በአንድ ሰዓት ውስጥ 60 ደቂቃዎች እንዲኖሩ የተደረገበት ጥንታዊ ምክንያት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 7 ደቂቃ

5000 ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረ ሚስጥራዊ ውሳኔ ዛሬም ጊዜን የምንቆጥርበትን መንገድ በቀጥታ ለመወሰን በቅቷል።

እአአ ጥቅምት 1793 ደግሞ አዲስ የተቋቋመው የፈረንሳይ ሪፐብሊክ ጊዜን ለመቀየር በመወሰን ያልተሳካ ሙከራ ማድረግ ጀመረ።

አብዮተኞቹ እንደወሰኑት ከሆነ አንድ ቀኑ በ24 ሰዓታት ሳይሆን በ10 ሰዓታት ይከፋፈላል። እያንዳንዱ ሰዓት 100 ደቂቃዎች ይኖሩታል። አንድ ደቂቃ ደግሞ 100 ሰከንዶች ይኖሩታል።

ይህም የዓመታትን አወቃቀር ለማዘመን (እና ከክርስትና ጋር ያለውን ቁርኝት ለማላቀቀ) የታለመ የቀን መቁጠሪያ አብዮት አካል ነበር። በዚህ ዕቅድ መሠረት አንድ ሳምንት 10 ቀናት እንዲኖሩት ነበር የታቀደው። አሁን ያሉትን ሰዓቶች ወደ መደበኛ ቁጥሮች የመቀየር ሥራ ተጀመረ። በማዘጋጃ ቤቶች እና በሃውልቶች ላይ የሚገኙ ሰዓቶችን የመቀየር እንቅስቃሴዎችም ተጀመሩ።

በለንደን በሚገኘው ሮያል ሙዚየም ግሪንዊች የሳይንስ አስተባባሪ የሆኑት ፊን ቡሪጅ እንዳሉት ይህ አካሄድ በፍጥነት ማለቂያ የሌለው ራስ ምታት ማስከተሉ አልቀረም።

አሁን ያሉትን ሰዓቶች እንደገና መቅረጽ እና መለወጥ እጅግ አስቸጋሪ ሆኖ ተገኘ። ስርዓቱ ፈረንሳይን ከጎረቤት አገሮች ለያት። የገጠሩ ሕዝብ የእረፍት ቀኑ በ10ኛው ቀን ብቻ መሆኑን ጠላው። ይህ ዓይነቱ የሰዓት አቆጣጠር በፈረንሳይ ከአንድ ዓመት በላይ ብዙም አልዘለቀም።

በቀን 24 ሰዓት፣ በሰዓት 60 ደቂቃ እና በደቂቃ 60 ሰከንድ እንዴት መቁጠር እንደጀመርን ለመረዳት ወደ ቀድሞው ዘመን መመለስ አለብን። በዚህ መንገድ ላይ እንድንቆጥር ያስቻለን ከቀደምት የቁጥር ስርዓቶች አንዱ ሲሆን ይህ አስቸጋሪ አቆጣጠር ለምን እስካሁን እንደቆየም ያብራራል።

የ60 መሠረት

መነሻዎቹ ሱሜሪያውያን ናቸው። ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ5300-1940 ገደማ በሜሶፖታሚያ (በዘመናዊቷ ኢራቅ አካባቢ) የኖሩ እና ከተሞችን ከመሠረቱት የመጀመሪያዎቹ ስልጣኔዎች አንዱ ናቸው።

ከብዙ ፈጠራዎቻቸው መካከል መስኖ እና ማረሻን ጨምሮ የመጀመሪያውን የታወቀ የጽሑፍ ስርዓት እንደፈጠሩ ይታመናል። ይህም በ60 ፅንሰ-ሃሳብ ላይ የተመሠረተ የቁጥር ስርዓትን ያካትታል።

እጅዎን ወፊት ዘርግተው ጣትዎን ሲያጥፉ ሦስት መገጣጠሚያዎች እንዳለዎት ያያሉ። በአንድ እጅ ጣቶች ላይ ያሉትን ሁሉንም መገጣጠሚያዎች (አውራ ጣትን ሳይጨምር) ይቆጥሩ እና 12 ይሆናሉ።

በተመሳሳይ ጊዜ የሌላኛው እጅዎ ጣት በመጠቀም አንድ ጊዜ እንደቆጠሩ ይያዙ። በሁለተኛው እጅዎ ላይ ያሉት አምስት ጣቶች እስኪጠቀሙ ድረስ በመጀመሪያው እጅዎ የጀመሩትን ቆጠራ ይቀጥሉ።

በቀላሉ ለማስረዳት በግራ እጅዎ አራት ጣቶች ላይ ያሉትን ሦስት አንጓዎች ቆጥረው 12 ሲደርሱ በቀኝ በኩል የመጀመሪያውን ጣት አንድ ብለው ይቆጣራሉ። ተመልሰው ወደ ግራ እጅ በመመለስ በድጋሚ ቆጠራውን ይቀጥላሉ።

በዚህ መንገድ የቀኝ እጅዎት አምስት ጣቶች ተቆጥረው እስኪያልቁ መቁጠርዎን ይቀጥላሉ ማለት ነው። ቆጥረው ሲጨርሱ ስንት ያገኛሉ? ስልሳ።

ይህ የሱሜሪያውያን የሒሳብ ስርዓታቸውን በ10 ሳይሆን በ60 ላይ ለምን እንደመሠረቱ ከሚገልጹ ግምታዊ መላ ምቶች አንዱ ነው። ዛሬ ጊዜን የምንለካበት መንገድም ሆኗል።

የፎቶው ባለመብት, The Fitzwilliam Museum, University of Cambridge

የምስሉ መግለጫ, በፈረንሣይ አብዮታዊ መንግሥት በ18ኛው ክፍለ ዘመን የተዋወቀው አዲሱ የሰዓት አቆጣጠር
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በወቅቱ የከተሞቻቸው እያደጉ መምጣት እና የሚፈልጉትን ትልቅ እንዲሁም ውስብስብ የግብርና ስርዓት ለመመዝገብ በሚል የጽሑፍ ቁጥሮች ዕድገት መኖር ነበረበት ሲሉ በካናዳ የኒው ብሩንስዊክ ዩኒቨርሲቲ የኩኒፎርም ባህሎች ባለሙያ የሆኑት ማርቲን ዊሊስ ሞንሮ ተናግረዋል።

ቁጥሮችን ለመከታተል፣ ዝርዝሮቹን በለስላሳ ሸክላ ላይ ለማስፈር ከታብሌት ያነሱ ሸክላዎችን መጠቀም ጀመሩ። ብዙም ሳይቆይ ሌሎች የሥዕል ምልክቶች የሱሜሪያውያን ታዋቂ የኩኒፎርም ጽሑፍን ተከትለው ብቅ አሉ።

እነዚህ የሸክላ ታብሌቶች የተገለጡት እና መረዳት የተቻሉት በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ነበር። ሱሜሪያውያን በርካታ የቁጥር ስርዓቶችን እንደተጠቀሙ ያሳያሉ ብለዋል ሞንሮ። ለሒሳብ በኋላም ለሥነ ፈለክ እና ለጊዜ መዋል የጀመረው በጣም ታዋቂው ሴክሳጌሲማል ሲስተም ተብሎ የሚጠራው ነው።

ሱሜሪያውያን አሁን 10ን ከምንጠቀምበት ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ 60 ተጠቅመዋል።

ዘጠኝ ስንደርስ በግራ በኩል አንድን ጽፈን በቀኝ በኩል ዜሮ እንጨምራለን ሲሉ በቅርቡ አሜሪካ ከሚገኘው ብራውን ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ እና የጥንት ታሪክ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያጠናቀቁት ኤሪካ መስዛሮስ ተናግረዋል።

"ከሴክሳጌሲማል ጋር ተመሳሳይ ነው። 59 ደርሰው ከዚያ በላይ የሆነ ቁጥር ከመያዝ ይልቅ አንድ ብቻ ይጠቀማሉ። ለዚህም አንድ ቦታ ብቻ ይጠቀማሉ።"

ሱሜሪያኖች የ60ን ስርዓት ለምን እንደወሰዱ ግልጽ አይደለም።

"60 ራሱ ከየት እንደመጣ ብዙ ማስረጃ የለም" ይላሉ ሞንሮ። አንዳንድ ምሁራን የሴክሳጌሲማል ስርዓት ከሱሜሪያውያን በፊት እንደነበረ ይጠቁማሉ።

የአጠቃቀም ቀላልነቱ ግን ግልጽ ነው። ያለምንም ትርፍ ስልሳ በአንድ፣ በሁለት፣ በሦስት፣ በአራት፣ በአምስት፣ በስድስት፣ በ10፣ በ12፣ በ15፣ በ20፣ በ30 እና በ60 ሊከፋፈል ይችላሉ።

በአንድ፣ በሁለት፣ በአምስት እና በ10 ብቻ ሊከፈል ከሚችለው 10 ጋር በማነጻጸር ብቻ ጥቅሞቹ ግልጽ መሆን ይጀምራሉ። "ለምሳሌ ለሂሳብ አያያዝ፣ ለግብር ወይም ለልጅዎ ውርስ ለመከፋፈል ቁጥሮችን እያዘጋጁ ከሆነ፣ እነዚህን የሒሳብ ሥራዎች ለማከናወን ቀላል መንገድ መኖሩ በጣም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል" ይላሉ ሜዛሮስ።

የጊዜ አመጣጥ

ሱሜሪያውያን ጊዜን እንደተጠቀሙ የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ የለም።

ሞንሮ የጊዜ አጠቃቀም በክልሉ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በባቢሎናውያን (ከሱሜሪያውያን በኋላ የመጣው ጥንታዊ የሜሶፖታሚያ ሥልጣኔ) የፀሐይ ቁጥሮችን እና የውሃ ሰዓቶችን ከመጠቀማቸው በፊት እንደነበረ ይናገራሉ።

ቀንን በሰዓታት በመክፈል የሚታወቀው የመጀመሪያው ሥልጣኔ የጥንት ግብጻውያን ነው ሲሉ በስዊዘርላንድ የባዝል ዩኒቨርሲቲ የአርኪኦአስትሮኖመር የሆኑት ሪታ ጋውትሺ ተናግረዋል።

ይህም ከክርስቶስ ልደት በፊት በ2500 ገደማ እንደነበር በሃይማኖታዊ ጽሑፎች ውስጥ ይታያል።

ከሰዓቶች ጋር የተያያዙ የመጀመሪያዎቹ የታወቁ ምልክቶች መጀመሪያ ላይ የሌሊቱን 12 ሰዓታት የሚያመለክቱ ነበሩ።

እነዚህም ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ2100 እስከ 1800 ባለው ጊዜ ውስጥ በነበሩ ግብጻውያን የሬሳ ሣጥን ውስጠኛ ክዳን ላይ የተገኙ በአግድም የተሳሉ የኮከብ ሰዓቶች እንደነበሩ ጋውትሺ ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, The Board of Trustees of the Science Museum, London

የምስሉ መግለጫ, ጊዜን ለመለካት ከሚያገለግሉት የጥንት መሳሪያዎች መካከል ሰንዲያልስ በግብፅ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1500 ጥቅም ላይ መዋሉ ተገልጿል

ግብፃውያን በ12 ለመከፋፈል ለምን እንደመረጡ እርግጠኛ አይደለም። ይህም ሙሉ ቀን ውስጥ ያሉትን ሰዓታት 24 አድርጓል።

ግብፃውያን የ12 ህብረ ከዋክብት የዞዲያክ ዑደት ነበራቸው፤ ነገር ግን ይህ የሆነው ለመጀመሪያ ጊዜ 12 ሰዓታት ከተጠቀሱ በኋላ ሊሆን ይችላል።

የአንድ እጅ መገጣጠሚያዎችን እና ጣቶችን በመጠቀም እስከ 12 መቁጠርም ሌላው አማራጭ ነው። አንዳንድ ባለሙያዎች የ10ቀን ሳምንት ምርጫቸው ከተወሰኑ ኮከቦች ጋር እንዴት እንደተቆራኘ ማሳያ ሊሆን እንደሚችል ያስባሉ።

የፀሐይ መነፅርን እና የውሃ ሰዓቶችን በመጠቀም ጊዜን ለመለካት የሚታወቁ የመጀመሪያዎቹ መሳሪያዎች ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1500 ግብፅ ውስጥ ታይተዋል።

አንዳንዶቹ በዕለት ተዕለት ሥራ ጥቅም ላይ ይውሉ ነበር። አብዛኛዎቹ ግን "ከጊዜ አጠባበቅ ይልቅ ከሃይማኖታዊ ሉል እና ከአምልኮ ሥርዓቶች ጋር የተያያዙ ሊሆኑ ይችላሉ" ይላሉ ጋውትሺ።

"በግሌ፣ ብዙዎቹ ለአማልክት የተሰጡ የቃል ኪዳን ስጦታዎች እንደሆኑ አስባለሁ። [ስለዘመኑ] ሳይንሳዊ ጊዜ አጠቃቀም ብዙ መረጃ የለንም" ብለዋል።

መጀመሪያ ላይ ስለ ዕለታዊ ሕይወት ጉዳዮች በሚገልጹ ጽሑፎች ውስጥ ትንሹ ክፍለ ጊዜ የሥራ ፈረቃ ነበር ይላሉ ጋውትሺ። ይህም ብዙውን ጊዜ ጠዋት ወይም ከሰዓት እንደሆነ ይታሰባል። ነገር ግን በጥንቷ ግብፅ (ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ30 ገደማ ጀምሮ) በሮማውያን ዘመን ሰዓታት መደበኛ በመሆን ግማሽ ሰዓታትም መታየት ጀመሩ ይላሉ።

የደቂቃዎች መምጣት

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባቢሎናውያንም የሰዓታት አጠቃቀማቸውን እያዳበሩ ነበር። ሰዓትን ወደ በጣም ትናንሽ ክፍሎች የከፋፈሉ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ሆነዋል። ይህ ግን ለጊዜ አጠባበቅ ዓላማዎች አልነበረም።

ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ2000 እስከ 540 የነበሩት ባቢሎናውያን ከሱሜሪያዊያን የኩኒፎርም ስክሪፕት እና የሴክሳጌሲማል የቁጥር ስርዓትን ተቀብለዋል። ሜዛሮስ እንደሚሉት ከሆነ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1000 ገደማ ፀሐይ በሰማይ ላይ ወደነበረችበት ተመሳሳይ ቦታ ለመመለስ ምን ያህል ጊዜ እንደፈጀባት በመስላት የቀን መቁጠሪያ አዘጋጅተው ነበር። ይህም ከ360 ቀናት ትንሽ ፈቀቅ ያለ ነበር።

ይህም በ60 ላይ የተመሠረተ የቁጥር ስርዓትን ለሚጠቀምው ሥልጣኔ ጠቃሚ ቁጥር ነበር። "ዋው፣ በሴክሳጌሲማል ስርዓት ውስጥ ይህ ጥሩ አይደለምን?" ይላሉ ሜዛሮስ።

"ይህም እያንዳንዳቸው 30 ቀናት ወደያዙ 12 ወራትን መርቷል" ይህም ከጨረቃ ዑደት ጋር ይጣጣማል ብለዋል።

ባቢሎናውያን ለዕለታዊ አጠቃቀም የመሆን የጊዜ ስርዓት ፈጥረዋል። ይህም ግብጻውያን እንዳደረጉት ቀንን እና ሌሊትን ወደ 12 መከፋፈል ነው። የእነዚህ "ወቅታዊ ሰዓቶች" ርዝመት እንደ ቀኑ እና ሌሊቱ ይለያያል። "ቀኑን በ12 የከፈልነው የሌሊቱን ሰማይ በ12 ወራት እና በ12 የዞዲያክ ምልክቶች ስለከፈልነው ነው" ይላሉ ሜሳሮስ።

ሌሎች ብዙ ጥንታዊ ሥልጣኔዎች ወቅታዊውን ሰዓቶችን ይጠቀሙ ነበር። ይህም በ15ኛው ክፍለ ዘመን በአውሮፓ እና በ19ኛው ክፍለ ዘመን ጃፓን ጥቅም ላይ ውለዋል።

ይህ የወቅቱ ሰዓት ግን ወደ ትናንሽ ክፍሎች አልተከፋፈለም ሲሉ ሞንሮ ተናግረዋል።

"[ይህ] እስከ ዘመናዊው ዘመን መጀመሪያ ድረስ ምንም ነገር አልነበረም… ባለማስፈለጉ ምክንያት በሜሶፖታሚያ እና በሌሎች ጥንታዊ ባህሎች ውስጥ የለም።"

የፎቶው ባለመብት, Cuneiform Digital Library Initiative

የምስሉ መግለጫ, የሱሜሪያን ታብሌት ከክርስቶስ ልደት በፊት በ3200 የሰው ልጅ ሒሳብን ያሰላበት የነበረ መሳሪያ ነው

ባቢሎናውያን ለዕለታዊ አገልግሎት ሳይሆን የሥነ ፈለክ ክስተቶችን ለማስላት እና ለመለካት ሌላ የጊዜ ስርዓት ፈጥረዋል።

ይህም ቀኑን በ12 "ቤሩ" ከፍሎታል። እያንዳንዱን ቤሩ ከሁለት ሰዓት ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ልናስብ እንችላለን። ባቢሎኒያ ብቻ ሳይሆኑ ለምሳሌ በጥንታዊ ቻይና እና ጃፓንም ታይተዋል።

በስሌቶቻቸው ውስጥ የበለጠ ግልጽነት ለመጨመር ባለው ፍላጎት ምክንያት ባቢሎናውያን የቤሩ ድርብ ሰዓታትን ወደ 30 ጥንታዊ ደቂቃዎች መከፋፈል ጀመሩ።

እያንዳንዳቸውም ከአሁኑ አራት ደቂቃዎቻችን አራት ጋር እኩል ወደ ሆኑ እና ኡሽ ወደ ተሰኙ የጥንት 30 ደቂቃዎች የተከፋፈሉ ናቸው።

እነዚህም ኒንዳ ወደሚባሉ 60 ትናንሽ ክፍሎች ተከፍለዋል። እያንዳንዳቸው አራት ዘመናዊ ሰከንዶች ያህል ዋጋ አላቸው። እነዚህ ንዑስ ክፍሎች ምናልባት ጥቅም ላይ የዋሉት "ነገሮችን በሴክሳጌሲማል ስርዓት ውስጥ ወደ 60 ቡድኖች ስለምንከፍል" ነው ይላሉ ሜዛሮስ።

ሆኖም ባቢሎናውያን "ጊዜን እንደ መከፋፈል አላሰቡም። በሰማይ ያለውን ርቀት ወይም የፕላኔቶችን ፍጥነት የሚለኩ ቁጥሮችን እንደ መከፋፈል እያሰቡት ነበር" ሲሉ ሞንሮ ተናግረዋል።

ከእነዚህ የጥንት የጊዜ አቆጣጠሮች መካከል ማን ማን ላይ እንደተመሠረተ በትክክል መናገር ከባድ ሊሆን ይችላል ይላሉ ጋውትሺ። "ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ330 ጀምሮ በአሌክሳንድሪያ አዲስ የሳይንስ ማዕከል የነበራት ግብጽ፤ ሰዎች እና ከሁሉም አካባቢዎች የመጡ ሃሳቦቻቸው የተዋሃዱበት ማዕከል ሆነች። ይህንን የሄለኒዝም ዓለም ብለን የምንጠራው ነው" ብለዋል።

ያም ሆኖ የጥንት ግሪኮች የባቢሎናውያንን የሥነ ፈለክ የጊዜ ስርዓት እንደተቀበሉት ግልጽ ነው ይላሉ ሜዛሮስ። "ተመሳሳይ ክፍፍል የነበራቸው ደግሞ ለነባር ሂደቶች አዳዲስ ምልከታዎችን እንዲያክሉ አስችሏቸዋል… ለባቢሎናውያን በቂ የሆነ ጥሩ ስርዓት ነው። ከእነሱ በኋላ የመጡት ሰዎች የሥነ ፈለክ መረጃዎችን እና መረጃዎችን ለመውሰድም ተጠቅመውበታል" ብለዋል።

ሰከንዶችን መቁጠር

ግሪኮች "ሰዎች ተመሳሳይ የመናገሪያ ጊዜ እንዲኖራቸው ለማረጋገጥ" በፍርድ ቤት የአሸዋ ሰዓቶች ቢያዘጋጁም የባቢሎናውያን የጊዜ ስርዓት ግን በኮከብ ቆጣሪዎች በፅንሰ-ሀሳብ ብቻ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን በአብዛኛው ለዕለት ተዕለት ሕይወት ጠቃሚ አይደለም" ይላሉ ጋውትሺ።

ከሄለንስቲክ ውህደቶች የወጡ የሰዓት፣ የደቂቃ እና የሰከንድ ፅንሰ-ሃሳቦች እስከ ዛሬ ድረስ ለዘመናት ተላልፈዋል። በጊዜ አቆጣጠር መሳሪያዎች ደቂቃዎች እና ሰከንዶች በየቀኑ ጥቅም ላይ መዋል እንዲጀምሩ ትክክለኛ ሆነው የተገኙት ከጥቂት መቶ ዓመታት በፊት ነበር።

ሰከንድ አሁን ስፍር ቁጥር በሌላቸው ሳይንሳዊ ትርጓሜዎች ውስጥ ጥቅም ላይ ውሏል። ከአንድ ሰከንድ ያነሱ የጊዜ ክፍሎችን መቁጠር ከጀመርን በኋላ፣ ሳይንቲስቶች ወደ ሜትሪክ ሲስተም ተዛውረው ወደ ሚሊ እና ማይክሮሰከንድ ይከፋፍሏቸዋል።

አቶሚክ ሰዓቶች በ20ኛው ክፍለ ዘመን ሳይንቲስቶች ሰከንድን በትክክል እንደገና እንዲገልጹ አስችሏቸዋል።

ይህም በፀሐይ ሽክርክሪቶች ላይ በመመስረት ከመግለፅ ወደ በኬሲየም-133 አቶሞች የማይክሮዌቭ ጨረር ላይ የተመሠረተ ትክክለኛ አካሄድ እንዲሸጋገሩ አስችሏቸዋል።

ዛሬ የአቶሚክ ሰዓቶች ከኢንተርኔት እስከ ጂፒኤስ ያለ እያንዳንዱን ዘመናዊ ሰዓት ይይዛል።

የጊዜ አቆጣጠር ታሪክ በሰው ልጅ ውሳኔዎች የሚወሰን የሰው ፈጠራ መሆኑን ያሳያል። ሰዓታት፣ ደቂቃዎች እና ሰከንዶች በምርጫዎች፣ በአጋጣሚዎች እና በክስተቶች አማካኝነት የተገኙ ናቸው።

ለዘመናትም እንደ ጠቃሚ ቅርስ ሆነው ቆይተዋል። ስርዓቱን አሁን መቀየር ምናልባትም በጣም ከባድ ሊሆን ይችላል።

ፈረንሳይ በ18ኛው ክፍለ ዘመን ሰዓትን ለመቀየር ባደረገችው ሙከራ ጨምር አዲሱ ስርዓት በተግባር ብዙም ጥቅም ላይ አልዋለም ነበር። ሪፐብሊኩ የርቀት መለኪያዎችን እና ምንዛሬን ለመቀየር ተመሳሳይ ጥረቶች ቢተገበሩም የቀድሞው አካሄድ እስከ ዛሬ ድረስ ጥቅም ላይ ውሏል።

የአስርዮሽ ሰዓት አቆጣጠር ለ17 ወራት ብቻ ቢቆይም የቀን መቁጠሪያው ለአስር ዓመታት ያህል ጥቅም ላይ ቢውልም "ተሞክሮ ነበር ግን አልተሳካም" ይላሉ ቡሪጅ።

የፈረንሳይ ብሔራዊ ኮንቬንሽን አባል የነበሩት ክላውድ-አንቶይን ፕሪዬ በ1795 ያደረጉት ንግግር የአስርዮሽ ሰዓት አጠቃቀምን መጨረሻ የጠቆሙ ሊሆኑ ይችላሉ።

ይህ ነው የሚባል ጥቅሙን የሚያቀርብ ሰው ካለመኖሩም በላይ ጥሩ ነበሩ ባሏቸው ሌሎች መለኪያዎች ላይ ጠባሳ አሳርፏል ሲሉ ገልጸዋል።