አምነስቲ፤ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት ሴቶችን "በወሲብ ባርነት" ይዘዋል እና "በቡድን ደፍረዋል" ሲል ከሰሰ

ፊቷን በእጇ የሸፈነች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት በሴቶች እና ሴት ልጆች ላይ "የወሲብ ባርነት" እንዲሁም "በቡድን መድፈርን" ጨምሮ የተለያዩ ወሲባዊ ጥቃቶችን ፈጽመዋል ሲል አዲስ ባወጣው ሪፖርት ከሰሰ።

የታጣቂ ቡድኑ አባላት በሴቶች ላይ የፈጸሟቸው ፆታዊ ጥቃቶች፣ ከፍርድ ውጪ የሆነ ግድያ እና የንጹኃንን ንብረት የማውደም ድርጊቶች "በጦር ወንጀልነት ሊፈረጁ የሚችሉ" እንደሆነ አስታውቋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዛሬ አርብ የካቲት27/2018 ዓ.ም. ይፋ የደረገው የምርመራ ሪፖርት፤ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱት የታጣቂ ቡድኑ አባላት ከአውሮፓውያኑ 2020 እስከ 2024 ባሉት ዓመታት የፈጸሟቸውን ድርጊቶች የዳሰሰ ነው። ምርመራው የተደረገው በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ውስጥ በሚገኙት ሳዮ እና አንፊሎ ወረዳዎች ውስጥ እንደሆነ ገልጿል።

የሰብአዊ መብቶች ተቋሙ ምርመራውን ሲያከናውን በቡድኑ አባላት ወሲባዊ ጥቃት ለተፈጸመባቸው 10 ሴቶች ቃለ መጠይቅ ማድረጉን እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችን ማነጋገሩን እና የሕክምና መዝገቦችን መመርመሩን አስረድቷል። በምርመራው ከተካተቱ ሴቶች መካከል ሰባቱ ጥቃት በተፈጸመባቸው ወቅት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች እንደነበረም አክሏል።

በ2011 ዓ.ም. የተጀመረው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሠ) እና የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ግጭት "ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለው በሲቪሉ ሕዝብ ላይ" እንደሆነ አምነስቲ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ ላይ ጠቅሷል።

የድርጅቱ የምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ሪጅናል ዳይሬክተር ቲጌሬ ቻጉታህ፤ "ለሰባት ዓመታት ያህል ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያሉ ታጣቂዎች በኮሚዩኒኬሽን እና በመገናኛ ብዙኃን መገደብ ምክንያት በተፈጠረው የጨለማ ሽፋን [ስር ሆነው] ንጹኃንን ለከፍተኛ ስቃይ ዳርገዋል" ብለዋል።

የአምነስቲ ሪፖርት እንደሚያስረዳው፤ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው 10 ሴቶች መካከል አምስቱ "ለወሲብ ባርነት" ተዳርገው ነበር። ሪፖርቱ፤ "ዘጠኙ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል፤ አንዷ ደግሞ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወታደርም እና በኦነሠ ታጣቂዎችም ጥቃት ደርሶባታል" ይላል።

በማሳያነት ተጠቀሰች አንዲት እናት እና በወቅቱ 12 ዓመቷ የነበረችው ልጇ ሦስት ሳምንት ለሚሆን ጊዜ ዋሻ ውስጥ እጃቸው ከዛፍ ጋር ታስሮ "በበርካታ የኦነሠ ወንዶች መደፈራቸውን" እንደተናገረች መግለጫው ላይ ሰፍሯል።

ወሲባዊ ጥቃት የተፈጸመባት እናት "ለሦስት ሳምንታት ያህል 15 ወንዶች እኔን እና ልጄን ይደፍሩን ነበር። ይፈራረቁብን ነበር" ማለቷን አምነስቲ በሪፖርቱ ገልጿል። በ2017 ዓ.ም. "በኦነሠ ተዋጊዎች በወሲብ ባርነት ተይዛ" የነበረች ሌላ ሴት የደረሰባት ሰቆቃም በሪፖርቱ ላይ በማሳያነት ተጠቅሷል።

እንደ አምነስቲ ገለጻ፤ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች "ባሎቻቸው፣ ወንድሞቻቸው ወይም አባቶቻቸው" የመንግሥት የፀጥታ ኃይል አባል በመሆናቸው ምክንያት የታጣቂ ቡድኑ አባላት "በበቀል እንደደፈሯቸው" ተናግረዋል።

"ከፆታዊ ጥቃቱ በኋላ ቤታቸውን ለቅቀው እንዲሄዱ እንደተገደዱ" እንዲሁም ይህንን ያላደረጉት ቤታቸው እንደተቃጠለ ሪፖርቱ አመልክቷል። ሁለት ሴቶች ወንድ ዘመዶቻቸው በታጣቂዎቹ እንደተገደሉ ተናግረዋል ተብሏል።

መሣሪያ የያዘ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ወሲባዊ ጥቃት እና ከባድ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል የተባሉት ሴቶች አሁንም ቢሆን "በኦነሠ ተዋጊዎች እና በባለሥልጣናት የበቀል እርምጃ እንደሚወሰድባቸው በመስጋት እና ከወሲባዊ ጥቃት ጋር ተያይዞ በሚመጣው መገለል የተነሳ" የሕክምና አገልግሎት እንዳላገኙ ተገልጿል።

የተቋሙ የምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ሪጅናል ዳይሬክተር ቲጌሬ ቻጉታህ፤ "እነዚህ ተደጋጋሚ በደሎች አሰቃቂ ብቻ አይደሉም፤ የጦር ወንጀል ሊሆኑ ይችላሉ" ብለዋል።

አምነስቲ የሰነዳቸው እነዚህ ግፎች የተፈጸሙት "ተጠያቂነት በሌለበት ከባቢ" ውስጥ እንደሆነ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ መንግሥት በአካባቢው የግንኙነት መስመሮችን ማቋረጡም ድርጊቶቹ እንዲፈጸሙ አስተዋጾ ማድረጉን ተናግረዋል።

"የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በቀውስ ጊዜያት ሳንሱርን ተግባራዊ ወደ ማድረግ ሲመለሱ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። ሙሉው ምሥል ከዚህም የከፋ ሊሆን ይችላል" ብለዋል።

"በሲቪሎች፣ በተለይም በሴቶች እና በልጃገረዶች ላይ የሚፈጸመው የበደል አዙሪት ማብቃት አለበት" ያሉት ቻጉታህ፤ "ዓለም አቀፍ እና የአፍሪካ የመብት ተከታታዮች" ድምጻቸው እንዲያሰሙ ጠይቀዋል።

"የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ወንጀለኞች ተጠያቂ ማድረግ እንዲሁም ለተጎጂዎች እና የጥቃት ሰለባዎች ፍትሕ እንዲሁም መፍትሔ ማቅረብን ዓላማው ያደረገ አስቸኳይ፣ ገለልተኛ እና ጥልቅ ምርመራ እንዲያጀምሩ መጠየቅ አለባቸው" ብለዋል።

በምርመራው የተካተቱ ሴቶችም በሚፈጸሙት "ጥቃቶቹ እንዲቆሙ እንዲሁም ፍትሕ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን" እንደጠየቁ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

የሰብአዊ መብቶች ተቋሙ ሪጅናል ዳይሬክተር፤ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትም እንደ "ወሲባዊ ጥቃትን፣ ሌሎች የስቅይት ድርጊቶችን፣ ግድያን፣ የግዳጅ መፈናቀል" ያሉ ድርጊቶችን የፈጸሙ አባላቱ ላይ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርበዋል።

መሣሪያ የያዘ ሰው

የፎቶው ባለመብት, AFP

የታጣቂ ቡድኑ አመራሮች፤ እነዚህን እና "ሌሎች በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ወንጀል የሆኑ ተግባራትን የፈጸሙ ታጣቂዎችን እና/ወይም አሃዶችን ትጥቅ ማስፈታት እና ማሰናበት አለባቸው" ብለዋል።

ታጣቂዎቻቸው "ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግን እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግን እንዲያከብሩ በአስቸኳይ ትዕዛዝ እንዲሰጡም" አሳስበዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን የተመለከተው ይህ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት ይፋ የሆነው፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ታጣቂ ቡድኑ በኦሮሚያ ክልል አርሶ ዞን "ቁጥራቸው በውል ያልተለዩ" ሰዎችን መግደሉን የሚገልጽ መግለጫ ባወጣ በቀናት ልዩነት ነው።

ኢሰመኮ ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ ታጣቂ ቡድኑ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በፈጸመው ጥቃት "የሕይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳት፣ እገታ እንዲሁም መፈናቀል" መድረሱን እንዳረጋገጠ አስታውቆ ነበር።

ኢሰመኮ ይህንን ከማለቱ አስቀድሞ በአካባቢው የተፈጸመው ግድያ በተመለከተ መግለጫ ያወጣው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ግን "በአርሲ ዞን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ ለደረሰው እልቂት" ተጠያቂ ያደረገው በመንግሥት ተሰማርተዋል ያላቸውን "ተላላኪዎች" ነው።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የወጣውን ሪፖርት በተመለከተ አርብ የካቲት 27/2018 ዓ.ም. ምሽት ላይ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥቷል።

የታጣቂ ቡድኑ ዋና አዛዥ አማካሪ የሆኑት ጅሬኛ ጉደታ በሰብአዊ መብቶች ድርጅቱ በአባላቱ ላይ የቀረበውን ክስ "መሠረት አልባ ነው" ሲሉ ውድቅ አድርገዋል።

"ለፕሮፓጋንዳ ሲባል የተሠራ ነው የሚመስለው። ለምን አሁን? ለምን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ብቻ? ለምን በምዕራብ ኦሮሚያ ብቻ? የሚሉ ጥያቄዎች ያጭራል" ብለዋል።

ወሲባዊ ጥቃት የጦር ወንጀል መሆኑን ጠቅሰው "አድሏዊነት ያለው አካል ሳያጠናው ወንጀሉን ለኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መስጠት በራሱ ወንጀል ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥተዋል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ "እኛን አላነጋገረንም" ያሉት አማካሪው ድርጊቱን የፈጸመው "ማን እንደሆነ ብናውቅ እርምጃ መውሰድ እንችላለን" ሲሉም ገልጸዋል።

ጨምረውም በሪፖርቱ ውስጥ "የተሳሳቱ" ነጥቦች በማለት "ጃል ገመቹ አቦዬ የምዕራብ ዕዝ ኮማንደር ሆኖ አያውቅም። የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ሀርሰዴ ከተቋቋመ በኋላ ኮማንዶቹ ስምንት ናቸው እንጂ አምስት አይደሉም" በማለት ተናግረዋል።

የተጎጂዎች ምስክርነት እና የሕክምና ማስረጃዎችን አምነስቲ ማቅረቡን በመጥቀስ እነዚህ በሠራዊቱ እንዴት ተቀባይነት እንደማይኖራቸው ከቢቢሲ የተጠየቁት አማካሪው "የተጎዳ ሰው ሊኖር ይችላል። የሕክምና ማስረጃ ሊቀርብ ይችላል። ግን ተጎጂዎች በዳዮቹ የተናገሩትን ነው የሚያነሱት። የፀጉር 'ስታይል' ላይ ተመርኩዘው ነው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ነው ያሉት እንጂ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መሆኑን በምን ያውቃሉ?" ብለው ተከራክረዋል።

"ኦሮሚያ ውስጥ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን በማስመሰል ወንጀል ይሠራል" ያሉት አማካሪው አቶ ጅሬኛ "ድምዳሜ ላይ ከመደረሱ በፊት ጥናት" ይቀድማል ሲሉ የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለዋል።

አምነስቲ ባወጣው በዚህኛው ሪፖርት ላይ "የገለልተኛነት" እና "ተዓማኒነት" ጥያቄ ያነሱት ጅሬኛ፤ "መንግሥት እንዲመርምር ይጠይቃል። ወንጀለኛ የሆነ፣ ከእኛ ጋር የሚፋለም አካል ተመልሶ የራሱን ወንጀል እንዲያጠና" መደረጉን ጠቅሰዋል።

የሠራዊቱ አባላት የቀረበባቸውን የወሲባዊ ጥቃት ክስ አለመፈጸማቸውን በምን እርግጠኛ እንደሆኑ ለቀረበላቸው ጥያቄ "የምናሠለጥነው፣ የምናስተምረው፣ የምናስታጥቀው እንዲህ ዓይነት ወንጀል እንዲፈጽም ሳይሆን አገር ነጻ እንዲያወጣ፣ ሕዝብን ከጭቆና እንዲያወጣ ነው" ብለው መልሰዋል።

ይህንን ወንጀል የፈጸመ የሠራዊቱ አባል ላይ "በሕጋችን መሠረት ከባድ ቅጣት" እንደሚጣል ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም "እርምጃ የተወሰደባቸው" እንዳሉ ቢገልጹም ዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል።

በሪፖርቱ በስም የተጠቀሱ ኮማንደሮችን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አነጋግሮ እንደሆነ ተጠይቀው ድርጊቱ "በእኛ ሠራዊት በፍጹም ሊከናወን፣ ሊደርግ የማይችል ነው" በሚል አስተባብለዋል።