ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ እና ኢራን አሸናፊነታቸውን ያወጁበት ጦርነት ምን አስከተለ?
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመጨረሻ ያሉት ገደብ ከመጠናቀቁ ከ90 ደቂቃዎች በፊት አሜሪካ እና ኢራን ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸው በጭንቀት ውስጥ ለቆየው ዓለም ፋታን ሰጥቷል።
ስምምነቱ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱት ጥቃት በ40ኛ ቀኑ እንዲቆም የሚያደርግ ሲሆን፣ ቴህራንም በዓለም የኃይል አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ቀውስ የፈጠረውን የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ለጊዜው ለመክፈት ተስማምታለች።
ስምምነቱ ይፋ ከሆነ በኋላ ሁለቱም አገራት ጦርነቱን በአሸናፊነት እንደተወጡት እየገለጹ ነው። የኢራንን ሥልጣኔ አመድ እንደሚያደርጉት ሲዝቱ የነበሩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ አገራቸው በጦርነቱ "አጠቃላይ እና የተሟላ ድል" ማግኘቷን ለፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ ተናግረዋል።
ኢራንም በበኩሏ በተደረሰው የተኩስ አቁም አማካኝነት በአሜሪካ እና በእስራኤል ላይ ድል መቀዳጀቷን ገልጻለች። አርብ ዕለት ፓኪስታን ውስጥ በሚጀመረው ድርድር ጦርነቱን በዘላቂነት ለማስቆም እንደምትጥር እና ጥያቄዎቿን እንደምታቀርብ አስታውቃለች።
የኢራን የፀጥታ ብሔራዊ ጠቅላይ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ "ጠላት በኢራን ሕዝብ ላይ በከፈተው የፈሪ ሕገወጥ እና የወንጀል ጦርነት የማይካድ፣ ታሪካዊ እና ከባድ ሽንፈት ደርሶበታል" ሲል "ኢራን ታላቅ ድል መቀናጀቷን" አውጇል።
በጦርነቱ ከአሜሪካ ጎን ተሰልፋ ኢራን ላይ ጥቃት ስትፈጽም የነበረችው እስራኤልም፤ ዋሽንግተን ከቴህራን ጋር የደረሰችውን የተኩስ አቁም ስምምነት እንደተቀበለችው የፕሬዝዳንት ትራምፕ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ለ39 ቀናት የተካሄደው ይህ ጦርነት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ እስራኤል ኢራን ላይ የከፈተችው የ12 ቀናት ጦርነት ተከታይ ሲሆን በኢራን ላይም ከባድ ጉዳት አድርሷል።
ከመጀመሪያው የጥቃቱ ዕለት አንስቶ ጠቅላይ መሪዋ እና ሌሎች ከፍተኛ ፖለቲካ እና ወታደራዊ መሪዎቿ የተገደሉባት ኢራን በቀላሉ እጇን አልሰጠችም።
ዶናልድ ትራምፕ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ በኢራን የአገዛዝ ለውጥ በማምጣት ይጠናቀቃል ያሉት ጦርነት የቴህራንን የአጸፋ እርምጃዎች አስከትሎ ለስድስት ሳምንታት ዘልቋል።
ኢራን የዓለም 20 በመቶ የነዳጅ ምርት ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ አገራት የሚወጣበትን ሆርሙዝ ወሽመጥ በመዝጋት የጦርነቱ ወላፈን በቀሪው ዓለምም እንዲዳረስ አድርጋለች። ከዚህም አልፋ የአሜሪካ ወዳጅ የሆኑ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራትን በድሮን እና በሚሳዔል ያለማቋረጥ ስታጠቃ ቆይታለች።
መጀመሪያ ላይ ኢራን እጅ እንድትሰጥ በአሜሪካ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ የተጠየቀች ቢሆንም ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። ለድርድር የሚሆኑ ነጥቦች በፕሬዝዳንት ትራምፕ ቢቀርቡም፤ ኢራን ተቃራኒ የሆነ የራሷን የድርድር አጀንዳ በማቅረቧ መግባባት ላይ ሳይደረስ ቀርቷል።
ሳምንታት እየተቆጠሩ ሲሄዱ እንዲሁም የሆርሙዝ ወሽመጥ የመርከቦች እንቅስቃሴ መስተጓጎል በዓለም የነዳጅ አቅርቦት እና በዋጋ ላይ ቀውስ ሲያስከትል አሜሪካ ሌሎች አገራት ጣልቃ እንዲገቡ እስከመጠየቅ ደርሳለች።
ትራምፕ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን አገራት (ኔቶ) አባላት የሆርሙዝ ወሽመጥን በማስከፈቱ በኩል እንዲሳተፉ እና ከአሜሪካ ጎን እንዲቆሙ ቢጠይቁም ተቀባይነት ሳያገኙ ቀርተዋል። ይህም ከምዕራባውያን ወዳጆቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ከማሻከር አልፎ አሜሪካን ከኔቶ ለማስወጣት እያሰቡ መሆናቸውን እንዲናገሩ አድርጓቸዋል።
የአሜሪካ የኔቶ አጋሮች እና ሌሎች አገራት በኢራን ላይ የሚካሄደውን ጦርነት የመቀላቀል ፍላጎት እንደሌላቸው በይፋ ገልጸዋል። አንዳንዶቹም የጦርነቱን ተገቢነት እስከመጠየቅ ደርሰዋል።
ኢራን በጦርነቱ ውስጥ የሆርሙዝን መተላለፊያ ጉዳይን እንደወሳኝ የተጽእኖ መሳሪያ በመያዝ ከጥቂት የወዳጆቿ መርከቦች ውጪ በሺዎች የሚቆጠሩት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በአካበቢው እንዳያልፉ አግዳ ቆይታለች።
በዚህም በዙሪያዋ ያሉትን ምጣኔ ሀብታቸው በነዳጅ ምርት ላይ የተመሠረተ፣ የአሜሪካ አጋር የሆኑ እና የዋሽንግተንን ጦር ሠፈሮች የሚያስተናግዱ የባሕረ ሰላጤው አገራት ምጣኔ ሀብትን ክፉኛ አዳክማለች።
በተጨማሪም ከአካባቢው የሚወጣውን ከፍተኛ መጠን ያለውን ነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ በስፋት የሚጠቀሙት በቀሪው የዓለም ከፍል የሚገኙ አገራት ውስጥ የተፈጠረው የአቅርቦት ችግር በጦርነቱ ቀስቃሾች ላይ አሉታዊ ስሜት እንዲፈጠር አድርጓል።
ይህ ጦርነት ከሆርሙዝ ወሽመጥ ጋር በተያያዘ ኢራን አዲስ ጥያቄን እንድታነሳ በር የከፈተላት ይመስላል። ከአንድ ሳምንት በፊት የአገሪቱ ፓርላማ ያወጣው አዲስ ሕግ በሆርሙዝ በኩል የሚተላለፉ መርከቦች ለኢራን ክፍያ እንዲፈጽሙ የሚያስገድድ ነው። ይህ ሃሳብም ኢራን ለድርድር ካቀረበቻቸው ነጥቦች መካከል አንዱ እንደሆነ እየተነገረ ነው።
ትራምፕ ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ የመጨረሻው ሰዓት ላይ ውሳኔያቸውን ያስቀለበሰው ስምምነት የተደረሰው በዋናነት በፓኪስታን አማካኝነት ሲሆን፣ ቻይናም ኢራንን ለድርድር በማግባባት ሚና እንደነበራት ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ "የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ የሆርሙዝ ወሽመጥን ሙሉ ለሙሉ፣ በአስቸኳይ በመክፈት ደኅንነቱ እንዲጠበቅ ለማድረግ በመስማማቷ በኢራን ላይ ሊካሄድ የነበረውን ጥቃት በሁለት ሳምንታት እንዲዘገይ ተስማምቻለሁ" ሲሉ አሳውቀዋል።
በዚህም ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ረቡዕ ሌሊት ለሐሙስ አጥቢያ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ክፍት እንድታደርግ የጊዜ ገድብ አስቀምጠዋል።
የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ለሁለት ሳምንታት መርከቦች በባሕር መተላለፊያው በኩል ያለ ችግር እንዲያልፉ ኢራን መፍቀዷን አረጋግጠዋል።
"በኢራን ላይ የሚፈጸሙት ጥቃቶች ከቆሙ፣ ኃያሎቹ የጦር ኃይሎቻችን ሲያካሂዱት የነበሩትን የመከላከል ዘመቻዎች የሚያቆሙ ይሆናል" በማለት ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በዚህም ምክንያት ለሳምንታት በሆርሙዝ አቅራቢያ በሚገኙ ወደቦች እና የውሃ አካላት ላይ ሲጉላሉ የነበሩት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በመንቀሳቀስ ነዳጅ ለማዘዋዋር ዕድል ያገኛሉ።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከታወጀ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ከ17 በመቶ በላይ ቅናሽ አሳይቷል። ሌሎችም የንግድ እንቅስቃሴዎች የተነቃቁ ሲሆን፣ በርካታ አገራት የተደረሰውን ስምምነት በበጎ ተቀብለውታል።
በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ አሜሪካ እና ኢራን በሚያደርጓቸው ድርድሮች ልዩነቶቻቸውን በማጥበብ ዘላቂ ሰላም ይወርዳል ተብሎ ይጠበቃል። ትራምፕ አሜሪካ ዘላቂ ስምምነት ላይ የመድረስ ፍላጎት እንዳላት በመግለጽ በኢራን የቀረበውን ባለ 10 ነጥብ ዕቅድ "የሚያሠራ" በማለት ሊነጋገሩበት እንደሚችሉ ጠቅሰዋል።
ኢራን ይፋ ያደረገችው ባለ10 ነጥብ የድርድር ሃሳብ በጦርነቱ ወቅት ከተከሰተው ሁኔታ በመሻገር የኢራንን ቆዩ ጥያቄዎችንም ለማስመለስ ያለመ ነው። ኢራን ለረጅም ጊዜ በአሜሪካ የተጣሉባት ማዕቀቦች እንዲነሱ፣ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ያላት መብት እንዲከበር እና የአሜሪካ ኃይሎች ከአካባቢዋ እንዲወጡ የሚሉት ይገኙበታል።
በተጨማሪ ደግሞ አሜሪካ እና እስራኤል ጦርነት እንዲከፍቱባት ዋነኛ ምክንያት የሆነው የኒውክሌር መረሃ ግብሯን የተመለከተ ነጥብ አቅርባላች። ይህም አሜሪካ ኢራን የምታካሂደውን ዩራኒየም የማዳበር ተግባሯን እንድትቀበል የሚጠይቅ ነው።
በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ከኢራን የሚተኮሱት ሚሳዔሎች ቁጥር እየቀነሱ መሆናቸውን እና በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚቆሙ በአሜሪካ በኩል ሲነገር ነበር። ነገር ግን የተኩስ አቁም እስከሚደረግበት ጊዜ ድረስ ኢራን በዙሪያዋ ባሉ አገራት እና በእስራኤል ላይ ያልተቋረጠ ጥቃት ስትፈጽም ቆይታለች።
ቁልፍ መሪዎቿ ተገድለውባት እና መሠረተ ልማቶቿ ወድመውባት አገዛዙ ይወድቃል ቢባልም የትራምፕ ተደጋጋሚ ዛቻዎች አልፈው መሪዎቿ ወደ ተኩስ አቁም ደርሰው ለድርድር እየተዘጋጁ ነው።
ትራምፕ በዚህ ጦርነት በየዕለቱ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር እያወጡ ተጨማሪ የመከላከያ በጀት እስከመጠየቅ ደርሰዋል። በአገር ውስጥ ያላቸው ተቀባይነት ላይም ከፍተኛ ጫና መፈጠሩን የሕዝብ አስተያየት መለኪያዎች እያመከለቱ ነው።
በተጨማሪም በኢራን ላይ ባካሄዱት ዘመቻ ወቅት ጀርባቸውን ከሰጧቸው ከኔቶ አጋሮቻቸው ጋር ተኮራርፈዋል። በቬንዙዌላ ላይ በጀመሩት ወረራ በጥርጣሬ ሲታዩ የነበሩት ትራምፕ አሁን ለይቶላቸው በአሜሪካውያን ፖለቲከኞች ሳይቀር በበርካቶች ዘንድ እንደጠብ ጫሪ እየታዩ ነው።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ሊያሳኳቸው ከሚፈልጓቸው ግቦች መካከል የኖቤል ሽልማትን ማግኘት አንዱ ነው። ለዚህም በተለያዩ አገራት መካከል የተከሰቱ ግጭቶችን በማስቆም እና በማሸማገል እራሳቸውን ለሽልማቱ ሲያዘጋጁ ነበር።
ነገር ግን ይህ በኢራን ላይ ያካሄዱት ጦርነት ወደ ኖቤል የሰላም ሽልማት የመቅረባቸውን ዕድል ሙሉ ለሙሉ ሊዘጋው የሚችል ክስተት እንደሆነ እየተነገረ ነው።
አሁንም ጦርነቱ በሁለት ሳምንታት የተኩስ አቁም ጋብ ሊል ቢችልም በድርድሩ ወቅት የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በድጋሚ እንዲቀሰቀስ ሊያደርገው ይችላል።
ያም ሆነ ይህ በአሁኑ ጊዜ የዚህ ጦርነት አሸናፊ በግልጽ የሚታይበት ሁኔታ የሌለ ሲሆን፣ ምናልባትም በቀጣይ ሳምንታት በሚደረጉ ድርድሮች በሚኖር የሰጥቶ መቀበል ስምምነት ከአሜሪካ እና ከኢራን ማን ምን አገኘ የሚለው አሸናፊውን ሊያሳይ ይችላል።