ተጨማሪ ወታደሮቿ እና የጦር መርከቧ ወደ ባሕረ ሰላጤው የደረሱት አሜሪካ የእግረኛ ዘመቻ ለማካሄድ መዘጋጀቷ ተነገረ

ቅዳሜ ዕለት በሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ወታደሮች እና አንድ የጦር መርከቧ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የደረሱት የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር ፔንታገን በኢራን ውስጥ ለሳምንታት የሚቆይ የእግረኛ ሠራዊት ዘመቻ ለማካሄድ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለጸ።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኢራን በሳዑዲ በፈጸመችው ጥቃት የአሜሪካ ወደታራዊ ጄት መመታቱ ተረገጋጠ

    ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በሚገኝ የአየር ኃይል ሰፈር ላይ በተፈጸመ ጥቃት የአሜሪካ የወደታራዊ ማዘዣ እና መቆጣጠሪያ አውሮፕላን መመታቱን ትክክለኛነታቸው የተረጋገጡ ፎቶዎች አመለከቱ።

    ከሳምንታት በፊት የተፈጸመውን ጥቃት የሚያሳዩ ፎቶዎች መጀመሪያ ላይ የተጋሩት የአሜሪካ ወታደራዊ ዜናዎችን በሚያወጣው የፌስቡክ ገጽ ላይ ነበር። ምሥሎቹ ኢ-3 ሴንትሪ የተባለው አውሮፕላን ለሁለት ተገምሶ አሳይተዋል።

    ቢቢሲ ባደረገው ማጣራት ፎቶዎቹ ከሳዑዲ ዋና ከተማ ሪያድ ደቡብ ምሥራቅ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የልዑል ሱልጣን አየር ኃይል ሰፈር የተነሱ ናቸው። በአውሮፕላኑ ዙሪያ የሚታዩት ነገሮች ከሳተላይት ምሥሎች ጋር ተመሳሳይ ናቸው።

    የቢቢሲ የመረጃ ማጣሪያ ቢቢሲ ቬሪፋይ ከጥቃቱ ቀን በፊት የወደመው ኢ-3 አውሮፕላን በስፍራው እንደነበረ በሳተላይት ምሥል የተመለከተ ሲሆን፣ ጉዳቱ የደረሰበት ተመሳሳይ አውሮፕላን ነው ለማለት ግን እርግጠኛ አይደለም።

    ማጣራት ከተደረገባቸው ፎቶዎች መካከል በአንዱ ላይ የአውሮፕላኑ የጭራ ቁጥር ይታያል። ቁጥሩን በመጠቀም በተደረገው ማጣራት አውሮፕላኑ በበረራ ላይ እንደነበር ለማረጋገጥ ተችሏል።

    በጥቃቱ ዕለት የተወሰዱ የሳተላይት ምሥሎች በአየር ኃይል ሰፈሩ ውስጥ እሳት እንደነበር አሳይተዋል። ነገር ግን እሳቱ ኢ-3 አውሮፕላኑ ላይ ጉዳት በደረሰበት ጥቃት የተነሳ ስለመሆኑ ግልጽ አይደለም።

    ከጥቃቱ በኋላ አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ለሮይተርስ ዜና ወኪል ኢራን በአየር ኃይል ሰፈሩ ላይ በፈጸመችው ጥቃት ሁለት በጽኑ የቆሰሉትን ጨምሮ 12 የአሜሪካ ወደታሮች መጎዳታቸውን ተናግሮ ነበር።

  2. ጦርነትን ተቀባይ ለማድረግ ኢየሱስ ክሰርቶስን መጠቀም አይቻልም፡ ፖፕ ሊዮ

    እስራኤል እና አሜሪካ በኢራን ላይ እያካሄዱት ያለው ጦርነት አንድ ወር በሞላው በአሁኑ ወቅት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳስ ሊዮ 14ኛ እግዚአብሔር ጦርነትን የሚያካሂዱ “እጃቸው በደም የተጨማለቀ” መሪዎችን ጸሎት አይቀበልም ሲሉ ተናገሩ።

    ጳጳሱ ቫቲካን ውስጥ በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የሆሳዕና በዓልን ለማክበር ለተሰበሰቡ በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ባደረጉት ንግግር የትኛውንም ጦርነት ለማካሄድ ኢየሱስ ክርስቶስን መጠቀም አይቻልም ብለዋል።

    "የሰላም ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ጦርነትን አይቀበልም፤ ጦርነት ተቀባይነት እንዲያገኝ ስሙን መጠቀም አይቻልም” በማለት ጦርነትን ተቃውመዋል።

    ለጳጳሱ ንግግር ምክንያት የሆነው አንዳንድ የአሜሪካ ባለሥልጣናት አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ በጋራ የከፈቱትን ጥቃት ተገቢነትን ለማሳየት መጽሐፍ ቅዱስን በመጥቀሳቸው ነው።

    ባለፈው ረቡዕ በአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር ፔንታገን ውስጥ በተካሄደ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት ክርስቲያናዊ ጥቅስን በመጥቀስ ጸሎት አድርገው ነበር።

    የሚጠቀሟቸውን ቃላት በጥንቃቄ በመምረጥ የሚታወቁት ፖፕ ሊዮ በኢራን ላይ የሚደረገው ጦርነት እንዲቆም በተደጋጋሚ ጠይቀዋል። ባለፈው ሰኞ ደግሞ በአየር የሚደረጉ ጥቃቶች ማንንም የሚለዩ ባለመሆናቸው እንዲታገዱ ጠይቀዋል።

  3. የአውሮፓ የባሕር ደኅንነት ተቋም መርከቦች ‘ከየመን የባሕር ክልል’ አንዲርቁ አስጠነቀቀ

    የየመኑ ሁቲ ታጣቂ ቡድን በቀይ ባሕር በኩል በሚያልፉ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸም እንደሚጀምር ማስጠንቀቁን ተከትሎ የአውሮፓ የባሕር ጉዞ ደኅነንት ተቋም መርከቦች ከየመን የባሕር ክልል እንዲርቁ አሳሰበ።

    የአውሮፓ ኅብረት የባሕር ትራንስፖርት ደኅንነት ተቋም በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች “በንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ሊፈጽሙ” ስለሚችሉ በተለይ ከቀይ ባሕር እና ከኤደን ባሕረ ሰላጤ እንዲርቁ አስጠንቅቋል።

    ይህ ማስጠንቀቂያ የወጣው የሁቲ አማጺያን ቅዳሜ ዕለት በእስራኤል ላይ ሚሳዔሎችን ከተኮሱ እና ተጨማሪ ጥቃቶችን እንደሚፈጽሙ ካሳወቁ በኋላ ነው።

    ሰፊውን የየመን ግዛት የሚቆጣጠሩት ሁቲዎች ከሕንድ ውቅያኖስ የዓለም አቀፍ የንግድ መስመር ወደ ሆነው ቀይ ባሕር መግቢያ በሆነው የባቤል መንደብ መተላለፊያ ላይ ጥቃት በመፈጸም የንግድ መርከቦችን እንቅስቃሴ የማደናቀፍ አቅም አላቸው።

    የአውሮፓ ኅብረት የባሕር ኃይል ተልዕኮ ጨምሮ እንዳስጠነቀቀው ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸው የንግድ መርከቦች ያለው “ስጋት እስኪቀንስ ድረስ” ከየመን የባሕር ክልል መራቅ ለደኅንነታቸው ጠቃሚ መሆኑን መክሯል።

    የደኅንነት ተቋሙ ባወጣው ሪፖርት ላይ በቀይ ባሕር ለሚተላለፉ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ላላቸው መርከቦች ያለው ስጋት ደረጃ “ከፍተኛ” መሆኑን አመልክቷል።

    ጨምሮም በቀይ ባሕር በኩል የሚያልፉ “ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ግንኙነት የሌላቸው” መርከቦችም ስጋት ያለባቸው ሲሆን፣ ይህም “በመካከለኛ” ደረጃ ላይ ይኛል ብሏል።

    በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች ለሁለት ዓመታት ጋዛ ውስጥ ጦርነት በተካሄደበት ጊዜ የእስራኤልን ጥቃት በመቃወም ለፍልስጤማውን ያለውን ድጋፍ ለማሳየት በቀይ ባሕር በሚተላለፉ መርከቦች ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ እንደነበር ይታወሳል።

  4. በእርግጥ አሜሪካ በኢራን ላይ የእግረኛ ወታደሮች ጥቃት ልትከፍት ነው?

    አሜሪካ ወደ ባሕረ ሰላጤው በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን እና ተጨማሪ የጦር መርከብ ማሰማራቷን ተከትሎ የእግረኛ ወታደሮች ጥቃት ልትከፍት የመሆኑ ጉዳይ እየተነገረ ነው።

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤም አሜሪካ የምድር ኃይል ጥቃት ለመፈጸም በምሥጢር እየተዘጋጀች መሆኑን ሲናገሩ፣ ዋሽንግተን ፖስት ደግሞ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ለእግረኛ ጥቃት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ዘግቧል።

    ይህንን የአሜሪካንን የእግረኛ ወታደሮች ጥቃት በተመለከተ የአገሪቱ ባለሥልጣናት አስካሁን ምን አሉ?

    ከሳምንታት በፊት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ: "ወደየትም ቦታ ወታደሮችን አልክም" ካሉ በኋላ ጨምረውም "የምልክ ከሆነ ደግሞ በእርግጠኝነት አልነግርህም" በማለት ነገሩን አድበስብሰውታል።

    ባለፈው አርብ ደግሞ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እንደተናገሩት አሜሪካ “እግረኛ ወታደሮችን ማሰማራት ሳያስፈልጋት” ዓላማዋን ማሳካት ትችላለች ብለዋል።

    ባለፉት ቀናት ወደ ባሕረ ሰላጤው የተሰማሩት ወታደሮች ጉዳይም ለፕሬዝዳንት ትራምፕ አማራጮችን ለመስጠት ነው በማለት “ለሚፈጠሩ ያልታሰቡ ሁኔታዎች ዝግጁ ለመሆን. . . ሁልጊዜም ለፕሬዝዳንቱ አመቺ ሁኔታን ማመቻቸት ነው” ብለዋል።

    ቅዳሜ ዕለት 3,500 የሚሆኑ የሠራዊቱ አባላትን የሚይዘው ዩኤስኤስ ትሪፖሊ የተባለው የጦር መርከብ ወደ አካባቢው መረድሱን የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ አስታውቋል።

  5. ወሳኝ ተቋሞቻቸው የኢራን ዒላማ የሆኑባቸው ባሕረ ሰላጤው አገራት

    በኢራን ላይ አሜሪካ እና እስራኤል የሚፈጽሙት እና በአጸፋው ኢራን በአካበቢው አገራት ላይ የምትፈጽመው ጥቃት ባለፉት 24 ሰዓታት በቁልፍ ተቋማት ላይ ጭምር ቀጥሏል።

    ትናንት ቅዳሜ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በሳምንቱ ውስጥ ከኢራን በኩል ከተፈጸሙባት ጥቃቶች ከፍተኛው የባለስቲክ ሚሳዔል አጋጥሟታል።

    ኤምሬትስ ግሎባል አልሙኒየም የተባለው ተቋም አቡ ዳቢ ውስጥ በሚገኘው ዋነኛው ማምረቻው ላይ በተፈጸመ ጥቃት ከባድ ጉዳት እንደደረሰበት እና በርካታ ሠራተኞቹ መቁሰላቸውን አስታውቋል።

    በዓለም ላይ ካሉ ትላልቅ አምራቾች መካከል አንዱ የሆነው የባህሬን የአልሙኒየም ማምረቻ ተመሳሳይ ጥቃት ተፈጽሞበታል።

    በኩዌት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በተፈጸመው ጥቃት የራዳር መቆጣጠሪያ ሥርዓቱ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ተዘግቧል።

    ከአሜሪካ ጋር ባላቸው የቀረበ ግንኙነት ምክንያት እና የጦር ሰፈሮቿን በማስተናገዳቸው ምክንያት የኢራን የበቀል ጥቃት ዒላማ የሆኑት የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት የጦርነቱ ቀጥተኛ ገፈት ቀማሾች ሆነዋል።

    የኢራን ሚሳዔሎች እና ድሮኖች የነዳጅ ተቋሞቻቸውን ከመምታታቸው በተጨማሪ የሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋቷ ምርታቸውን ለመሸጥ ተቸግረው ምጣኔ ሀብታዊ ኪሳራ እየገጠማቸው ነው።

    ጦርነቱ እንዲቆም እየጠየቁ ያሉት የባሕረ ሰላጤው አገራት በአሜሪካ ዕቅድ መሠረት ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው ድርደር ውስጥ ለመሳተፍ እየጠየቁ ነው።

    በኢራን ላይ በተከፈተው ጦርነት ሰበብ ቀውስ የገጠማቸው አገራቱ ወደፊት ከአሜሪካ እና ከኢራን ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ላይ የተለያየ አቋም ይዘዋል።

  6. ከሆርሙዝ ወሽመጥ በተጨማሪ በቀይ ባሕር ላይ የተደቀነው ሌላው ስጋት

    በመካከለኛው ምሥራቅ የኢራን ወዳጅ ከሆኑ ቡድኖች መከካል አንዱ የሆነው እና ድንበሮችን አቋርጦ አስራኤል መድረስ የሚችሉ መሳሪያዎችን የታጠቀው የየመኑ ሁቲ ለአንድ ወር ድምጹን አጥፍቶ ቆይቶ በእስራኤል ላይ ጥቃት መፈጸም ጀምሯል።

    ሁቲዎች ከሁለት ዓመት በፊት እስራኤል በሐማስ ላይ ጦርነት እያካሄደች በነበረበት ጊዜ ለሐማስ ያለውን አጋርነት በእስራኤል ላይ የድሮን እና የሚሳዔል ጥቃቶችን በተደጋጋሚ ከመፈጸሙ በተጨማሪ በቀይ ባሕር በኩል በሚተላለፉ መርከቦች ላይ ጥቃት ከፍቶ ነበር።

    በወቅቱ የአሜሪካ እና የእስራኤል እንዲሁም የሌሎችን ምዕራባውያን መርከቦችን ዒላማ አድርጎ ጉዳት ከማድረጉ በተጨማሪ በጥቃቱ የሰጠሙ መርከቦች አሉ።

    ሁቲዎች በቀይ ባሕር በኩል በሚያልፉ መርከቦች ላይ በሚፈጽሙት ጥቃት ምክንያት የንግድ መርከቦች እንቅስቃሴ በመስተጓጎሉ የባሕር ትራንስፖርት ጉዞ በሌላ አቅጣጫ እንዲሆን በማስገደድ ወጪን ከመጨመሩ ባሻገር የሸቀጦችን እንቅስቃሴ አደናቅፎ ነበር።

    አሁንም ሁቲዎች ኢራንን በመደገፍ በመርከቦች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ ከሆነ በኢራን በተዘጋው የሆርሙዝ ወሽመጥ ምክንያት የተፈጠረውን ዓለም አቀፍ ቀውስ የበለጠ ያወሳስበዋል።

    ሁቲዎች ጠላት በሚሏት እስራኤል ላይ ጥቃታቸውን እንደሚቀጥሉ እና በቀይ ባሕር በኩል በሚተላለፉ መርከቦች ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ አሳውቀዋል።

    ይህ ደግሞ ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከእስያ ተነስተው በቀይ ባሕር በኩል ወደ ምሥራቅ እና ሰሜን አፍሪካ እንዲሁም ወደ አውሮፓ የሚጓዙ መርከቦች ጉዟቸውን በቀናት በማራዘም ውጪያቸውን በሚጨምረው በደቡብ አፍሪካ በኩል ለመጓዝ እንዲገደዱ ያደርጋል።

    የሁቲዎች ቀይ ባሕር ላይ ጥቃት መፈጸም ከጀመሩ ኢራን የተከፈተባትን ጥቃት ተከትሎ በዘጋችው የሆርሙዝ ወሽመጥ ምክንያት የተፈጠረውን ዓለም አቀፍ ቀውስ ያወሳስበዋል።

  7. አሜሪካ የመደራደር ፍላጎቷን እየገለጸች ለእግረኛ ጥቃት እየተዘጋጀች ነው - የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ

    በኢራን መንግሥት ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ተጽእኖ ካላቸው ፖለቲከኞች መካከል አንዱ የሆኑት የአገሪቱ ፓርላማ አፈ ጉባኤ አሜሪካ የምድር ጥቃት ለመክፈት እየተዘጋጀች ነው ሲሉ ከሰሱ።

    አፈ ጉባኤው ሞሐማድ ባግሄር ጋሊባፍ በኢራን ላይ የተከፈተውን ጦርነት አንደኛ ወር በማስመለክት መንግሥታዊው ኢርና የዜና አገልግሎትን ጨምሮ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ላይ በቀረበነው መልዕክት ላይ ነው ይህንን ያሉት።

    አፈ ጉባኤው እንዳሉት “ጠላታችን በይፋ ስለድርድር እየተናገረ፣ በምሥጢር የእግረኛ ሠራዊት ጥቃት ለመፈጸም እያሴረ ነው” ሲሉ ከስሰዋል።

    ጨምረውም አሜሪካ ድርድር በማለት ያቀረበችውን ባለ 15 ነጥብ የድርድር ነጥብን “በጦርነት ልታሳካው ያልቻለችውን ፍላጎቷ” ናቸው በማለት ተችተዋል።

    አፈ ጉባኤው ጋሊባፍ በእግረኛ ወታደሮች የምድር ላይ ጥቃት የሚከፈት ከሆነ የኢራን ኃይሎች “የአሜሪካ ወታደሮች መሬታችንን ሲረግጡ እሳት ሊያዘንቡባቸው እየጠበቁ ነው” ብለዋል።

    ትራምፕ በተደጋጋሚ ያቀረቡትን የኢራንን እጅ መስጠት በተመለከተ አፈ ጉባኤ በአረብኛ ቋንቋ የአገራቸው ምላሽ “ግልጽ” ነው በማለት “ውርደትን” እንደማይቀበሉ ገልጸዋል።

    አንዳንድ ያልተረጋገጡ ዘገባዎች እንደሚሉት የትራምፕ አስተዳደር ጋሊባፍ ቀጣይ የአገሪቱ መሪ ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ ያምናል።

  8. እስራኤል ሊባኖስ ውስጥ ሦስት ጋዜጠኞችን ገደለች

    የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ በአንድ መኪና ላይ አነጣጥሮ በፈጸመው ጥቃት ሦስት ሊባኖሳውያን ጋዜጠኞችን ገለደ።

    ጃዚኒ በተባለችው ከተማ ውስጥ በተፈጸመው ጥቃት የሄዝቦላህ የቴሌቪዥን ጣቢያ አል ማናር ዘጋቢ አሊ ሾይብ እንዲሁም የአል ማዳይን ዘጋቢዎቹ ፋጢማ እና ሞሐመድ ፌቶኒ ተገድለዋል።

    ቅዳሜ ምሽት የጋዜጠኞቹን ግድያ የሚቃወም ሰልፍ በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ውስጥ ተካሂዷል።

    ግድያውን የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ “ቀጣናው እና ለዓለም ለመገናኛ ብዙኃን ማኅበረሰቡ ከባድ ጉዳት ነው” ብለዋል።

    አራግቺ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባወጡት ጽሁፍ ጥቃቱን “ግልጽ የታሰበበት ግድያ” እና “እውነታን የሚዘግቡትን ዝም ለማሰኘት” የሚደረግ ሙከራ ነው ብለዋል።

    የእስራኤል ጦር በፈጸመው ጥቃት አሊ ሾይብን መግደሉን ያረጋገጠ ሲሆን፣ ነገር ግን አሊ በጋዜጠኛ ስም የሄዝቦላ ተልዕኮ ፈጻሚ ነው ሲል ከስሶታል።

    ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ እስራኤል ሊባኖስ ውስጥ ጋዜጠኞችን ዒላማ በማድረግ ስትከሰስ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን የቢቢሲ የመካከለኛው ምሥራቅ ወኪል ገልጿል።

  9. የአሜሪካ ጦር መርከብ እና ወታደሮች ቅዳሜ መካከለኛው ምሥራቅ ደረሱ

    በባሕረ ሰላጤው የሚካሄደው ጦርነት ሁለተኛ ወሩን በጀመረበት በአሁኑ ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ የአሜሪካ ወታደሮች እና የጦር መርከብ ቅዳሜ ዕለት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ መድረሳቸው ተዘገበ።

    በኢራን ላይ የሚካሄደውን ጦርነት ለማቆም ድርድር ይደረጋል እየተባለ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ተጨማሪ ወታደሮች ወደ አካበቢው መድረሳቸው ያለውን ስጋት ያባብሰዋል ተብሎ ተሰግቷል።

    ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ቀደም ሲል እንደዘገበው የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር በኢራን ውስጥ ለሳምንታት ለሚደረግ የእግረኛ ዘመቻ እየተዘጋጀ ነው። ነገር ግን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለዕቅዱ ይሁንታቸውን መግለጻቸው አልታወቀም።

    ወደ ቀጣናው አሁን መድረሳቸው ከተነገረው ወታደሮች በተጨማሪም ዩኤስኤስ ትሪፖሊ የተባለቸው የጦር መርከብ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ መድረሷን የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ አስታውቋል።

    ዕዙ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ባሠራጨው መረጃ ላይ መርከቧ 3,500 የሚሆኑ መርከበኞች እና የባሕር ኃይል ወታደሮች እንዲሁም የትራንስፖርት እና የወጊያ አውሮፕላኖች ይዛለች።

  10. አሜሪካ በአንድ ወር ኢራን ውስጥ ከ11 ሺህ በላይ ዒላማዎችን መታሁ አለች

    የአሜሪካ ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) በኢራን ላይ ‘ኤፒክ ፊዩሪ’ በሚል በከፈተው እና አንድ ወር በሞላው ጥቃት በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ከ11 ሺህ በላይ በሚሆኑ ዒላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታወቀ።

    በአንድ ወር ውስጥ በኢራን ላይ ከ11 ሺህ በላይ የጥቃት በረራዎች መካሄዳቸውን እና ከ150 በላይ የኢራን የጦር መርከቦች እንደወደሙ ወይም ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውቋል።

    በዕዙ መግለጫ ላይ የአሜሪካ ኃይሎች በዋናነት ዒላማ ያደረጉት “የኢራን አገዛዝን የድኅነንት ተቋማት እና ተጨባጭ ስጋት የደቀኑ ቦታዎችን” መሆኑን አመለክቷል።

    በሪፖርቱ ላይ በኢራን ግዛት ላይ ከባሕር በመነሳት ጥቃት መፈጸም የሚችሉ መርከቦች እና ጀልባዎች ጥቃቶችን በመምራት መሳተፋቸውን አመልክቷል።

    ከአንድ ወር በፊት እስራኤል እና አሜሪካ በኢራን በከፈቱት ጦርነት በአገሪቱ ውስጥ በርካታ ተቋማት ላይ ጥቃት እየተፈጸመ ሲሆን፣ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የኢራን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

    ምንም እንኳን በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ድርድር ይጀመራል ተብሎ ቢጠበቅም ጦርነቱ አሁንም አልቆመም።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት እየፈጸሙ ሲሆን፣ ኢራንም በአጸፋው በእስራኤል ላይ እና የአሜሪካ አጋር በሆኑት የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ላይ እየፈጸመች ነው።

  11. ኢራን የእስራኤል እና የአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎችን ለመምታት ዛተች

    በዋና ከተማዋ ቴህራን ውስጥ በሚገኘው የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የእስአኤል እና የአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎችን ዒላማ እንደሚያደርግ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ዛተ።

    በኢራን ዩኒቨርስቲዎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ለመበቀል በቀጣናው የሚገኙ የሁለቱ አገራት ሁለት ዩኒቨርስቲዎች “በአጸፋ ጥቃት እስኪመቱ ድረስ ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች ተገቢ ዒላማዎች ይሆናሉ” ሲል ሠራዊቱ አስጠንቅቋል።

    “በመከካለኛው ምሥራቅ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ያሉ ሠራተኞች፣ ተማሪዎች እና በአቅራቢያቸው የሚገኙ ነዋሪዎች ለደኅነንታቸው ሲሉ ከዩኒቨርስቲዎቹ በአንድ ኪሎ ሜትር እዲርቁ እንመክለራን።”

    የአብዮታዊ ዘቡ መግለጫ ጨምሮም አሜሪካ በቀጣናው በሚገኙ ተቋማቷ ላይ የሚፈጸም የአጸፋ ጥቃትን ለማስቀረት የምትፈልግ ከሆነ በኢራን ዩኒቨርስቲዎች ላይ የደረሱትን ጥቃቶች አስከ ማክሰኞ እኩለ ቀን ድረስ ማውገዝ አለባት ብሏል።

  12. አሜሪካ ኢራን ውስጥ የእግረኛ ወታደሮች ዘመቻ ለማካሄድ እየተዘጋጀች መሆኑ ተነገረ

    የአሜሪካ የመከከላያ ሚኒስቴር ፔንታገን በኢራን ውስጥ ለሳምንታት የሚቆይ የእግረኛ ሠራዊት ዘመቻ ለማካሄድ እየተዘጋጀች መሆኗን ዋሽንግተን ፖስት ዘገበ።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ ጋዜጣው እንደዘገበው ወታደሮችን ማሰማራትን የተመለከተውን የፔንታገን ዕቅድ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስለማጽደቃቸው ግልጽ አይደለም።

    ነገር ግን የተዘጋጀው እግረኛ ወታደሮችን የማሰማራት ዕቅድ ሙሉ ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል የወረራ ዘመቻ ሳይሆን በልዩ ተልዕኮ ኃይሎች እና በመደበኛ እግረኛ ወታደሮች አማካኝነት የሚፈጸሙ ጥቃቶችን የሚመለከት መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ።

    በአሁኑ ጊዜ ከአራት ሺህ በላይ የባሕር ኃይል ወታደሮችን የያዙ ተጨማሪ የጦር መርከቦች ወደ ባሕረ ሰላጤው እያመሩ ሲሆን፣ ሌሎች የአየር ወለድ ወታደሮች ደግሞ በተጠንቀቅ ላይ ናቸው። በተጨማሪም ሌሎች ኃይሎችንም ለማሰማራት ውይይት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።

    ቢቢሲ ወደ ኢራን እግረኛ ሠራዊት ለማዝመት ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑ የፕሬዝዳንት ትራምፕ ጽህፈት ቤት እና የመከላከያ ሚኒስቴሩ አስተያየት እንዲሰጥ ጠይቋል።

  13. የየመኑ ታጣቂ ቡድን በእስራኤል ላይ ሁለተኛውን ጥቃት መፈጸሙን አስታወቀ

    የየመን ታጣቂ ቡድን ሁቲ ለሁለተኛ ጊዜ በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ በሚገኙ አካባቢዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታወቁ።

    በየመን ጦር ሠራዊት ውስጥ የሚገኘው የሁቲ ታጣቂ ኃይል ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ እንዳስታወቀው ቡድኑ “በበርካታ የእስራኤል ወሳኝ ወታደራዊ ቦታዎች ላይ የክሩዝ ሚሳዔሎች እና የድሮኖች” ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

    ጨምሮም ጥቃቶቹ ከኢራን እና ከሄዝቦላህ ወታደራዊ ዘመቻዎች ጋር “ተቀናጅተው” የተካሄዱ መሆናቸውን እና “የታሰባላቸውን ዓላማም አሳክተዋል” ብሏል።

    “ወንጀለኛው ጠላት የሚፈጽማቸው ጥቃቶች እና ወረራ አስከሚቆም ድረስ” በቀጣይ ቀናትም ተጨማሪ ጥቃቶች እንደሚቀጥሉ ቡድኑ አስታውቋል።

    የቡድኑ ቃል አቀባይ በቴሌግራም ገጹ በኩል ጥቃት መፈጸሙን ከማስታወቁ በፊት የእስራኤል እና የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ሁለተኛው ጥቃት መፈጸሙን ዘግበው ነበር።

    በኢራን ላይ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ከጀመረ ከአንድ ወር በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁቲዎች በእስራኤል ላይ ጥቃት የፈጸሙት ቅዳሜ ዕለት ነው።

    እስራኤል ጥቃቱ መፈጸሙን አረጋግጣ ከየመን በኩል የተተኮሰ ሚሳዔልን ማክሸፏንም አስታውቃለች።

  14. የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ከኢራኑ ፕሬዚዳንት ጋር ተነጋገሩ

    የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ ከኢራኑ ፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ጋር በስልክ መወያየታቸውን ገለጹ።

    ሁለቱ ባለሥልጣናት ከአንድ ሰዓት በላይ በፈጀው የስልክ ውይይታቸው “ዝርዝር ጉዳዮችን" መወያየታቸውን ገልጸዋል።

    ሻሪፍ በኤክስ ገጻቸው ላይ ከአሜሪካ እና የባህረ ሰላጤው አገራት ጋር "ውይይቶችን በማመቻቸት እና ግጭቶችን በማርገብ" ዙሪያ በማሳተፍ ረገድ “ፓኪስታን እያደረገች ስላለው ቀጣይነት ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አሳውቄያቸዋለሁ” ሲሉ አስፍረዋል።

    ፓኪስታን ከዚህ ወደም በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሚደረግ ንግግርን ለማዘጋጀት ጥያቄ አቅርባ ነበር።

    ሻሪፍ እስራኤል በቴህራን ላይ የምትፈጽመውን ድብደባ አውግዘው ፓኪስታን “ከጀግኖች የኢራን ሕዝቦች ጎን ትቆማለች” ብለዋል።

  15. ሁቲዎች ቀይ ባሕርን የሚያጠቁ ከሆነ ሁኔታው የከፋ ሊሆን ይችላል - የመካከለኛው ምሥራቅ ተንታኝ

    በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች ባለፈው አንድ ወር እጃቸውን ሰብስበው የተቀመጡበትን የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት በዛሬው ዕለት ተቀላቅለዋል። የየመኖቹ ታጣቂዎች ወደ ኢራን ሚሳዔል ማስወንጨፋቸውን ተናግረዋል። የእስራኤል መከላከያ ሠራዊትም ከየመን ሚሳዔል መወንጨፉን ገልጾ ነበር።

    በቻታም ሀውስ የምርምር ባልደረባ የሆኑት ፋሬያ አል ሙስሊም “በሌላኛው ወሳኝ ዓለም አቀፍ የንግድ መስመር” ላይ የተቀመጡት ሁቲዎች በኢራን ጦርነት ውስጥ መሳተፋቸው “ትልቅ ትርጉም” እንዳለው ተናግረዋል።

    ሁቲዎች እስካሁን ቀይ ባሕር ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ አለመግለጻቸውን ተመራማሪው ‘ቱዴይ’ ለተሰኘው የቢቢሲ የራዲዮ ፕሮግራም አስረድተዋል። ባለሙያው ሁቲዎች “ራሳቸውን ከሌላ የአሜሪካ ጥቃት ለማትረፍ እየሞከሩ” ሊሆን ይችላል የሚል ምልከታ አላቸው።

    የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ሁቲዎች በቀጣናው ጥቃት እንዳይፈጽሚ ለማድረግ ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር በመሆን በ2025 በቦንብ የመደብደብ ዘመቻ ከፍቶ ነበር።

    ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ሙሉ በሙሉ ለመዝጋት እየዛተች ባለችበት በዚህ ጊዜ ሁቲዎች የቀይ ባሕርን ጉዞ የሚያግዱ ከሆነ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ለባለሙያው ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። አል ሙስሊም “አስፈሪ ነው። አሁንም አስፈሪ ቅዠት ውስጥ ነው ያለነው፤ ይሄ ደግሞ ከቅዠቶች ሁሉ የከፋው ነው” ብለዋል።

    የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ሁቲዎች በቀይ ባሕር የሚያልፉ መርከቦችን ሲያጠቁ እና ወደ እስራኤል ሚሳዔል ሲተኩሱ ነበር። ይህንን እርምጃ የወሰዱትም ለፍልስጤማውያን ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት እንደሆነ በወቅቱ ገልጸዋል።

    ሁቲዎች በባሕር መስመሩ የሚያልፉ የንግድ መርከቦችን በድሮን እና በሚሳዔል ሲያጠቁ ነበር። ጀልባዎች እና ሄሊኮፕተር በመጠቀምም በቀይ ባሕር መጓዝን አስቸጋሪ አድርገውት ነበር።

    በዚህም ምክንያት ኩባንያዎች የመርከቦቻቸውን የቀይ ባሕር መስመር በመቀየር በሌላ አቅጣጫ ረጅም ጉዞ ለማድረግ ተገድደዋል።

  16. ሳዑዲ አረቢያ፣ ቱርክ እና ግብፅ በቀጣናው ያለውን ግጭት ለማርገብ በፓኪስታን ሊወያዩ ነው

    የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢሻቅ ዳር አገራቸው የሳዑዲ አረቢያ፣ የቱርክ እና የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን እአአ ከመጋቢት 29-30 በዋና ከተማዋ ኢስላማባድ እንደምታስተናግድ ገለፁ።

    ሚኒስትሮቹ “ቀጣናው ውስጥ ያለውን ውጥረት ለማርገብ በሚደረጉ ጥረቶች ላይ” አተኩረው እንደሚወያዩ ዳር በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።

    የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውይይቱ በፓኪስታን ዋና ከተማ እንደሚካሄድ እና ለዚህም ሚኒስትሩ ወደ ስፍራው ማምራታቸውን የሚያረጋግጥ መግለጫ አውጥቷል።

    ፓኪስታን በቀጣናው የሰላም አደራዳሪነት ሚና ለመጫወት ጥረት እያደረገች ነው።

    ኢስላማባድ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሚደረገውን ውይይት ለማስተናገድ ሀሳብ አቅርባለች። እነዚህ ውይይቶች ይካሄዱ እንደሆነ እስካሁን ምንም ዓይነት ማረጋገጫ አልተገኘም።

    በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ"በፓኪስታን በኩል በሚተላለፉ መልዕክቶች" አማካኝነት ሁለቱ አገራት "ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ውይይቶች እያደረጉ" መሆኑን ገልጸው ነበር።

    ትራምፕ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ የጻፉትን የኤክስ ልጥፍ ፎቶ በማንሳት በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ አጋርተዋል።

    ሻሪፍ በጻፉት ጽሑፍ ፓኪስታን የሚደረጉ ንግግሮችን ለማስተናገድ "ዝግጁ" እንደሆነች ተናግረዋል።

  17. ሩሲያ በዩክሬን የተጠቀመችውን የድሮን ቴክኖሎጂ በማሻሻል ለኢራን እያቀረበች መሆኑ ተዘገበ

    ሩሲያ፤ የተለያዩ አይነት ድሮኖችን ለኢራን እያቀረበች መሆኑን ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ባለሥልጣናት መስማቱን አሶሺዬትድ ፕሬስ ዜና ወኪል ዘገበ። ከተላኩት መሣሪያዎች መካከል ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ ከኢራን የቀረበላትን የድሮን ቴክኖሎጂ የተሻሻለ ስሪት እንደሚገኝበትም ተገልጿል።

    ጦርነት የተከፈተባት ኢራን ላለፈው አንድ ወር ወደ እስራኤል፣ የባህረ ሰላጤው ጎረቤቶቿ እና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ አሜሪካ የጦር ሰፈሮች ድሮኖችን በመላክ ጥቃት ስትፈጽም ቆይታለች። ኢራን በራሷ የሻሄድ ድሮን ክምችት አላት።

    ሩሲያ በበኩሏ ከዚህ ቀደም ቴህራን ያገኘቻቸውን የመጓዝ አቅማቸውን ጭምር በመጨመር የድሮኖቹን ዲዛይን ማሻሻሏን የኤፒ ዘገባ ያመለክታል።

    የሩሲያ እና ኢራን ባለሥልጣናት ድሮኖች ከሞስኮ ወደ ቴህራን የሚተላለፉበትን መንገድ በተመለከተ ውይይት ማድረጋቸውን አንድ አውሮፓ የስላላ ኃላፊ ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል። የአሜሪካ የመከላከያ ባለሥልጣን በበኩላቸው፤ ይህ ድሮን የማጓጓዝ ዕቅድ የአንድ ጊዜ ይሁን በተከታታይ የሚደረግ ግልጽ አለመሆኑን ተናግረዋል ተብሏል።

    ዘገባው እንደሚያስረዳው ሁለቱም ባለሥልጣናት ምን ያህል ድሮኖች እንደሚላኩ ወይም ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ አልገለጹም። ሌላ የአውሮፓ ባለሥልጣን በበኩላቸው ብዛቱ አነስተኛ የሆነ ድሮን በጦርነቱ ውስጥ የሚኖረው ውጤት አነስተኛ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

  18. የኩዌት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በድሮን ተመታ

    የኩዌት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በበርካታ ድሮኖች ጥቃት እንደተፈጸመበት የአገሪቱ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ቃል አቀባይ ለኩዌት የዜና ወኪል ተናገሩ።

    በአየር ማረፊያው ላይ ደረሰው ጉዳት ውስን እንደሆነ እና በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን መናገራቸውንም ተገልጿል። ጉዳቱ የደረሰው በአየር ማረፊያው የራዳር ስርዓት ላይ እንደሆነ ሮይተርስ የዜና ወኪሉን ጠቅሶ ዘግቧል።

    የኩዌት ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ጥቃት ሲፈጸምበት ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ረቡዕ ዕለት በኢራን ድሮን በተፈጸመ ጥቃት የአገሪቱን የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዒላማ ተደርጎ ነበር።

  19. በሊባኖስ የተፈጸመን ጥቃት የሚያሳይ ምስል

    የሊባኖስ መንግሥታዊ የዜና ወኪል እስራኤል በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል በሚገኙ በርካታ ከተሞች ላይ ተከታታይ ጥቃት ማድረሷን ዘግቧል።

    በሊባኖስ የሚንቀሳቀሰው እና በኢራን የሚደገፈው የሄዝቦላህ ቡድን፣ በሰሜናዊ እስራኤል የሚገኙ የቴል አቪቭ ወታደራዊ ስፍራዎችን ዒላማ ያደረገ ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል።

  20. ሌሊቱን በባሕረ ሰላጤው አገራት እና ኢራን ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች

    በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን የሚሳዔል ጥቃቶች ሌሊቱን መቀጠላቸው ተሰምቷል። ኢራን በበኩሏ ወደ እስራኤል እና የባሕረ ሰላጤው አገራት ሚሳዔሎች መተኮሷ ተገልጿል።

    • የእስራኤል አምቡላንስ አገልግሎት አርብ ዕለት ኢራን ያስወነጨፈችው ሚሳዔል በማዕከላዊ እስራኤል በርካቶች ላይ ጉዳት ማድረሱን እና አንድ የ52 ዓመት ሰው መሞታቸውን አስታውቋል።
    • የእስራኤል ጦር በበኩሉ ከየመን የተወነጨፈ ሚሳዔልን ማክሸፉን ገልጿል።
    • በደቡባዊ ኦማን በሳላህ ወደብ ላይ በተፈጸመ ሁለት የድሮን ጥቃት አንድ የውጭ አገር ዜጋ መጎዳቱን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
    • በዩኤኢ፣ ኩዌት እና ባሕሬን እንዲሁ የአየር መቃወሚያዎች የሚተኮሱ ድሮኖችን ማክሸፋቸው ተገልጿል። በዩኤኢ አቡዳቢ የሚሳዔል ስብርባሪ አምስት ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሷል።
    • የሳዑዲ አረቢያ መከላከያ ሚኒስቴር ወደ ሪያድ የተተኮሱ ሦስት ድሮኖችን እና ባለስቲክ ሚሳዔል ማክሸፉን አስታውቋል። አርብ ዕለት በልዑል የአየር ኃይል ላይ በደረሰ ጥቃት 12 የአሜሪካ ወታደሮች መጎዳታቸው ተሰምቷል።