ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፈቃድ ሞት ጥያቄዋን በሕግ ካሳገዱባት አባቷ ጋር ስትከራከር የቆየችው ስፔናዊት ሕይወቷ እንዲያልፍ ተደረገ
ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ታሪክ ወሲባዊ ጥቃት እና ራስን ማጥፋት የተመለከቱ ገለጻዎችን ይዟል
በፈቃዷ ለመሞት ለረዥም ጊዜ ከአባቷ ጋር የሕግ ክርክር ያደረገች የስፔናዊት ሐሙስ ዕለት በገዛ ፈቃዷ ሕይወቷ እንዲያልፍ ተደረገ።
የ25 ዓመቷ የባርሴሎና ነዋሪ ኖኤልያ ካስቲሎ በአውሮፓውያኑ 2022 ራሷን ለማጥፋት በሞከረችበት ወቅት በደረሰባት ጉዳት የተነሳ አካሏን ማንቀሳቀስ እንዳትችል ያደረጋት ጉዳት ደርሶባታል።
የካታላን መንግስት በ2024 በሕክምና ድጋፍ ሕይወቷ እንደያልፍ መብት ሰጥቷት ነበር። ይሁን እንጂ ባለቀ ሰዓት አባቷ የህግ ተቃውሞ ማንሳታቸውን እና ወግ አጥባቂው የክርስቲያን ጠበቆች ቡድን (አቦጋዶስ ክሪስቲያኖስ) በጉዳዩ ጣልቃ መግባቱን ተከትሎ ሂደቱ ተቋርጧል።
አባት፤ ልጃቸው ውሳኔዋን የሚያውክ የባህሪ መዛባት አጋጥሟታል በማለት ተከራክረዋል።
"መንግስት የሰዎችን ሕይወት በተለይም አዕምሮ ጤና ችግር ያለባቸው እጅግ ተጋላጭ የሆኑ ወጣቶችን ሕይወት የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበትም" ገልጸዋል።
ይግባኙ የ18 ወራት የሕግ ውዝግብ ካስነሳ በኋላ የአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ፍርድ ቤት (ኢሰኤችአር) ኖኤሊያ ካስቲሎን ደግፎ ወስኗል።
አቦጋዶስ ክሪስቲያስ ሐሙስ ምሽት በኤክስ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ፤ ካስቲሎ በሐኪሞች ድጋፍ ሕይወቷ ማለፉን አስታውቋል። ጉዳዩ "በስፔን በሕክምና እርዳታ የመሞት ሕግ ውስጥ ያሉትን ክፍተቶች አጉልቶ ያሳያል" ሲል ቡድኑ ገልጿል።
ካስቲሎ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ለአንድ የስፔን ቴሌቪዥን ጣቢያ እንደተናገረችው፤ አባቷ በክብር የመሞት ውሳኔዋን በሕጋዊ መንገድ ለማገድ ሞክረዋል። "ውሳኔዬን አላከበረም" ብላለች።
የነበራትን አስቸጋሪ የልጅነት ጊዜዋን፤ በተለይም አብዛኛውን የሕጻንነት ዕድሜዋን በእንክብካቤ መስጫ ማዕከላት ማሳለፏን አንስታም ተርካለች።
ለመተኛት የሚረዳትን የእንቅልፍ ክኒን ወስዳ ከተኛች በኋላ ለአራት ዓመት አብሯት በነበረ በቀድሞ የወንድ ጓደኛዋ የጾታዊ ጥቃት እንደተፈጸመባት ተናግራለች። በሌላ አጋጣሚ ደግሞ በምሽት ክበብ ውስጥ በበርካታ ወንዶች ጥቃት እንደደረሰባት ገልጻለች።
የ25 ዓመቷ ወጣት ሁልጊዜም "ብቸኝነት ይሰማት" እንደነበር እና በሕክምና ባለሙያዎች ድጋፍ ሕይወቷ እንዲያልፍ ለማድረግ የደረሰችው ውሳኔ ላይ ምንም ጥርጣሬ እንዳልነበራት ተናግራለች።
"ከቤተሰቤ ውስጥ ማንም የሚደግፍኝ የለም። እኔ እሄዳለሁ፤ እናንተ እዚህ የምትቆዩት ህመሙን ሁሉ ይዛችሁ ነው። ባለፉት ዓመታት ያሳለፍኩትን ስቃይ ሁሉስ? በሠላም ለመሄድ እና ህመሙን ማስቆም ብቻ ነው የምፈልገው" ብላለች።
"የአባት፣ የእናት ወይም የእህት ደስታ ከልጅ ደስታ መቅደም የለበትም" ስትልም ተናግራለች።
ቤተሰቦቿ መጥተው መሰናበት እንደሚችሉ የገለጸችው ኖኤሊያ፤ ገዳዩ መርፌ ሲሰጣት ግን ከሐኪሟ ጋር ብቻዋን መሆን እንደምትፈልግ አክላለች።
እናቷ ዮላንዳ በልጇ ውሳኔ እንደማትስማማ ነገር ግን "እንደምታከብረው" ተናግራለች።
ስፔን በሐኪም ድጋፍ የሚደረግ ሕይወት የማስቆም ህግን በአውሮፓውያኑ 2021 ተግባራዊ አድርጋለች። በመንግስት መረጃ መሰረት በ2024 ብቻ 426 በሐኪም ድጋፍ ለመሞት የቀረቡ ጥያቄዎች ተቀባይነት አግኝተዋል። ይህ አሃዝ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተገኘ ትልቅ ቁጥር ነው።
ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት አቅንቶ በዳኛ ውሳኔ ሲሰጥበት ግን ይህ የመጀመሪያው ነው።