በፊት ምን ይመስል ነበር?

አቶ ብሩክ በመኪኖች ላይ የዋጋ ጭማሪውን የሚመለከቱት የአውሮፓውያኑ 2026 ከገባበት ጊዜ አንስቶ ነው።

ቻይና ውስጥ የሚወጡ ሕጎች የመኪና ሽያጭ ላይ ጫና እንደሚያሳድሩ በመጥቀስ፤ "ከቻይና የምንገዛቸው አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ባይነዱም ጥቅም ላይ የዋሉ (Used) ተብለው ነው ኤክስፖርት የሚደረጉት" ይላሉ።

በቻይና ሕግ ተሽከርካሪዎች ለውጭ ገበያ ሲቀርቡ ያልተነዱ (0 mileage) ወይም አገልግሎት የሰጡም ቢሆን የኤክስፖርት ቁጥር ለመጨመር ነጋዴዎችን ማበረታቻ እርምጃዎች ሲወሰዱ ቆይተዋል።

በዚህ ዓመት የቻይና ተሽከሪካሪዎችን "ስም ለመጠበቅ" ሲባል ከተላለፉ አዳዲስ ድንጋጌዎች መካከል ጥቅም ላይ የዋሉ መኪኖች ኤክስፖርት ከመደረጋቸው በፊት 6 ወራት እንዲቆዩ ማድረግ ይጠቀሳል። ከዚያ ቀድመው ኤክስፖርት የሚደረጉ ከሆነ ግን መዳረሻው አገር ላይ መለዋወጫ ማቅረብ ግዴታ ሆኗል።

"ስድስት ወር በመጠበቅ ግዴታ ምክንያት ኤክስፖርት ሲደረጉ የነበሩ መኪኖች ቁጥራቸው ቀንሷል" ሲሉ አቶ ብሩክ ያስረዳሉ።

በአውሮፓውያኑ 2026 የተመረቱ የቻይና መኪኖች አሁንም ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ አለመግባታቸውንም ያክላሉ።

በቻይና በኤሌክትሪክ መኪኖች ላይ 5 በመቶ የታክስ ጭማሪ መደረጉም ሌላኛው የዋጋ ንረት ምክንያት ነው። በእዚህ ላይ የኢራን ጦርነት የመርከብ መጓጓዣ ዋጋ ላይ ያሳደረው ጫና መጨመሩ ለተሽከርካሪዎች ዋጋ መናር የራሱ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

"ከዱባይ እና አካባቢው ተሽከርካሪ የሚያመጡ አስመጪዎች እዚህ እየሸጡ ለቀጣይ ከዚያ ያዝዙ ነበር" የሚሉት የአውቶሞቲቭ ጉዳዮች ተንታኙ በሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት እና ጦርነቱ በፈጠረው ስጋት "የተጋነነ" የዋጋ ጭማሪ በገበያው ላይ መከሰቱን ይናገራሉ።

ለዋጋ መጨመሩ ከቻይና የሕግ ማሻሻያ በተጨማሪ በኢትዮጵያ በኩል ያሉ ለውጦችም እንደሚጠቀሱ ባለሙያው ይናገራሉ።

አስመጪዎች ከውጭ መኪና ሲያስገቡ ለባትሪ ዋስትና እንዲያቀርቡ፣ መለዋወጫ እንዲያቀርቡ እንዲሁም ከሽያጭ በኋላ ጥገና እንዲያቀርቡ የሚደነግግ ጠንካራ እና "ለማኅበረሰቡ የሚጠቅም" ሕግ መውጣቱን ያስረዳሉ።

ይሄንን መስፈርት አሟልተው ከትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የብቃት ማረጋገጫ ያደሱ የተሽከርካሪ አስመጪ ተቋማት ቁጥር አነስተኛ ሆኖ ቆይቷል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አንዳንድ አስገዳጅ ሁኔታዎችን በማላላቱ የብቃት ማረጋገጫ ያሳደሱ ተቋማት ቁጥር መጨመሩን አቶ ብሩን ይናገራሉ።

ለምሳሌ የጋራዥ መኖርን ግዴታ የሚያደርገው ድንጋጌ ላልቶ መኪና አስመጪዎች ጋራዥ ካላቸው ጋር እንዲጣመሩ ተደርጓል።

"ለስድስት ወራት ገደማ የብቃት ማረጋገጫቸውን አድሰው ተሽከርካሪ ማምጣት የቻሉ ድርጅቶች ቁጥር አንሶ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን መሻሻል አለ። ይሄ ተደማምሮ ያሳደረው የዋጋ ጭማሪ ላይ የኢራን ጦርነት ሲከሰት የማጓጓዣ ዋጋ ደግሞ ጨምሯል" ብለዋል።

የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ዋጋ ላይ መናርን ማስከተሉን ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኤሌክትሪክ ዋጋ ጭማሪ ከኢራን ጦርነት ጋር ይገናኛል?

በኢትዮጵያ መኪና ገበያ ከፍተኛ ድርሻ ያለው ታምሪን ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ፤ የኦፕሬሽን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ፋኑኤል ኃይለ ከኢራን ጦርነት ወዲህ "የመኪና አሽከርካሪዎች የነዳጅ መኪና ፍራቻ የጨመረ ይመስላል" ይላሉ።

ብዙ አሽከርካሪዎች ከነዳጅ ወደ ኤሌክትሪክ መኪና የመሻገር "ጉጉት" እንዳሳዩ እና ገበያውም የሚያሳየው የፍላጎት መጨመርን መሆኑን ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ ያለው የመርከብ ጉዞ ዋጋ መጨመር የተሽከርካሪዎች ገበያ ላይ ያሳደረው ጫና በጉልህ የሚታይ መሆኑን ያስረዳሉ።

ታምሪን ለገበያ ከሚያቀርባቸው ተሽከርካሪዎች መካከል የሱዙኪ ከነዳጅ ሞተር ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል በመውሰድ የሚሠሩ (Smart Mild Hybrid) እንዲሁም የጃክ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ይገኙበታል።

አቶ ፋኑኤል አሁን እጃቸው ላይ ያሉ መኪኖችን በተመለከተ "ዋና ወጪዎች ተሰልተው በተቀመጠ የትርፍ ህዳግ" ስለሚሠሩ የዋጋ ለውጥ አለማድረጋቸውን ያስረዳሉ።

ሆኖም ግን ተመሳሳይ ሞዴሎች ላይ የአምራች ዋጋ መጨመር ወይም የባሕር ትራንስፖርት ዋጋ መጨመር በግልጽ ታይቷል።

"ከጂቡቲ መኪኖችን ለማንሳት በትራንስፖርት ላይ ከእጥፍ በላይ ጭማሪ ታይቷል" ይላሉ።

አሁን በእጃቸው ላይ ባሉ መኪኖች ላይ ዋጋ ባይጨምሩም፤ በቀጣይ የሚመጡ ተሽከርካሪዎች ላይ ጭማሪው እንደሚታይ ግን "ግልጽ ነው" ሲሉ የኦፕሬሽን ምክትል ሥራ አስኪያጁ ይናገራሉ።

ከኢራን ጦርነት በተጨማሪ ከታክስ እና ከቫት ጋር የተያያዙ የዋጋ ጭማሪዎች የተሽከርካሪዎች ዋጋ ላይ እንደሚንጸባረቁም ያክላሉ።

በአሁኑ ወቅት ገበያ ላይ ከሚገኙት ተሽከርካሪዎች ውስጥ ለምሳሌ ያህል ሱዙኪ ዲዛየር 4.6 ሚሊዮን ብር ገደማ እንዲሁም የጃክ መኪና ወደ 4.2 ሚሊዮን ብር ገደማ በገበያ ላይ እየተሸጡ ነው።

አቶ ፋኑኤል፤ እንደ አቶ ብሩክ ሁሉ ቻይና በአዲሱ የአውሮፓውያን ዓመት ያወጣችው ሕግ ያሳደረውን ጫናም ይጠቅሳሉ።

የቻይና አዲስ ሕግ "የዋጋ መቀየር" እንደሚያስከትል "መኪኖች በሕጋዊ አስመጪዎች በኩል ብቻ፣ በትክክለኛ ዋጋቸው ከሙሉ ዋስት ጋር ስለሚመጡ የዋጋ መስተካከል ይኖራል" በማለት ያስረዳሉ።

የኢራን ጦርነት ያስከተለው የነዳጅ ዋጋ መጨመር በባሕር እና በየብስ ጉዞ ላይ ያሳደረው የዋጋ መናር "መንገድ ላይ ያሉ ጭነቶችን ጨምሮ የዋጋ ለውጥ" እንዳስከተለ ሳይጠቅሱ አያልፉም።

የሱዙኪም የጃክም ተሽከርካሪዎች እንዲሁም መለዋወጫዎች ዋጋ በቀጣይ መጨመሩ አይቀሬ መሆኑን ያክላሉ።

ከኢራን ጦርነት ወዲህ "የነዳጅ መኪና ያላቸው ሰዎች እንዲሁም ድርጅቶች ሸጠው ወደ ኤሌክትሪክ የመቀየር ፍላጎት" መታየቱን ይጠቅሳሉ። ተመሳሳይ የፍላጎት ለውጥ በአዲስ መኪና ገዢዎች ዘንድም ተስተውሏል።

ኢትዮጵያ ካለፉት ጥቂት ዓመታት በወዲህ በነዳጅ በሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ላይ ገደብ በመጣል ለኤሌክትሪክ መኪኖች ማበራታቻን እየሰጠች ነው።

በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰተው ጦርነት ለነዳጅ እጥረት ምክንያት በመሆኑ መኪና የመግዛት ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ፊታቸውን ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እንዲያዞሩ ተጨማሪ ምክንያት ሆኗቸዋል።