በኬንያ የጨቅላ ሕጻናትን ጨምሮ የበርካታ ሰዎች አስከሬንን የያዘ የጅምላ መቃብር ተገኘ

ነጭ ጋወን የለበሱ ሰዎች አስከሬኖቹን ሲያወጡ
የምስሉ መግለጫ, የተወሰኑት አስከሬኖች በአቅራቢያው ከሚገኝ ካውንቲ ሆስፒታል የመጣ እነደሆነ ተገልጿል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በምዕራብ ኬንያ ኬሪቾ ከተማ ውስጥ ሕጻናትን ጨምሮ የ32 ሰዎች አስከሬንን የያዘ የጅምላ መቃብር ተገኘ።

ፖሊስ መጀመሪያ በስፍራው እንደተቀበሩ የተጠረጠሩ የ14 ሰዎች አስከሬንን ለማውጣት የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ካገኘ በኋላ ቁፋሮ ሲያካሂድ ተጨማሪ ሟቾችን ማግኘቱ ተገልጿል።

የአስከሬን ምርመራ ባለሙያ የሆኑት ሪቻርድ ንጆሮጌ ማክሰኞ ምሽት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "በከረጢቶች ውስጥ የተሞሉ አስከሬኖች" ማግኘታቸውን ጠቅሰው "በጣም ያልተለመደ" ሲሉ ገልጸውታል።

ረቡዕ ዕለት አስከሬኖቹን በፍጥነት ለመለየት እና የሞቱበት ሁኔታን ለማወቅ ምርመራ እንደሚጀመር ተገልጿል።

ንጆሮጌ "ሰባት አዋቂዎች እና 25 ሕጻናት" መገኘታቸውን ገልጸው ሕጻናቱ ዕድሜያቸው ከጨቅላ ጀምሮ እስከ ሽል እንደሚገመት ተናግረዋል።

በጅምላ መቃብሩ ውስጥ በርካታ የሰውነት ክፍሎችም መገኘታቸውም ተገልጿል።

የአስከሬን ምርመራ ባለሙያው አክለውም አንዳንድ አስከሬኖች ከሆስፒታሎች እና ከሬሳ ማቆያ ክፍሎች የተገኙ ቢመስሉም፣ ይህ ከአስከሬን ምርመራ በኋላ እንደሚወሰን ተናግረዋል።

የአዋቂዎቹ አስከሬን በጣም የበሰበሰ መሆኑን እና የሕጻናቱ አስከሬን ግን የመበስበስ ደረጃው እምብዛም መሆኑን ገልጸው ይህም በጅምላ መቃብሩ ላይ የተገኙት አስከሬኖች በተለያዩ ጊዜያት መሞታቸውን ያመለክታል ብለዋል።

ማክሰኞ ዕለት የፖሊስ ወንጀል መርማሪዎች እና የፎረንሲክ ቡድኖች በስፍራው ተገኝተው የጅምላ መቃብሩን በመቆፈር አስከሬኖቹን ሲያወጡ ታይተዋል።

አንዳንድ አስከሬኖች ሳይበላሹ የተገኙ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ከፊል የአካል ክፍላቸው እና አጥንቶች በከረጢቶች ውስጥ ተገኝተዋል።

አንዳንድ የፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን አባላት አስከሬኖቹን ከጅምላ መቃብር ውስጥ ሲያወጡ በግልጽ ሲንቀጠቀጡ ተስተውለዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች የሚወጡትን አስከሬኖች ለማየት በስፍራው ተሰብስበው ነበር
የምስሉ መግለጫ, የአካባቢው ነዋሪዎች የሚወጡትን አስከሬኖች ለማየት በስፍራው ተሰብስበው ነበር
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የጅምላ መቃብሩ የተገኘው አንድ ግለሰብ ጥቆማ ከሰጠ በኋላ ሲሆን ፖሊስ ወዲያውኑ ምርመራ ማድረግ መጀመሩ ተገልጿል።

ሰኞ ዕለት የኬንያ ወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት (ዲሲአይ) የመጀመሪያ ደረጃ ግኝት በማለት ይፋ እንዳደረገው ከሆነ ባለፈው ሳምንት አርብ 13 ማንነታቸው ያልታወቁ አስከሬኖች በአጎራባች ኒያሚራ ካውንቲ ከሚገኝ ሆስፒታል ወጥተው ወደ ኬሪቾ ለቀብር ተወስደዋል።

ይሁን እንጂ ስለተገኙት ተጨማሪ አስከሬኖች እና የጅምላ መቃብሩ አሁንም ያልተመለሱ ጥያቄዎች መኖራቸው ተገልጿል።

አስከሬኖቹ የተቀበሩት በኬንያ ብሔራዊ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ባለቤትነት በተያዘው ስፍራ ሲሆን፣ ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ እስካሁን ድረስ አልታወቀም።

ምክር ቤቱ ከጅምላ መቃብሩ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ገልጿል።

የድርጅቱ አንድ ኃላፊ ለዴይሊ ኔሽን ድረ ገጽ እንደተናገሩት የቀብር ሥነ ሥርዓቱ የተፈፀመው ያለእነሱ ፈቃድ ሲሆን፣ የምክር ቤቱ ባለሥልጣናትንም በሁኔታው ተደናግጠዋል ብለዋል።

የኬንያ ወንጀል ምርመራ ቀደም ሲል የቀብር ሥነ ሥርዓቱ የተፈጸመበት ሁኔታ ላይ ሕገ ወጥ ድርጊቶች ስለመኖራቸው እያጣራ መሆኑን ተናግሯል።

ከኒያሚራ የመጣ የሕዝብ ጤና ጥበቃ ኃላፊ እና የመቃብር ስፍራ ጠባቂ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር መዋላቸው እና ሌሎችም ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነ ተዘግቧል።

የሰብዓዊ መብቶች ቡድን የሆነው 'ቮካል አፍሪካ' ስለ ጅምላ መቃብሩ መገኘት "የዚህን አሳዛኝ ሁኔታ ትክክለኛ የወንጀል ስፋት የሚያጋልጥ" መሆኑን ተናግሯል።

"የአስከሬኖቹ የአካል ክፍል መቆረጥ እና መለያየት በመገለጹ ግኝቱ ፈጣን፣ ግልጽ ምርመራ እና አገራዊ ተጠያቂነትን የሚጠይቅ የወንጀል ደረጃ መኖሩን ያመለክታል" ብሏል።

የኬንያ የሕግ ማኅበር ፕሬዝዳንት ፌይዝ ኦዲያምቦ በበኩላቸው "የተጎጂዎች ማንነትን መለየት በተቻለ ፍጥነት መከናወን አለበት" ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ የጅምላ መቃብር የተገኘው በ2023 በማሊንዲ የባሕር ዳርቻ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ ጫካ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ አስከሬኖች ከተገኙ በኋላ ሲሆን፣ ይህም በአገሪቱ ውስጥ ከአምልኮ ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ የጅምላ ሞቶች ሁሉ እጅግ የከፋው ነው።

ራሱን ፓስተር ብሎ የሚጠራው ፖል ማኬንዚ ሕጻናትን ጨምሮ የ429 ሰዎች አስከሬን በጅምላ መቃብሮች ውስጥ ከተገኘ በኋላ በቁጥጥር ስር ውሏል።

ግለሰቡ ተከታዮቹን በረሃብ ራሳቸውን እንዲገድሉ አዝዟል ተብሎ ቢከሰስም እርሱ ግን ክዶ ተከራክሯል።