ኢራን በእስራኤል የኒውክሌር ተቋም አቅራቢያ ጥቃት ፈጸመች

የፎቶው ባለመብት, Maxar
ኢራን በደቡብ እስራኤል በዲሞና ከተማ በሚገኘው የኒውክሌር ተቋም አቅራቢያ የሚሳዔል ጥቃት ፈጸመች።
ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (አይኤኢኤ) ከዲሞና ከተማ 13 ኪሜ ርቀት ላይ በሚገኘው የኒውክሌር ምርምር ተቋም ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ መረጃ እንደሌለው ገልጿል።
ጥቃቱ ቅዳሜ ዕለት በኢራን ናታንዝ የኒውክሌር ተቋም ላይ ለደረሰው ጥቃት ምላሽ እንደሆነ የኢራን የመንግሥት ቴሌቪዥን ዘግቧል። "ከዚያ ክስተት በኋላ ከጣቢያው ውጭ የጨረር መጠን መጨመር ሪፖርት አልተደረገም" ብሏል አይኤኢኤ።
የአይኤኢኤ ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮስ "በተለይም በኒውክሌር ተቋማት አቅራቢያ ከፍተኛ ወታደራዊ ጥንቃቄ መደረግ አለበት" ብለዋል።
የእስራኤል የአምቡላንስ አገልግሎት በዲሞና በተፈጸመው ጥቃት 40 ሰዎች ሕክምና እያገኙ መሆኑን ገልጿል። ከእነዚህ መካከል 37ቱ ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን የ10 ዓመት ልጅ በአስጊ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ነው ብሏል።
በቅርብ ርቀት በምትገኘው አራድ ከተማ በተፈጸመ ሌላ ጥቃት 68 ሰዎች ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጿል። ከእነዚህም ውስጥ 47ቱ ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን 10ቱ ደግሞ አስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ሲል አሳውቋል።
"ይህ በጣም ከባድ ሁኔታ ነው" ሲል የአስቸኳይ የሕክምና ባለሙያው ያኪር ታልካር በአራድን ስለተፈጸመው ጥቃት ገልጸዋል። "ብዙዎች ቆስለዋል፤ የተለያየ ጉዳት የደረሰባቸውም አሉ" ብለዋል።
የእስራኤል ባለሥልጣናት ሚሳዒሎቹ በአየር መከላከያ ስርዓቶችን እንዴት ሊያመልጡ እንደቻሉ እየመረመሩ ነው።
"በዲሞናም ሆነ በአራድ ጥቃቶቹን ለማስቆም ያልቻሉ የሚሳዔል መከላከያዎች ተተኩሰዋል። በዚህም በመቶዎች ኪሎ ግራም በሚመዝኑ ሁለት የባለስቲክ ሚሳዔሎች ሁለት ቀጥተኛ ድብደባዎች ደርሷል" ሲሉ የእስራኤል የእሳት አደጋ ተከላካዮች ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በኔጌቭ በረሃ ውስጥ የሚገኘው የሺሞን ፔሬዝ ኔጌቭ የኒውክሌር ምርምር ማዕከል "ዲሞና ሬአክተር" በመባል ይታወቃል። የእስራኤልን ይፋ ያልተደረገ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንደያዘ መታመን ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል።
በይፋ የሚነገረው ጣቢያው በምርምር ላይ ብቻ ያተኮረ እንደሆነ ነው። ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት ያህል በሥልጣን ላይ የነበረው መንግሥት በጉዳዩ ዙሪያ አሻሚ አቋም ቢይዝም፤ እስራኤል የኒውክሌር ቦምብ መሥራቷ የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ ቆይቷል።
ይህም ማለት እስራኤልን በመካከለኛው ምሥራቅ ብቸኛዋ የኒውክሌር መሣሪያ ባለቤት ያደርጋታል ማለት ነው። ስለዚህ አካባቢው ዒላማ መደረጉ በእስራኤል በኩል በከፍተኛ ትኩረት እንዲታይ ያደርገዋል።
እስራኤልም ሆነች አሜሪካ የጦርነቱ ዋና ዓላማ የኢራንን የኒውክሌር ቦምብ የማልማት ዕቅም ማስቀረት መሆኑን አስቀምጠዋል።
የኢራን የአቶሚክ ኢነርጂ ድርጅት በናታንዝ የተፈጸመውን ጥቃት የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች መስፋፋትን በተመለከተ የተደረሰውን ስምምነት የሚጥስ እንደሆነ ገልጾ፤ ምንም እንኳን "የራዲዮአክቲቭ ቁሶች ማፈትለካቸው ሪፖርት ባይደረግም በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ምንም ዓይነት አደጋ የለም" ብሏል።
ናታንዝ በየካቲት 21 በተቀሰቀሰው የጦርነቱ የመጀመሪያ ቀናትም ሆነ በሰኔ ወር ለ12 ቀናት በዘለቀው ጦርነት ወቅት ዒላማ ተደርጎ ነበር።
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ቅዳሜ ዕለት ናታንዝን በተመለከተ ለቀረበለት ጥያቄ በአካባቢው ጥቃት ስለመፈጸሙ እንደማያውቅ ተናግረዋል።















