የአሜሪ አቃቤ ሕግ፤ የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት 'የዘረፉትን' የሕዝብ ሀብት ተጠቅመው ሊከራከሩ አይገባም ሲል ተቃወመ

የቀድሞው የቬንዙዌላን መሪ ኒኮላስ ማዱሮ እና ባለቤታቸው ሲሊያ ፍሎሬስ የሕግ ሂደታቸውን ለመደገፍ የቬንዙዌላን መንግሥት ገንዘብ እንዲጠቀሙ ሊፈቀድላቸው ይገባል የሚለው ክርክር በፍርድ ቤት ታየ።
የማዱሮ እና የፍሎሬስ ጠበቆች ፍርድ ቤቱ የቀረበባቸውን የናርኮ ሽብርተኝነት ክስ ውድቅ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። በላቲን አሜሪካዋ አገር ላይ በተጣለው ማዕቀብ ምክንያት ገንዘቡን እንዳይጠቀሙ መከልከላቸውን በምክንያትነት አንስተዋል።
አቃቤ ሕጎች በበኩላቸው ማዱሮ የቬንዙዌላን ሐብት "ስለዘረፉ" ገንዘቡን ለሕግ ክፍያዎች መጠቀም የለባቸውም ሲሉ ተከራክረዋል።
የ92 ዓመቱ ዳኛ አልቪን ሄለርስቴይን "የመከላከል መብት ወሳኝ ነው" ብለዋል። በክርክሩ ምክንያት ጉዳዩን ውድቅ እንደማያደርጉም ተናግረዋል።
ዳኛው በሚቀጥለው የፍርድ ቤት ቀጠሮ ላይ ውሳኔ እንደሚሰጡ ገልጸዋል።
የአሜሪካ ኃይሎች ጥር 3 ካራካስ ወደ ሚገኘው የፕሬዝዳንቱ መኖሪያ በመግባት ማዱሮ እና ፍሎሬስ እንደወሰዱ፤ ኋላም በኒውዮርክ የጦር መሣሪያ እና የአደንዛዥ ዕፅ ክስ እንደተመሰረተባቸው ይታወሳል። ጥንዶቹ የቀረበባቸውን ክስ ውድቅ አድርገዋል።
ሐሙስ ዕለት ማዱሮ እና ባለቤታቸው አረንጓዴ ካኪ የእስር ቤት ልብስ ለብሰው፤ በመካከላቸው ከነበሩት በርካታ ጠበቆች ጋር በጸጥታ ተቀምጠው የክርክሩን ትርጉም በጆሮ ማዳመጫዎች ተከታትለዋል።
የትናንቱ ሂደት፤ ማዱሮ ታፍነው መወሰዳቸውን እና ንጹህ እንደሆኑ ለብዙ ደቂቃዎች ከተናገሩበት የመጀመሪያ የፍርድ ቤት ውሏቸው ፍጽም ተቃራኒ ነበር። ያለፈው ችሎት ሲጠናቀቅ ከፍርድ ቤቱ ጥግ የተቀመጠ ግለሰብ ማዱሮ ላይ ሲጮህ ተደምጧል።
ባል እና ሚስቶቹም እንዲሁም የቬንዙዌላ መንግስት በአሜሪካ ማዕቀብ ስለተጣለባቸው፤ የሕግ ክፍያቸውን በመንግሥት እንዲሸፈን ፈቃድ ማግኘት ይኖርባቸዋል።
የአሜሪካ የውጭ ሐብት ቁጥጥር ቢሮ መጀመሪያ ላይ ፈቃድ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ውሳኔውን ቀይሯል።
ሁለቱ ግለሰቦች የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት በመሆናቸው ምክንያት የቬንዙዌላ መንግሥትን ገንዘብ ማግኘት እንደማይችሉ እና ለጠበቆች ለመክፈል የሚያስችል በቂ ገንዘብ እንዳላቸው አቃቤ ህግ ተከራክሯል። ማዱሮ እና ባለቤታቸው ግን ይህንን ክደዋል።
በአሜሪካ ሕግ መሰረት ማዱሮ እንደማንኛውም ተከሳሽ ገንዘብ ከሌላቸው በፍርድ ቤት የተሾመ ጠበቃ የማግኘት መብት አላቸው።
ዳኛ ሄለርስቴይን፤ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የማዱሮ ጠበቃ ባሪ ፖላክን መከራከሪያ የደገፉ ይመስላል። የማዱሮ ጠበቃ፤ ክሱ በሌላ አገር ውስጥ የቀድሞው መሪ ላይ የተመሰረተ ክስ በመሆኑ ጉዳዩ በመንግሥት ከሚመደብ ጠበቃ በላይ እንደሚሆን እና ይህም ተከሳሹ የሚያገኘውን ድጋፍ ሊያሳንሰው እንደሚችል በመጥቀስ ተከራክሯል።
አቃቤ ህግ፤ ማዱሮ እና ባለቤታቸው የቬንዙዌላ መንግስትን ገንዘብ እንዲያገኙ በአሜሪካ መንግሥት እንዳልተፈቀደላቸው ተናግረዋል። አሜሪካ በማዱሮ አገዛዝ ወቅት በጣለችው የረጅም ጊዜ ማዕቀብ እና ጥንዶቹ "የቬንዙዌላውያንን ሀብት ለራሳቸው ጥቅም በመዝረፋቸው" ምክንያት መታገዳቸውን ገልጸዋል።
ዳኛ ሄለርስቴይን በበኩላቸው ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር በመዋላቸው ምክንያት የውጭ ፖሊሲው ሁኔታ ተቀይሯል ብለዋል።
"ከቬንዙዌላ ጋር በድጋሚ ግንኙነት ፈጥረናል" ብለዋል። ማዱሮ ከታሰሩ በኋላ የቀድሞዋ ምክትል ፕሬዝዳንት ዴልሲ ሮድሪጌዝ ስልጣኑን ተረክበዋል። አገሪቱም ከአሜሪካ ጋር የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን እንደገና መጀመሯን ተናግረዋል።
"የቬንዙዌላ መንግሥት ለመክፈል ፈቃደኛ ነው" ሲሉም አክለዋል።
የማዱሮ ጠበቆች ጉዳዩን ሙሉ በሙሉ ውድቅ እንዲደረግ ስለፈለጉ ዳኛው ጉዳዩን እንዴት መፍታት እንደሚችሉ ግራ ተጋብተው ነበር።
"መፍትሔው ምንድን ነው?" ሲሉ ዳኛው ሁለቱንም ወገኖች ደጋግመው ጠይቀዋል።
አሜሪካ ማዱሮን የከሰሰችው በናርኮ ሽብርተኝነት ሴራ፣ በኮኬይን ማሰራጨት እና የጦር መሣሪያዎችን በመያዝ ወንጀሎች ነው።
ማዱሮ እና ባለቤታቸው እስካሁን የዋስትና ጥያቄ ያላቀረቡ ሲሆን በብሩክሊን የፌዴራል ሜትሮፖሊታን እስር ቤት ታስረዋል። የቀጣይ የችሎት ቀን አልተወሰነም።
ሐሙስ ዕለት በዋሽንግተን በተካሄደው የካቢኔ ስብሰባ ላይ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው በማዱሮ ላይ ተጨማሪ ክሶችን ለማቅረብ እያጤነች መሆኑን ተናግረዋል። ማዱሮ "ፍትሃዊ ፍርድ" እንደሚያገኙም ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቬንዙዌላ ዋና ከተማ ካራካስ ነዋሪዎች የፍርድ ቤት ውሎውን በቅርበት እንደሚከታተሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጡረታ የወጡት የሕግ ባለሙያዋ አና ፓትሪሺያ የመንግስት ሳንሱር ቢኖርም ሁሉም ሰዉ ሂደቱን ለመከታተል እየሞከረ መሆኑን ገልጸዋል።
"የቬንዙዌላ ሚዲያዎች የሚያወጡትን ነገር መቆጣጠር ይችላሉ፣ ነገር ግን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን መቆጣጠር አይችሉም" ሲሉ ከየት መረጃ እንደሚያገኙ ጠቁመዋል።
የማዱሮ ዕጣ ፈንታን በተመለከተ በተወሰነ ደረጃ የሐዘን ስሜት እንዳላቸው አልሸሸጉም።
"እሱ ሁሉንም ነገር የነበረው፤ ነገር ግን በስግብግብነት እና በተጋነነ እኔነት ምክንያት የነበረውን ያጣ ሰው ነው። ሰው በመሆኑ አዝንለታለሁ። ለሠራቸው ወንጀሎች መጠየቅ ስላለበት ግን የዕድሜ ልክ እስራት እንደሚፈረድበት ተስፋ አደርጋለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።
በምዕራብ ካራካስ የሚኖሩት አጉስቲና ፓራ "ፕሬዚዳንቴ ማዱሮ ይለቀቃሉ" የሚል እምነት እንዳላቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
"ጉድለቶቹ ቢኖሩም፣ መጥፎ ፕሬዝዳንት አልነበረም። ንፁህ መሆኑን ያውቃል፤ ይህንንም ያረጋግጣል።"
የአሜሪካ መንግስት "በምን እንደሚከስሰው እንኳን አያውቅም" ብለዋል ፓራ።
"በዕፅ ዝውውር እና የጦር መሳሪያ በመያዝ ከሰውታል። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ብዙ ሰዎች በሞቱበት በቬንዙዌላ የሚፈጽሙትን መቀበል አልችልም" ሲሉ ተናግረዋል።















