በጋሞ ዞን መሬት መንሸራተት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 70 መድረሱ ተገለጸ

የሚያለቅሱ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Gamo Zone Communication

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ውስጥ በሦስት ወረዳዎች በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ እስከ ቀኑ ስምንት ሰዓት ድረስ የ70 ሰዎች አስከሬን መገኘቱን የክልሉ መንግሥታ አስታወቀ።

ቀን ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ፖሊስ ተጨማሪ 64 ሰዎች እስካሁን የደረሱበት አለመታወቁን እና ፍለጋ እየተካሄደ መሆኑን ገልጾ ነበር።

አመሻሽ ላይ መግለጫ የሰጡት የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ኃይለማሪያም ተስፋዬ፤ ቀኑ 8 ሰዓት ድረስ የ70 ሰዎች አስከሬን መገኘቱን እንዲሁም 3,480 ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ተናግረዋል።

የመሬት መንሸራተቱ በደረሰባቸው አካባቢዎች 90 የመኖሪያ ቤቶች እንደወደሙም ተገልጿል።

በጋሞ ዞን ሰሞኑን በተከሰተ የጎርፍ አደጋ ምክንያት የጠፉ ሰዎች ቁጥር በአጠቃላይ 128 መድረሱን የተናገረው የክልሉ ፖሊስ እስካሁን ባለው መረጃ የ64 ሰዎች አስክሬን መገኘቱን ተናገሮ ነበር።

የክልሉ ፖሊስ በጋሞ ዞን የመሬት መንሸራተት ከደረሰባቸው ሦስት ወረዳዎች መካከል ከባድ አደጋ ያስተናገደው የጋጮ ባባ ወረዳ ማዞ ዶይሳ ቀበሌ መሆኑን ገልጾ እስካሁን የ59 ሰው አስክሬን መገኘቱን ገልጿል።

ቀሪ አምስቱ አሴክሬኖች በቦንኬና ከምባ ዙሪያ ወረዳ የተገኙ መሆናቸውን የክልሉ ፖሊስ ለቢቢሲ ጨምሮ ገልጿል።

በዞኑ ለሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነው የመሬት መንሸራተት ያጋጠመው ከካቲት 30 ጀምሮ እስከ መጋቢት 2/2018 ዓ.ም. የጣለውን ዝናብ ተከትሎ ነው።

የዞኑ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ መጋቢት 2 2018 ዓ.ም. በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ባጋራው መረጃ በጋጮ ባባ ወረዳ ማዞ ዶይሳ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት ሕይወታቸው ካለፈ 52 ሰዎች በተጨማሪ እስካሁን የደረሱበት ያልታወቀ 50 ሰዎችን የመፈለግ ጥረቱ መቀጠሉን አስታውቆ ነበር።

የክልሉ ፖሊስ ዛሬ ማለዳ ባጋራው አዲስ መረጃ በዞኑ አደጋ ባጋጠመባቸው አካባቢዎች መጥፋታቸው የተመዘገበ ሰዎች 128 መሆናቸውን አስታውቆ የ64 ሰዎች አስከሬን መገኘቱን ገልጿል።

የጋሞ ዞን የከተማና አስተዳደር ልዩ አማካሪ አቶ ተስፋጺዮን ዘነበ በዞኑ ደጋማ አካባቢዎች በጣለው "ወቅቱን ያልጠበቀ ከፍተኛ ዝናብ" የመሬት ናዳው መከሰቱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የመሬት ናዳው የደረሰው መጋቢት 1 2018 ዓ.ም. "ከእኩለ ለሊት በኋላ ነው" ያሉት አቶ ተስፋጺዮን "ባልተለመደ እና ባልተጠበቀ መንገድ ከፍ ያለ ዝናብ ይጥል ነበር" ሲሉ ሁኔታውን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ኃላፊው አክለውም በአካባቢው ይጥል የነበረው ዝናብ ረቡዕ መጋቢት 2 2018 ዓ.ም. ማለዳ ድረስ መቀጠሉን እና ይህም ሁኔታውን አስቸጋሪ ማድረጉን ተናግረዋል።

አቶ ተስፋጺዮን የ52 ሰዎች አስከሬን ከናዳው ውስጥ በቁፋሮ መውጣቱን ገልጸው የ50 ሰዎች ፍለጋ ቀጥሏል ብለዋል።

በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Gamo Zone Comm.

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዞኑ በርካታ ተዳፋት ቦታዎች እንደሚገኙ የገለፁት አቶ ተስፋጺዮን፣ አሁን የመሬት ናዳው በደረሰበት ስፍራ ግን ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት አደጋ ደርሶ እንደማያውቅ ተናግረዋል።

በዞኑ የመሬት ናዳ ይከሰትባቸዋል ተብለው በጥናት በተለዩ አካባቢዎች ነዋሪዎችን የማንሳት እና ወደ ሌላ ቦታ ወስዶ የማስፈር ስራዎች መሰራታቸውን የተናገሩት አቶ ተስፋጺዮን "ይህ አካባቢ ግን ከዚህ ዓይነት ግምት እና ስጋት ነጻ ስለነበር" ምንም ዓይነት እርምጃ አለመወሰዱን አስረድተዋል።

በጋሞ ዞን የጣለን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተ ከባድ ጎርፍ እና የመሬት ናዳ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተሰግቷል።

የዞኑ ባለሥልጣናት በአደጋው የጠፉ 64 ሰዎችን የመፈለግ ጥረቱ አሁንም መቀጠሉ የገለጹ ሲሆን፣ በሕይወት ለተረፉትም እርዳታ የማሰባሰብ ሂደት ተጀምሯል።

ከባዱ አደጋው የደረሰው ከከባድ ዝናብ በኋላ ባጋጠመ የመሬት መንሸራተት ሲሆን፣ አካባቢው ተዳፋት በመሆኑ የሕይወት አድን ሥራውን ከባድ አድርጎታል።

አደጋው በተከሰተበት ሥፍራው የዞኑ ዋና አስተዳዳሪን ጨምሮ የፌደራል እና የክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተገኝተው በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ሰዎችን አጽናንተዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኘው የጋሞ ዞን በተደጋጋሚ በከባድ ዝናብ እና በጎርፍ ከሚጠቁ የአገሪቱ አካባቢዎች መካከል አንዱ ነው።

በ2016 ዓ.ም. በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተው ተመሳሳይ የመሬት መንሸራተት ከ200 ሰዎች በላይ መሞታቸው ይታወሳል።

በደቡብ ኢትዮጵያ የመሬት መንሸራተት እና የጎርፍ አደጋዎች የሚከሰቱ ሲሆን፣ በ2016 ከባድ ዝናብ ባሰከተለው የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ሕይታቸውን አጥተዋል።