አዲሱ የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ ማን ናቸው?

ሞጅታባ ኻሜኒ

የፎቶው ባለመብት, Tasnim News Agency

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት የተገደሉት የኢራን አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ሁለተኛ ልጅ የሆኑት ሞጅታባ ኻሜኒ አባታቸውን በመተካት የአገሪቱ ጠቅላይ መሪ እንዲሆኑ ተሹመዋል።

አዲስ መሪ ለመምረጥ የተሰበሰበው 88 አባላት ያሉት የሊቃውንት ጉባኤ፤ የአባታቸውን ጠንካራ ፖሊሲዎች ያስቀጥላሉ ተብለው የሚገመቱትን ሞጅታባን መምረጡን አስታውቋል።

ሞጅታባ ይህንን ሥልጣን የተረከቡት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እርሳቸው እንዲሾሙ እንደማይፈልጉ እየተናገሩ ባሉበት ወቅት ነው።

የሞጅታባ መመረጥ "ተቀባይነት እንደሌለው" ሲናገሩ የቆዩት ትራምፕ፤ ምርጫው ይፋ ከሆነ በኋላ ደስተኛ አለመሆናቸውን እንደገለጹ ፎክስ ኒውስ ዘግቧል።

እስራኤልም ብትሆን ሥልጣኑን የሚረከበውን ሰው የጥቃት ዒላማ እንደምታደርግ ዝታለች። የኢራን የደኅንነት ኃላፊ በበኩላቸው አዲሱ ጠቅላይ መሪ የተመረጡት የሊቃውንት ጉባዔው ላይ "የትራምፕ ቦንብ ድብደባ ስጋት" በተጋረጠበት ሁኔታ ውስጥ እንደሆነ ተናግሯል።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ የጠቅላይ መሪነቱን ሥልጣን የተረከቡት የ56 ዓመቱ ሞጅታባ ከአባታቸው በተቃራኒ ብዙም ዕይታ ውስጥ የገባ ሕይወት አልነበራቸውም።

ምንም ዓይነት የመንግሥት ሥልጣንም ሳይዙ ቆይተዋል። ለሕዝብ የቀረቡ ንግግሮችን ወይም ቃለ መጠይቆችን ካለማድረጋቸውም በላይ ጥቂት በፎቶዎች እና ቪዲዮዎች ብቻ ነው የሚታወቁት።

ሆኖም የአባታቸውን ወንበር ይተካሉ የሚል ለረዥም ጊዜ የቆዩ ጭምጭምታዎች ነበሩ። በ2000ዎቹ መጨረሻ በዊኪሊክስ ይፋ የተደረጉ የአሜሪካ የዲፕሎማሲ መረጃዎች "ከበስተጀርባ ያለው ኃይል" ሲሉ ይገልጿቸዋል።

በአሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) ዘገባ መሠረት ሞጅታባ በሥርዓቱ ውስጥ "ብቃት ያለው እና ኃይለኛ መሪ" ተብለው በሰፊው ይታመኑ ነበር።

የሞጅታባ ኻሜኒን ባነር የያዘ ኢራናዊ
የምስሉ መግለጫ, ሞጅታባ ኻሜኒ ቀጣዩ መሪ እንደሚሆኑ ተገምቷል

ሞጅታባ ኻሜኒ ማን ናቸው?

ሞጅታባ የተወለዱት በአውሮፓውያኑ መስከረም 8 ቀን 1969 በሰሜን ምሥራቅ ማሽሃድ ከተማ ውስጥ ሲሆን፣ ከስድስቱ የኻሜኒ ልጆች ሁለተኛው ናቸው።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዋና ከተማዋ ቴህራን ውስጥ በሚገኘው ሃይማኖታዊው አላቪ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።

ሞጅታባ በ17 ዓመታቸው በኢራን-ኢራቅ ጦርነት ወቅት ለበርካታ አጫጭር ጊዜያት በአገራቸው ጦር ውስጥ አገልግለዋል ሲሉ የኢራን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል ለስምንት ዓመታት የዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት የኢራን አገዛዝ ኢራቅን ይደግፉ በነበሩት በአሜሪካ እና በምዕራባውያን ላይ ያለውን ጥርጣሬ የበለጠ እንዲያጠናክር አድርጎታል።

በ1999 ሞጅታባ የሺአ ሃይማኖታዊ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ቆም ወደ ተባለችው የሺአዎች ቅድስት ከተማ አቅንተዋል።

ከዚያም መልስ እስከአሁን ድረስ የሃይማኖት አባቶችን ልብስ ያለበሱ ሲሆን፣ በለጋ ዕድሜያቸው ሊከታተሉት የሚገባውን ሃይማኖታዊ ትምህርት በ30 ዓመታቸው ለመከታተል ለምን እንደወሰኑም አይታወቅም።

ሞጅታባ በኢራን አመራር ውስጥ በመካከለኛ ደረጃ ላይ ያሉ ሃይማኖታዊ መሪ በመሆናቸው ጠቅላይ መሪ ሆነው ለመመረጥ ያላቸውን ዕድል ሊያደናቅፈው ይችላል የሚል ግምት ነበር።

ሞጅታባ ዃሜኒ በ2024

የፎቶው ባለመብት, West Asia News Agency Via Reuters

ከቅርብ ቀናት ወዲህ ለኢራን አስተዳደር ቅርበት ያላቸው አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት እና ባለሥልጣናት ሞጅታባ ኻሜኒን "አያቶላህ" በማለት በከፍተኛው የሃይማኖት ማዕረግ መጠራት ጀምረዋል።

አንዳንድ ታዛቢዎች ጉዳዩ የሃይማኖት ደረጃቸውን ከፍ ለማድረግ እና ለአገሪቱ አመራርነት ዕጩ አድርጎ ለማቅረብ እንደተዘየደ ሙከራ አድርገው ቆጥረውታል።

"አያቶላህ" የሚለውን ማዕረግ መያዝ የአንድን ሰው የትምህርት ደረጃ እና እውቀት አመላካች ተደርጎ ይወሰዳል። ቀጣዩን መሪ ለመምረጥ ከሚያስፈልጉት መስፈርቶች እና ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ ተደርጎም ይቆጠራል።

ሟቹ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ በአውሮፓውያኑ 1989 ሁለተኛው ጠቅላይ መሪ ከሆኑ በኋላ በፍጥነት "አያቶላህ" ተብለው ማዕረግ መሰጠቱን ማስታወስ ያስፈልጋል።

የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ክሶች

የሞጅታባ ስም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሕዝብ ጎልቶ የደረሰው ማህሙድ አህመዲነጃድ በአውሮፓውያኑ 2005 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ባሸነፉበት ወቅት ነው።

የለውጥ አራማጁ ዕጩ መህዲ ካሮቢ ለጠቅላይ መሪው አያቶላህ ኻሜኒ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ልጃቻው ሞጅታባ በአብዮታዊው ዘብ እና ባሲጅ በሚባለው መንግሥታዊ ሚሊሻ አማካኝነት አህመዲንጃድ እንዲያሸንፉ ለሃይማኖት ቡድኖች ገንዘብ በመስጠት በድምጽ አሰጣጡ ላይ ጣልቃ ገብተዋል ሲሉ ከስሰዋቸዋል።

ከአራት ዓመታት በኋላም ሞጅታባ ተመሳሳይ ክስ ገጥሟቸዋል። የአህመዲንጃድ ዳግም መመረጥ በመላ አገሪቱ አረንጓዴ ንቅናቄ በመባል የሚታወቀውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ቀስቅሷል።

አንዳንድ ተቃዋሚዎች ሞጅታባ አባታቸውን በመተካት በኢራን ጠቅላይ መሪ ሆነው ሊተኩ ይችላል የሚለውን ሀሳብ የሚቃወሙ መፈክሮችን አሰምተዋል።

በወቅቱ ምክትል የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ሙስጣፋ ታጅዛዴህ ውጤቱን "የምርጫ መፈንቅለ መንግሥት" ሲሉ ገልጸውታል። ይህንን ተከትሎ ለሰባት ዓመታት የታሰሩ ሲሆን፣ ይህም "የሞጅታባ ኻሜኒ ቀጥተኛ ፍላጎት" እንደሆነ ተናግረዋል።

ተቃዋሚዎች በ2009 አደባባይ ወጥተው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የ2009ኙ የአረንጓዴ ንቅናቄ

የለውጥ አራማጆች የሚባሉት ሚር-ሆሴይን ሙሳቪ እና መህዲ ካሮቢ ከአውሮፓውያኑ 2009 ምርጫ በኋላ በቁም እስር ላይ ቆይተዋል።

የካቲት 2012 ላይ ሞጅታባ ከሙሳቪ ጋር ተገናኝተው ተቃውሟቸውን እንዲያቆሙ አሳስበዋቸዋል ሲሉ የኢራን ምንጮች የቢቢሲ የፋርስ ቋንቋ አገልግሎት ለሆነው ቢቢሲ ፐርሺያ ገልጸዋል።

ብዙዎች ሞጅታባ ከተሾሙ የአባታቸውን ጠንካራ ፖሊሲ እንደሚያስቀጥሉ ይጠብቃሉ። አንዳንዶች ደግሞ አባታቸውን፣ እናታቸውን እና ሚስታቸውን በአሜሪካ እና በእስራኤል ጥቃት ያጡ ሰው ለምዕራባውያን ጫና እንደማይንበረከኩ ያምናሉ።

የእስላማዊ ሪፐብሊክን ኅልውና ማረጋገጥ እና አገሪቱን ከፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውድቀት ለማዳን ትክክለኛው ሰው መሆናቸውን ለሕዝቡ ለማሳመን ከባድ ሥራ እንደሚጠብቃቸውም ይታመናል።

የአመራር ብቃታቸው ገና አልተፈተሸም። ከዚህ በተጨማሪ የሪፐብሊኩ ሥልጣን ወደ ውርስ ሥርዓት እየተለወጠ ነው የሚለው ግንዛቤ የሕዝብን ቅሬታ የበለጠ ሊያባብሰው ይችላል።

ሞጅታባ ከተመረጡ እስራኤል ዒላማ ይሆናሉ። የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር እንደተናገሩት ማንኛውም የአያቶላ ኻሜኒ ተተኪ "ዒላማቸው" ይሆናል።