ከእርጅና ጋር የሚመጡ የጤና ችግሮችን ለማስወገድ እና ጤናማ እርጅና እንዲኖረን ምን እናድርግ?

ስፖርት የሚሠሩ ሰዎች
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

የልብ ሐኪሙ ዶ/ር ኤሪክ ቶፖል የ98 ዓመቱን አዛውንት ወ/ሮ ኤልአር በነበራቸው ሕክምና ቀጠሮ ወቅት ሲያገኛቸው አንድ ነገር ትኩረቱን ሳበው።

ወደ ቀጠሯቸው ሲመጡ ያለምንም እርዳታ፣ ለብቻቸው መሆኑ ነበር ትኩረቱን የሳበው።

ወደ ሕክምና ማዕከሉ እንዴት እንደመጡ ሲጠይቃቸው "ራሴ እየነዳሁ ነው የመጣሁት" የሚል ቆፍጠን ያለ ምላሽ አገኘ።

"ለብቻዋ የምትኖር፣ እጅግ ባልተለመደ መልኩ ንቅት ያለች፣ በርካታ ማኅበራዊ ሕይወት ያላት፤ ነገር ግን ለብቻዋ መሆን የምትወድ ሴት መሆኗን ተረዳሁ" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ዶ/ር ቶፖል በአሜሪካ ስመ ጥር የሆነው የስክሪፕስ የምርምር ማዕከል መሥራች ሲሆን፣ ስሙን በተለያዩ ምርመሮች እና መጽሐፍትን በመጻፍ ተክሏል።

የቅርብ ጊዜ ሥራው ለምን አንዳንዶቻች ከሌሎች በተሻለ ጤነኛ እና ረዥም ዕድሜ ለመኖር እንደቻሉ የሚተነትን ነው።

ዶ/ር ቶፖል በሚነገሩ አፈ ታሪኮች እና የተሳሳቱ እምነቶች ሰዎች እንዳይታለሉ ያስጠነቅቃል።

"ምንም መረጃ የማይገኝባቸው እና የማያስረጁ የሚባሉ መድኃኒቶች፣ ሕክምናዎች እና ቴራፒዎች ያለምንም ሳይንሳዊ ድጋፍ እየተሰጡ ነው።"

"ምናልባት አንድ ቀን ያ ምትሃታዊ መድኃኒት ሊኖረን ይችላል። [በአግባቡ አንድናረጅ የሚያደርግ]፤ ነገር ግን አሁን ምንም የለንም። ለማግኘትም ቅርብ አይደለንም" ሲል አክሏል።

በአግባቡ ለማርጀት የሚያስችሉን ሳይንስ የሚደግፋቸው ምሥጢሮች ታድያ የትኞቹ ናቸው?

የዘረ መል ሚና

ጎን ለጎን የተቀመጡ እናት እና ልጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጥናቶች ከዚህ በፊት ይታመን ከነበረው በተቃራኒ ዘረመል ያለው አስተዋጽኦ አነስተኛ መሆኑን ደርሰውበታል

በአውሮፓውያኑ 2007 ዶ/ር ቶፖል እና ቡድኑ ምንም ዓይነት የጤና ችግር የሌለባቸውን፣ ዕድሜያቸው በ80ዎቹ ውስጥ እና ከዚያ በላይ የሆኑ 1,400 የሚጠጉ አሜሪካውያን ዘረ መል ለስድስት ዓመት ያህል ሲከታተሉ ቆይተዋል።

ዶ/ር ቶፖል "እነዚህን ለማግኘት በጣም አስቸጋሪ የሆኑ ሰዎች ናቸው፤ በከባድ ወይም ሥር በሰደደ በሽታ በጭራሽ ያልታመሙ፣ የረጅም ጊዜ መድኃኒት የማይወስዱ እና ዕድሜያቸው ከ85 በላይ የሆናቸው ናቸው" ብለዋል።

በዕድሜ የገፉት ወይንም ሱፐር ኤጀርስ በሚልየሚጠሯቸውን እነዚህ ሰዎች ሲያጠኑ፣ ቡድኑ ለምን ጤናማ እንደነበሩ ለማስረዳት በዘረ መል ውስጥ ያገኘው መልስ በጣም ጥቂት ነው።

ዶ/ር ቶፖል የ98 ዓመቷን ወይዘሮ ኤልአርን ያገኘው ያንን ጥናት ካሳተመ በኋላ ነው። ምንም እንኳ በጥናቱ ውስጥ የተካተተች ባይሆንም በአዲሱ መፍሐፉ ውስጥ ታሪኳ ተካትቷል።

የቤተሰብ አባላቷ በለጋ ዕድሜያቸው የሞቱ ቢሆንም እርሷ ግን እስከ ጤናዋ ያረጀች በመሆኑ በምሳሌነት ጠቅሷታል።

ዶ/ር ቶፖል "እነዚህ ሰዎች የማይታመን፣ ጤናማ የእርጅና ዘመን ላይ የደረሱ፣ እስከ መቶ ዓመት ዕድሜ ድረስ የኖሩ፣ 100 ዓመት የሞላቸው ሰዎች በአጠቃላይ በዘራቸው ውስጥ ተመሳሳይ ታሪክ የለም።"

"ምናልባት አንዳንድ የዘረ መል አካላት ሊኖሩ ይችላሉ፤ ግን ያ ዋነኛው ማብራሪያ አይደለም።"

"ዘረ መል ለጤናማ እርጅና ምክንያት ላይሆን ይችላል የሚለው ሃሳብ ያለጊዜው በመሞት እና ሥር የሰደደ በሽታ በቤተሰባቸው ታሪክ ውስጥ ለሚገኝ እፎይታን የሚሰጥ ነው" ሲሉ ዶክተር ቶፖል ይናገራሉ።

ነርስ የአዛውንቷን ወገብ ስትለካ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

'እርጅና ብቻህን ና'

ዶክተር ቶፖል ረዥም ዕድሜ የሚኖሩ አዛውንቶች በተለምዶ ከዕድሜ ጋር በተያያዘ በሚከሰቱ ስር የሰደዱ በሽታዎች የመጠቃት ዕድላቸው አነስተኛ መሆኑን በጥናታቸው ማረጋገጣቸውን ይናገራሉ።

የሰውነት መቆጣት እንደ ኢንፌክሽን እና መመረዝ ያለ ጉዳት በሚያጋጥምበት ወቅት የሰውነት ተፈጥሯዊ እና ጤናማ ምላሽ ነው።

በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ውስጥ በሚገኘው ጤናማ እርጅና ተቋም የምርምር ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ዴቪድ ጌምስ የሰውነት መቆጣት ለረጅም ጊዜ ሲቆይ የልብና የደም ሥር በሽታዎችን ጨምሮ ወደ ሌሎች ስር የሰደዱ ሕመሞች ሊያመራ ይችላል ብለዋል።

ይህ ሂደት ከዕድሜ ጋር የተያያዙ ሕመሞች (inflammageing) በመባል ይታወቃል ይላሉ።

"ሥር የሰደደ የሰውነት መቆጣት ችግር ለረዥም ጊዜ የሚቆይ፣ ሁልጊዜ እዚያ ያለ እና ትልቅ ሕመም የሚሆን ነው" ሲሉ ይገልጹታል።

አንዱ ጽንሰ ሃሳብ የዘመናዊው አኗኗራችን ያንን የሰውነት መቆጣት እየፈጠረው ነው የሚል ነው። ምክንያቱ ደግሞ ሰውነታችን በዝግመተ ለውጥ እና አሁን በምንኖርበት ሁኔታ መካከል ያለው አለመመጣጠን ነው።

ጌምስ "ሰውነታችን የተዋቀረው የምግብ እጥረት ባለበት ዓለም ነው። ሁልጊዜ ለትርፍ ምግብ የተሠራ አይደለም፤ በተለይ ከፍተኛ ቅባት ያላቸው እና የተጣራ ምግብ ይዘት ያላቸው ምርቶች።"

ፕሮፌሰር ጌምስ ከመጠን ያለፈ ውፍረት እንደ የስኳር፣ የመርሳት እና የልብ ችግር በሽታዎችን ከሚያስከትልበት አንደኛው መንገድ የሰውነት መቆጣት ነው ይላሉ።

የሰውነት መቆጣትን እንዴት መከላከል ይቻላል?

የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች በጠረጴዛ ላይ ተደርድረው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ለጤናማ እርጅና ቁልፍ ከሆኑ ነገሮች መካከል አንዱ ፍራፍሬዎች እና አትክልቶችን በመመገብ የሚገኝ ነው

አብዛኛዎቹ የዶክተር ቶፖል ምክሮች ብዙውን ጊዜ እንድንከተላቸው የምንበረታታውን የጤናማ አኗኗር መመሪያዎችን ያንፀባርቃሉ።

ብዙ ፍራፍሬዎችን እና አትክልቶች ያለው አመጋገብን ይመክራል።

በቂ እና ጥሩ እንቅልፍ ማግኘትም አስፈላጊ ነው።

"በእያንዳንዱ ምሽት በአንጎላችን ውስጥ የሚወገዱ ምርቶች፣ ሜታቦላይትስ አሉን፤ በእውነቱ መርዛማ እና የሰውነት መቆጣትን የሚያበረታቱ እና በቅርብ ዓመታት ውስጥ በተገኘ ግሊምፋቲክ ቻናል እየተባለ በሚጠራው በኩል ማጽዳት አለብን" ሲሉ ዶክተር ቶፖል ያብራራሉ።

የግሊምፋቲክ ቻናል እአአ በ2012 የታወቁ ሲሆን፣ ለአንጎል እንደ ቆሻሻ ማስወገጃ ሥርዓት ሆኖ እነዚህን ምርቶች በመተላለፊያ ሥርዓቶች በኩል ያጓጉዛል።

በኋላ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሥርዓቱ በምንተኛበት ወቅት የበለጠ ንቁ ነው።

"በቂ እንቅልፍ ካልወሰድን እነዚህን ቆሻሻዎች አናስወግድም፤ እና አእምሯችንን የሚያስቆጡበት ዕድል ያገኛሉ። ስለዚህ የነርቭ ሕመም አምጪ በሽታዎችን ለመከላከል ጥልቅ እንቅልፍ ለመተኛት የተሻለ ነገር ማድረግ አለብን" ሲሉ ይመክራሉ።

በእድሜ የገፋች ሴት ስፖርት ስትሰራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከባድ መሆን እንደሌለበት ዶ/ር ቶፖል ይመክራሉ፤ መንቀሳቀስ አስፈላጊ ነው ሲሉ አክለዋል

በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግንም ይመክራል።

ለቢቢሲ "መድኃኒቱ ቢሆን ኖሮ ካሉን ግኝቶች ሁሉ ትልቁ መድኃኒት ይሆን ነበር" ብለዋል።

ፈጣን የእግር ጉዞ ወይም ብስክሌት መጋለብ፣ የኤሮቢክ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለዚህ ምሳሌዎች ናቸው ብለዋል።

"ከባድ መሆን የለበትም፣ ቀጣይነት ያለው ማንኛውም እንቅስቃሴ ጠቃሚ ነው።"

ሁለት አረጋውያን ሴቶች ከአዛውንት ወንድ ጋር ቁጭ ብለው ሲጫወቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ማኅበራዊ ሕይወትን መጠበቅ ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ጠቃሚ ነው

ማኅበራዊ ግንኙነት እና መገለልን ማስወገድ ለአእምሮ መዳከም (ዲሜንሺያ) የመጋለጥ ዕድልን ዝቅ እደሚያደርግ ይናገራሉ፤ እርግጥ ነው ተመራማሪዎቹ በምን ያህል መጠን ለሚለው ወጥ መልስ የላቸውም።

የ2020 የላንሴት ጥናት ማኅበራዊ መገለልን ማስወገድ የዓለም አቀፍ የመርሳት በሽታ ሥርጭትን በ4 በመቶ እንደሚቀንስ ገምቷል።

ሌላው በሲድኒ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት ከአውስትራሊያን፣ ከሰሜን አሜሪካን፣ ከአውሮፓ፣ ከደቡብ አሜሪካ፣ ከእስያ እና ከአፍሪካ አገራት የተውጣጡ 13 ዓለም አቀፍ ጥናቶችን ውጤት የተነተነ ሲሆን፣ የትኛውን የማኅበራዊ መስተጋብር ዓይነት ትልቅ ውጤት እንዳለው ተመልክቷል።

"በየወሩ ወይም በየሳምንቱ ከቤተሰብ እና ከጓደኞች ጋር የሚኖር ተደጋጋሚ መስተጋብር በዲሜንሺያ የመያዝ ዕድልን እንደሚቀንስ እና በተጨማሪም ከሌሎች ጋር መኖር እና የማኅበረሰብ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ የመሞትን ዕድል እንደሚቀንስ ደርሰንበታል" ሲሉ በሲድኒ ዩኒቨርሲቲ ጥናት ውስጥ ከተሳተፉት መካከል አንዱ የሆኑት ዶክተር ሱራጅ ሳምታኒ ተናግረዋል።

ማኅበራዊ ግንኙነት በአንጎል ውስጥ የአልዛይመርስ በሽታን ተፅእኖ ለመቋቋም ይረዳል ተብሎ ይታሰባል። እንደ አልዛይመር ሶሳይቲ ዩኬ ከሆነ እንደ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያሉ ጤናማ ባህሪያትን፣ ውጥረትን እና የሰውነት መቆጣትን ለመቀነስ ይረዳሉ።

ዶክተር ቶፖል፣ ኤልአር ለዚህ ፍጹም ምሳሌ ነች ይላሉ።

"በጣም ተወዳጅነት አላት፤ ይህም ከብዙ ማኅበራዊ መስተጋብር ጋር አብሮ የሚሄድ ነው። ብዙ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች አሏት፤ ሠዓሊ ነች በዚህም ሽልማቶችን አግኝታለች።"

"ልንመኘው የሚገባን ይህ ነው፤ ጤናማ እርጅና።"

'ማርሽ ቀያሪው'

ዶ/ር ኤሪክ ቶፖል አካላዊ እንቅስቃሴ እየሰራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ኤሪክ ቶፖል

በተጨማሪም ወደፊት ዶክተሮች ከዕድሜ ጋር የተዛመዱ በሽታዎችን ለመተንበይ እና ለመከላከል ብዙ መረጃዎችን እንዲተነትኑ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ይረዳቸዋል ተብሎ ይታመናል።

ሌላው ቀርቶ አንድ ሰው በየትኛው ዕድሜ ላይ እነዚህን በሽታዎች ሊያዳብር እንደሚችል ለመተንበይ እና አስቀድሞ የአኗኗር ለውጦችን ለማድረግ ያግዛል።

"እኛ እየተነጋገርን ያለነው አንድ ጊዜ የልብ ድካም ካጋጠመህ በኋላ ሁለተኛውን ከመከላከል ይልቅ በሽታው ጭራሹኑ እንዳይከሰት መከላከል ላይ ነው" ይላል።

ዶ/ር ቶፖል ይህን የመሰለ የአደጋ ስጋት ትንተና እንደ "ማርሽ ቀያሪ" ሲገልጹት፤ ፕሮፌሰር ጌምስ ግን ምንም እንኳን እንደዚህ ዓይነት መረጃ ቢቀርብላቸውም ሰዎች በሕይወታቸው ላይ ጉልህ ለውጦችን እንዲያደርጉ መጠየቅ ምን ያህል ምክንያታዊ ነው ይላሉ።

"እንደዚያ ልትል ትችላለህ፤ ሁሉም ሰው በአግባቡ የማይመገበው ለምንድነው? ታውቃላችሁ፤ ትክክለኛ አመጋገብ ይኑራችሁ፤ ጤናማ ምግብ ተመገቡ፣ ወደ ስፖርት ማዘውተርያ ይሂዱ፤ ዱብ ዱብ ይበሉ ልንል እንችላለን። ነገር ግን አብዛኞቹ ሰዎች ይህን ለማድረግ ጊዜ አይኖራቸውም" ብለዋል።

"ምንም ዓይነት ፈጣን እና ቀላል መልስ ያለን አይመስለኝም።"