በኬንያ በጎርፍ መጥለቅለቅ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 66 ደረሰ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በኬንያ በተለያዩ አካባቢዎች በደረሰ የጎርፍ መጥለቅለቅ ቢያንስ 66 ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።

የአገሪቱ ፖሊስ እንዳስታወቀው ሰሞኑን ባጋጠመው የጎርፍ መጥለቅለቅ ተጨማሪ አራት ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ባለፈው ሳምንት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 66 መድረሱን ገልጿል።

በመዲናዋ ናይሮቢ ከፍተኛ ዝናብ የጣለ ቢሆንም በሰዎች ላይ ተጨማሪ ጉዳት አላደረሰም ተብሏል።

በመዲናዋ በሚኒባስ ሲጓዙ የነበሩ 11 ሰዎች በጎርፍ ተውጠው በአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ሕይወታቸውን ማትረፍ ተችሏል።

በሌላ በኩል ቤታቸው በጎርፍ ሲወሰድ አብረው የተወሰዱ ሁለት ሕጻናትንም እንዲሁ በሕይወት ማትረፍ መቻሉን የኬንያ ቀይ መስቀል አስታውቋል።

በኬንያ እየጣለ ያለውን ከፍተኛ ዝናብ ተከተሎ ወንዞች በመሙላታቸው ጎርፍ መንገዶችን ሲዘጋ፣ በኃይል አቅርቦት እና በቤቶች ላይም ጉዳት አድርሷል።

በአንዳንድ ዋና ዋና መንገዶች የሚገኙ ድልድዮች በጎርፍ በመወሰዳቸው ምክንያት ተዘግተዋል። በጎርፍ የተጥለቀለቁ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውም ተነግሯል።

የኬንያ የአገር ውስጥ ሚኒስቴር በቀጣዮቹ ቀናትም ከፍተኛ ዝናብ እንደሚኖር አስታውቆ የጎርፍ አደጋውም በዚያው ልክ ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቋል።

በመሆኑም ስጋት ያለባቸው አካባቢ ነዋሪዎች ለጊዜው አካባቢያቸውን እንዲለቁ ጠይቋል። ቢያንስ 2 ሺህ ሰዎች በመዲናዋ ናይሮቢ ቤታቸውን እንዲለቁ ተነግሯቸዋል።

የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በጎርፍ የሚጠቁ ሰዎችን ለመርዳት በመላ አገሪቱ ርብርብ እያደረጉ መሆኑን ገልጿል።

በመላ አገሪቱ በጎርፍ ከሞቱት 66 ሰዎች መካከል ግማሾቹ ወይም 33 የሚሆኑት የሞቱት በዋና ከተማዋ ናይሮቢ ውስጥ ነው።

ነዋሪዎች በተለይ በመዲናዋ ፓርክ ላንድ ተብሎ በሚጠራው ክፍል በአንዳንድ ቦታዎች ላይ እስከ ሁለት ሜትር ከፍታ ያለው የውሃ ማቆር ተፈጥሮ ማየታቸውን ገልጸዋል።

አንዳንዶቹ ቅድመ ማስጠንቀቂያውን ተከትሎ ሰፈር ቀይረው ማደራቸውንም ተናግረዋል።

ባለፈው ቅዳሜ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የተዘጉ የውሃ መውረጃ ቦዮችን ለመክፈት ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረው ነበር።

ነገር ግን ቢቢሲ ያነጋገራቸው በናይሮቢ የፓርክላንድስ ነዋሪዎች እስካሁን የውሃ መውረጃ መስመሮቹ እየከፈቱ ያሉት በራሳቸው ጥረት ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ምግብ እና መድሃኒት መላኩንም ተናግረዋል።

ከኬንያ በተጨማሪ በደቡብ ኢትዮጵያ ጋሞ ዞንም ከፍተኛ ዝናብ ባስከተለው የመሬት መንሸራተት ሳቢያ ከ100 በላይ ሰዎች ሞተዋል።