የእንጆሪ ጣዕም ያለው ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት በአፍሪካ ለሕፃናት መቅረብ ጀመረ
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተለያዩ የረድኤት ድርጅቶች የፀረ ኤችአይቪ ሕክምና (አንቲ-ሪትሮቫይራል ቴራፒ) መድኃኒት በሰባት የአፍሪካ አገራት ለሚገኙ ሕፃናት ለማከፋፈል አዲስ ፕሮጀክት ጀምረዋል።
ሕፃናት ዕለታዊ መድኃኒቶቹን እንዲወስዱ ለማበረታታት ደግሞ የሚዋጡት መድኃኒቶች ጣፋጭ የእንጆሪ ጣዕም እንዲኖራቸው ተደርጓል ተብሏል።
በየዕለቱ የሚዋጡት መድኃኒቶች መራራ በመሆናቸው ምክንያት በርካታ ሕፃናት መድኃኒቶቹን ለመውሰድ ፈቃደኛ አይሆኑም ነበር።
ጃኔት ጊናርድ በዓለም ዓቀፉ የጤና ኤጀንሲ ዩኒትኤድ የምትሠራ ሲሆን በመላው ዓለም እስከ 1.8 ሚሊየን የሚደርሱ ሕፃናት ኤችአይቪ በደማቸው እንዳለ ትገልጻለች።
"ከእነዚህ ሕፃናት መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ምንም አይነት ሕክምና አያገኙም። መድኃኒቶቹን የሚያገኙ ሕፃናት ደግሞ የሚሰጧቸው መድኃኒቶች በጣም መራራ በመሆናቸው ምክንያት አልያም የአዋቂዎች መድኃኒት ተሰባብሮ ስለሚሰጣቸው ለመውሰድ ፈቃደኞች አይደሉም'' ትላለች።
በዚህ ምክንያት ብቻ በየዓመቱ 100 ሺህ የሚሆኑ ሕፃናት ይሞታሉ።
የረድኤት ድርጅቶቹ ለማከፋፈል ያሰቡት መድኃኒት በእንጆሪ ጣዕም የተዘጋጀ ሲሆን፤ ያለ ምንም ችግር ሕፃናቱ ደስ ብሏቸው እንዲወስዱት ታስቦ ነው የተዘጋጀው።
ዓለም ዓቀፉ የጤና ኤጀንሲ ዩኒትኤድ ከክሊንተን ሄልዝ አክሰስ ኢኒሼቲቭ እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን እንዲሁም የተለያዩ መድኃኒት አምራቾች በጥምረት ይህንን መድኃኒት ለማዘጋጀት በማሰብ፣ በማምረትና በማከፋፈል ላይ መሳተፋቸውን ጃኔት ጊናርድ ትገልጻለች።
''ይህ መድኃኒት ሕክምናው ለሚያስፈልጋቸው ሕፃናት በትክክል መድረስ የሚችል ከሆነ ትልቅ ስኬት ነው።''
በእንጆሪ ጣዕም የተዘጋጁት መድኃኒቶች በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ለገበያ የቀረቡ ሲሆን፤ እስከ 100 ሺህ የሚደርሱ መድኃኒቶች ወደ አፍሪካ መድረስ ጀምረዋል።
መድኃኒቱ ከወዲሁ ወደ ናይጄሪያ፣ ማላዊ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ዚምባብዌ፣ ኬንያ እና ቤኒን ተወስዶ ጥቅም ላይ መዋል መጀመሩንም ጃኔት ጊናርድ ገልጻለች።
"ከዚህ በፊት እንዲህ አይነት መድኃኒቶችን ለማሰራጨት ዓመታት ይፈጅብን ነበረ። አሁን ግን ከሌላ ጊዜው በአምስት እጥፍ ፍጥነት መድኃኒቶቹ እየተከፋፈሉ ነው። የሳምንታት እድሜ ላላቸው ሕፃናት የሚሆን መድኃኒት እስካሁን ድረስ አልነበረም። አሁን ግን ይህ ችግርም ተቀርፏል። የአዋቂዎችን መድኃኒት ፈጭተን ለሕፃናት መስጠት አይጠበቅብንም። አሁን ለእነሱ የሚሆን መድኃኒት ተገኝቷል።"
መድኃኒቶቹ ዋጋቸው ከዚህ በፊት ከነበሩት ከግማሽ በላይ የሚቀነስ እንደሆነ ጃኔት ጊናርድ ገልጻለች።
ከዚህ ቀደም 500 ዶላር በዓመት ያስወጣ የነበረው የፀረ ኤችአይቪ ጥምር ሕክምና (አንቲ-ሪትሮቫይራል ቴራፒ) መድኃኒት በአዲሱ ዋጋ መሠረት በዓመት ወደ 120 ዶላር ወርዷል።
እንዳያመልጥዎ
ከየፈርጁ
በስፋት የተነበቡ
የሚፈልጉት ይዘት የለም