ብልጽግና ፓርቲ ዕጩ ባላቀረበበት ትግራይ ክልል ምርጫ ይካሄዳል?

የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

ብልጽግና ፓርቲ፤ ምርጫ የመካሄዱ ነገር አጠራጣሪ በሆነበት ትግራይ ክልል ለሚገኙ የፓርላማ እና የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች አንድም ዕጩ አለማቅረቡን ቢቢሲ የተመለከተው የዕጩዎች ዝርዝር ያሳያል። ስድስት ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሁለት ቅንጅቶች በበኩላቸው 101 ዕጩዎችን አስመዝግበዋል።

በትግራይ የቀረበው ጠቅላላ ዕጩዎች ቁጥር በክልሉ ካሉት የፓርላማ እና የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ብዛት ያነሰ ነው። የፌዴሬሽን ምክር ቤት አከራካሪ ባላቸው ስፍራዎች ላይ ውሳኔ ከማሳለፉ በፊት ይፋ የተደረገ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በትግራይ ክልል በድምሩ 182 መቀመጫዎች አሉ።

ከዚህ ውስጥ 152 ያህሉ የክልል ምክር ቤት እንደሆኑ፤ 38ቱ ደግሞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትግራይ ተወካዮች እንደሆኑ ተጠቅሷል።

ምርጫ ቦርድ ከአንድ ወር ገደማ በፊት የካቲት 23/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ "በትግራይ እና አማራ ክልል መንግሥታት መካከል አከራካሪ ሆነው የቆዩት አምስት የምርጫ ክልሎች"፤ ከትግራይ "ውጪ ሆነው ለብቻቸው" ምርጫ እንዲደረግባቸው መወሰኑን አስታውቋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት፤ "በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት" ምርጫ እንዲደረግ የወሰነባቸው የምርጫ ክልሎች "ሑመራ፣ አዲ ረመፅ፣ ኮረም ኦፍላ፣ ጠለምት እና ራያ" ናቸው።

ቢቢሲ አማርኛ በተመለከተው የዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ በእነዚህ የምርጫ ክልሎች ለመወዳደር የተመዘገቡ ተወካዮች አልተካተቱም።

በትግራይ ክልል ከፍተኛ የዕጩዎች ቁጥር ያስመዘገበው ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ተነጥለው በወጡ ፖለቲከኞች የተመሠረተው ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑትን የፓርቲው ሊቀ መንበር ጌታቸው ረዳን ለውድድር ያላቀረበው ስምረት፤ ሰባት ዕጩዎችን ያስመዘገበው ለፓርላማ ወንበሮች ነው።

የትምህርት ሚኒስቴር አማካሪ እና የፓርቲው የውጭ ግንኙነት ኃላፊው ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወትን ጨምሮ 30 ዕጩዎች ደግሞ ለክልሉ ምክር ቤት ለመወዳደር ቀርበዋል።

ትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ ፓርቲ 24 ዕጩዎችን ለፓርላማ እና ለክልል ምክር ቤት በማስመዝገብ በሁለተኝነት ተቀምጧል። ነጻነት እና እኩልነት እንዲሁም ራያ ራዩማ ፓርቲዎች በዕጩ ብዛት ተከታይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) እና ትንሳኤ ሥርዓት ቃንጪ ሃቂ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅንጅት የሆኑት ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት እና ሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረትም ዕጩዎቻቸውን አስመዝግበዋል።

ቁርጡ ያልታወቀው የትግራይ ክልል ምርጫ

በደም አፋሳሹ ጦርነት ምክንያት ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ያልተካሄደበት የትግራይ ክልል፤ ላለፉት አምስት ዓመታት በሕዝብ ተወካዮች እና በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውስጥ አልተወከለም። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተነሳ በአገር አቀፍ ደረጃ ምርጫ በተራዘመበት ወቅት ለብቻው ምርጫ በማካሄድ የመሰረተው የክልል ምክር ቤትም ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ተበትኗል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትግራይ ምርጫ እንደማይካሄድ በይፋ ባያሳውቅም፤ ከሌሎች አገሪቱ አካባቢዎች በተለየ በክልሉ የመራጮች ምዝገባ ሂደት አልተጀመረም።

በአገር አቀፍ ደረጃ የመራጮች ምዝገባ በተጀመረበት የካቲት 28/2018 ዓ.ም. ትግራይ ክልል ውስጥም ተመሳሳይ ሂደት ለማከናወን ዕቅድ የነበረ ቢሆንም "በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካ" መቅረቱን የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ መናገራቸው አዲስ ማለዳ ተዘግቦ ነበር።

ሰብሳቢዋ የምርጫ ምዝገባ ሂደቱ ወደፊት እንደሚጀመር በወቅቱ እንደገለጹም ተነግሯል። እስካሁን ድረስ ግን በክልሉ የመራጮች ምዝገባ አለመጀመሩን ቢቢሲ ትግርኛ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ምርጫ ቦርድ፤ በክልሉ የሚገኙ ምርጫ ክልሎች እና የምርጫ ጣቢያ ጽሕፈት ቤቶች እንዲዘጋጁለት ከታኅሣሥ ጀምሮ ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ያቀረባቸው ጥያቄዎች እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸውን ምንጮች ተናግረዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምንጭ፤ "በትግራይ ያለው ሁኔታ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል አይደለም" የሚል ድምዳሜ ላይ መደረሱን ለቢቢሲ ትግርኛ አስረድተዋል። ይሁን እንጂ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይህንን ድምዳሜውን ለምርጫ ቦርድ አለማሳወቁን ጠቅሰዋል።

በቅርቡ ለቦርዱ ምላሽ ሊሰጥ እንደሚችል የተናገሩት ምንጩ፤ "ምርጫ የሕዝቦች መብት ቢሆንም፣ አሁን በትግራይ ምርጫ የሚካሄድበት ዕድል የለም ማለት ይቻላል" ብለዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጥር ላይ ከቦርዱ በድጋሚ ደብዳቤ ከተጻፈለት በኋላ፤ በምርጫ ጉዳይ ላይ "የጋራ መግባባት እና አቋም ለመያዝ" በሚል በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ስብሰባ ጠርቶ ነበር።

በዚህ ስብሰባ "አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች፤ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ሳይመለሱ እና የትግራይ የግዛት አንድነት ወደ ነበረበት ሳይመለስ በትግራይ የሚካሄድ ምርጫ የለም" የሚል አቋም ላይ መስማማታቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ትግርኛ ገልጸዋል።

ቢቢሲ የትግራይ ክልል የምርጫ ዝግጅት በተመለከተ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምላሽ ለማግኘት ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም።

የትግራይ ፖለቲካዊ ሁኔታ ለምርጫ ያመቻል?

ከአንድ ገደማ ዓመት በፊት በመጋቢት 30/2017 ዓ.ም. የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትነትን የተረከቡት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ በወቅቱ በፈረሙት "የቃል ኪዳን ሰነድ" ላይ ከሚገኙ ስምንት ኃላፊነቶች አንዱ ከምርጫ ጋር የተያያዘ ነው።

ትግራይ ክልልን "ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዝግጁ" የማድረግ የቤት ሥራ የተሰጣቸው ሌተናንት ጄነራል ታደሰ፤ ይህንን ማሳካት የቻሉ አይመስልም። የሚመሩት ጊዜያዊ አስተዳደር የተራዘመለት የአንድ ዓመት ቆይታ ጊዜም ሊጠናቀቅ ከሁለት ሳምንት ያነሰ ዕድሜ ቀርቶታል።

ባለፈው ዓመት በተሻሻለው የፌደራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓትን የሚደነግግ አዋጅ መሠረት፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩ የቆይታ ጊዜ በድጋሚ "ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ጊዜ" ሊራዘም ይችላል። ይሁንና እስካሁን የጊዜያዊ አስተዳደሩን ዕጣ ፋንታ በተመለከተ ከፌደራል መንግሥትም ሆነ ከክልሉ ባለሥልጣናት በይፋ የተሰጠ አስተያየት የለም።

ታደሰ ወረደ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የፌደራል እና የትግራይ ክልል ግንኙነት ይበልጥ ሻክሯል። የፌደራል መንግሥት የድጎማ በጀት እንዲሁም ወደ ክልሉ የሚደርስ የነዳጅ አቅርቦት መቋረጡን አስታውቋል።

በተጨማሪም ጥር ወር ላይ የፌደራል እና የክልሉ ኃይሎች ግጭት ውስጥ ገብተው ነበር። በወቅቱ ወደ ትግራይ የሚደረግ የአውሮፕላን በረራ ለአምስት ቀናት ተቋርጦ እንደነበርም ይታወሳል።

በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መንግሥታት መካከል የፈጠረው ውጥረትም ይበልጥ ከርሯል። አዲስ አበባ እና አሥመራ ጦርነት ውስጥ የሚገቡ ከሆነ ትግራይ ክልል ዋነኛ የግጭት ማዕከል ይሆናል የሚል ስጋትም ተፈጥሯል።

ከፖለቲካ ፓርቲነት የተሰረዘው የትግራዩ ዋነኛ የፖለቲካ ተዋናይ ህወሓትም፤ "ሕጋዊ ሰውነቱ ወደ ነበረበት ሳይመለስ በትግራይ ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ እንደማይታሰብ" የፓርቲው ቃል አቀባይ ሚካኤል አስገዶም ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ትግራይ ክልል ውስጥ አስቻይ ሁኔታ ያልተፈጠረው ለምርጫ ብቻ አይደለም። የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽንም በትግራይ ክልል ሊያደርግ የነበረውን "የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊዎች ልየታ መድረክ" በአዲስ አበባ እንደሚያካሂድ ዛሬ አርብ መጋቢት 18/2018 ዓ.ም. አስታውቋል።

ኮሚሽኑ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው "በክልሉ ተሳታፊዎችን የመለየት እና አጀንዳ የማሰባሰብ ተግባር ለማከናወን የሚረዳ አስቻይ ሁኔታ ባለመፈጠሩ" እንደሆነ ገልጿል።

"አስቻይ ሁኔታ እንዲፈጠር" የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርን እና በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጭምር ያካተቱ "ከ22 በላይ ውይይቶችን በመቀለ እና አዲስ አበባ" ከተሞች ማድረጉንም አስታውሷል።

በዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ ባለው ትግራይ ምርጫ ይካሄዳል የሚለው ሀሳብ ለክልሉ ነዋሪዎች የሚዋጥ አይመስልም። ከእነዚህ ነዋሪዎች አንዱ በመቀለ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ እና ሥነ-ጽሁፍ መምህር እና አክቲቪስት የሆኑት አብርሃ ኃይለዝጊ ናቸው።

አብርሃ፤ ክልሉ ከምርጫ ይልቅ የጦርነት ስጋት እንዳረበበት ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል። ጦርነት ይጀመራል በሚል ስጋት ወጣቶች ወደሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች እየተጓዙ መሆኑንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የክልሉ ሁኔታ እርግጠኝነት ላይ ለመድረስ በማያስችሉ ሁኔታዎች የተሞላ መሆኑን የሚናገሩት አብርሃ፤ "አሁን ምርጫ ቅንጦት ሆኗል" ሲሉ ምልከታቸውን አጋርተዋል።

"የአከራካሪዎቹ ቦታዎች" ምርጫ ጉዳይ

የፌዴሬሽን ምክር ቤት "አከራካሪ" ሲል የገለጻቸው አምስት ምርጫ ክልሎች ከትግራይ ውጪ ሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወካይ እንዲመረጥባቸው ያሳለፈው ውሳኔ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ፓርቲዎች እና ከ"ሓራ መሬት" ታጣቂዎች ጭምር ተቃውሞ ገጥሞታል። በአማራ ክልል በኩል ያሉ የፖለቲካ ተዋናዮች በአንጻሩ ድጋፋቸውን ችረውታል።

ተቃዋሚው ስምረት ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታ በማቅረብ ውሳኔውን አሳግዶት የነበረ ቢሆንም ኋላ ላይ ክሱን አቋርጧል። ፍርድ ቤቱም እግዱን አንስቷል።

ይህንን ተከትሎ በፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት በአካባቢዎቹ ምርጫ እንደሚካሄድ ይጠበቃል። በምርጫ ክልሎቹ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወካይ ለመሆን በዕጩነት የሚቀርቡት የትኛዎቹ ፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው የሚለው ግን እስካሁን ግልጽ አይደለም።

ቢቢሲ አማርኛ ያነጋገራቸው አንድ የምርጫ ሕግ ባለሙያ፤ እነዚህ ቦታዎች ከትግራይ ክልል ውጪ ሆነው በቀጥታ ምርጫ እንዲደረግባቸው መወሰኑ በክልላዊ ፓርቲነት የተመዘገቡ የፖለቲካ ቡድኖችን ከመወዳደር ሊያግዳቸው እንደሚችል ገልጸዋል።

የምርጫ ሕግ ባለሙያው "ከሁለቱም ክልሎች ውጪ ከሆነ የየትኛውም ክልል ፓርቲ አይሳተፍም። የትግራይ ክልል ፓርቲ እንዳይወዳደር አካባቢው ከትግራይ ክልል ተነስቷል። የአማራ ክልል ፓርቲም እንዳይወዳደር በአማራ ክልል ስር ያለው ጊዜያዊ አስተዳደርም ሕጋዊ አይደለም። የሆነ ዓይነት ማብራሪያ ይፈልጋል" ብለዋል።

እንደ ባለሙያው ገለጻ በዚህ አሠራር መሠረት አካባቢውን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወክል ዕጩ ማቅረብ የሚችሉት እንደ ብልጽግና ያሉ አገር አቀፍ ፓርቲዎች ናቸው።

ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ከምርጫ ቦርድ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም። ቢቢሲ በተመለከተው የምርጫ ዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ እነዚህ አካባቢዎች አልተካተቱም።

ይሁን እንጂ በአማራ ክልል ስር የተመሠረተው የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ሰቲት፣ ሁመራ ዞን አመራሮች የብልጽግና ፓርቲን ማኒፌስቶ እና የምርጫ ምልክት ባለፈው የካቲት ላይ በዞኑ ይፋ አድርገዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አሸተ ደምለው፤ "7ኛው አገራዊ ምርጫ ሕዝባችን የመምረጥ መብቱን ያገኘበት ታሪካዊ እና ፍትሐዊ ምርጫ [ነው]" ሲሉ በማስተዋወቂያ መድረኩ ላይ ተናግረዋል።

የአካባቢው ሕዝብ "በምርጫው መሳተፉ የሕዝቡን የወሰን እና የማንነት ጥያቄ መመለስ የሚያሳይ ትልቅ ዕድል" መሆኑን የገለጹት የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ደግሞ ነዋሪዎች እንዲመርጡ አሳስበዋል።

የምርጫ ሕግ ባለሙያው፤ በእነዚህ አካባቢዎች በቀጥታ ለተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ እንዲደረግ የተወሰነው "የፌደራል መንግሥቱ በጀት የሚመድብለት እና የሚቆጣጠረው፣ የሚያግዘው የፖለቲካ አስተዳደር በአካባቢው እንዲመሠረት" ለማድረግ ነው የሚል ምልከታ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ባለሙያው አከራካሪ ተብለው በተገለጹት አካባቢዎችም ቢሆን ለሚካሄደው ምርጫ የሚሆን አስተማማኝ ደኅንነት የመኖሩ ጉዳይ ላይ ጥያቄ ያነሳሉ። የራያ አካባቢዎች በትግራይ ኃይሎች ስር እንደሚገኙም በማሳያነት ጠቅሰዋል።

"በተለይ በኮረም፣ አላማጣ፣ ራያ ያሉት አካባቢዎች ከሞላ ጎደል በህወሓት አስተዳደር [ናቸው]፤ ከዚያም ካለፈ ግጭት የሚፈጠርባቸው ናቸው" ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። በወልቃይት አካባቢዎች "የበላይነት ያለው ኃይል" በመኖሩ ምርጫ ለማደራጀት የተሻለ ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰዋል።

አክለውም፤ በራያ አካባቢዎች "ምርጫ ቦርድ በምን ዓይነት ሁኔታ ምርጫውን ሊያደራጅ እንደሚችል እርግጠኛ አይደለሁም። በሌሎቹ የትግራይ አካባቢዎች ምርጫ የማይደረግ ከሆነ በእነዚህም ላይ ለማድረግ የሚያስችል ፖለቲካዊ እና ደኅንነት ሁኔታ አለ ብዬ አላስብም" ብለዋል።