የፌስቡክ ባለቤት ሜታ ልጆችን ለወሲባዊ ይዝቶች በማጋለጥ 375 ሚሊየን ዶላር ተፈረደበት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ ኒው ሜክሲኮ ግዛት ውስጥ የሚገኝ ፍርድ ቤት የፌስቡክ ባለቤት የሆነው ሜታ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮቹ ለልጆች ምን ያህል ደኅንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን በተመለከተ አሳሳች መረጃ ሰጥቷል በሚል 375 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት ጣለበት።
የፌስ ቡክ፣ የኢንስታግራም እና የዋትስአፕ ባለቤት የሆነው ሜታ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮቹ ሕጻናትን ለወሲባዊ ይዝቶች እንዲሁም ለወሲብ አዳኞች ተጋላጭ በማድረግ ተጠያቂ መሆኑን ዳኞች አረጋግጠዋል።
የኒው ሜክሲኮ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ራውል ቶሬዝ እንዳሉት የፍርድ ቤቱ ውሳኔ "ታሪካዊ" እና በሕጻናት ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ግዛቲቱ በሜታ ላይ ባቀረበችው ክስ ስኬታማ ሆናለች ብለዋል።
በሊቀመንበሩ እና በዋና ሥራ አስፈጻሚው ማርክ ዘካርበርግ በመመራት የሜታ ቃል አቀባይ እንደተናገሩት ኩባንያቸው በፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንደማይስማማ እና ይግባኝ እንደሚጠይቅ አሳውቀዋል።
ጉዳዩን የተመለከተው የዳኞቹ ቡድን ሜታ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮቹ የወጣት ተጠቃሚዎችን ደኅንነት በመጠበቅ በኩል ስላላቸው አስተማማኝነት ለሕብረተሰቡ አሳሳች መረጃ በመስጠት የኒው ሜክሲኮን ሕግን ጥሷል ብለዋል።
ክሱ በተሰማባቸው ባለፉት ሰባት ሳምንታት ለዳኞቹ የሜታ ውስጣዊ ሰነዶች የቀረቡ ሲሆን፣ የቀድሞ የኩባንያው ሠራተኞች ተቋሙ ሕጻናትን ለወሲብ የሚያድኑ ሰዎች መድረኮቹን ይጠቀሙበት እንደነበረ እንደሚያውቅ ምስክርነት ሰጥተዋል።
የግዛቲቱ ዐቃቢያነ ሕጎች የሜታን ውስጣዊ ጥናትን በመጥቀስ በአንድ ሳምንት ውስጥ ከኢንስታግራም ተጠቃሚዎች መካከል 16 በመቶ የሚሆኑት ያልተፈለጉ የእርቃን ምሥሎች ወይም የወሲብ ድርጊቶችን እንዲያዩ መደረጋቸውን ሪፖርት አድርገዋል።
ሜታ በበኩሉ በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮቹ ላይ ተጠቃሚዎች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመከላከል እና የታዳጊዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ለዓመታት ሲሠራ መቆየቱን ገልጿል።
በ2024 ኢንስታግራም ታዳጊዎች አጠቃቀማቸውን ለመቆጣጠር የሚያግዛቸውን የተለየ አካውንት ያቀረበ ሲሆን፣ ባለፈው ወር ደግሞ ልጆች በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ራስን መጉዳትን የሚመለከቱ ይዘቶች እየፈለጉ መሆናቸውን ለወላጆች የሚጠቁም ዘዴን አቅርቧል።
ሜታ የቀረበበትን ክስ ተከትሎ እንዲከፍል የተጣለበት 375 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት በዳኞቹ የተሰላው ተፈጽመዋል የሚባሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ጥሰቶች ላይ አስከ አምስት ሺህ ዶላር የሚደርስ ቅጣት በመጣል ነው።
በተመሳሳይ ሜታ ሎስ አንጀለስ ውስጥ ሌላ ክስ ቀርቦበት በፍርድ ቤት እየታየ ነው። አንዲት ወጣት የጉግል ንብረት የሆነውን ዩቲዩብን ጨምሮ ኢንስታግራም እና ሌሎች የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች በዘረጉት አሠራር ምክንያት ከልጅነቷ አንስቶ ሱሰኛ እንደሆነች ክስ አቅርባለች።
ይህንን የመሳሰሉ በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ባለቤቶች ላይ የቀረቡ በሺዎች የሚቆጠሩ ክሶች ወደ ተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ፍርድ ቤቶች እየቀረቡ ነው።
በአውሮፓውያኑ 2023 ኒው ሜክሲኮ ግዛት ሜታ ታዳጊዎችን ወደ ወሲባዊ ይዘቶች በመምራት እና ለወሲብ ዝውውር በማጋለጥ ክስ መሥርቶበት ነበር።
አንድ የሜታ የቀድሞ ሠራተኛ ለፍርድ ቤት በሰጠው ምስክርነት ላይ "የሜታ ባለሥልጣናት ይዘቶቻቸው ልጆችን እየጎዱ መሆናቸውን ያውቃሉ፤ ከሠራተኞቻቸው የሚቀርቡ ማስጠንቀቂያዎችን ችላ በማለት እና ሕብረተሰቡን ስለሚያውቁት ጉዳይ ዋሽተዋል" ሲል ወቅሷል።















