የአሜሪካን ጦር ጄት አብራሪ በኢራን ግዛት ውስጥ ፈልጎ ለማግኘት የሚደረገው 'አስፈሪ እና አደገኛ' ዘመቻ
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስካሁን የወጡ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ኢራን ውስጥ ተመትቶ የወደቀው የዩኤስ ኤፍ-15 ተዋጊ አውሮፕላን አብራሪን በሕይወት ማግኘት ተችሏል።
ይህ እውነት መሆኑ ከተረጋገጠ አሜሪካ ከአስርት ዓመታት በላይ ባካሄደችው ረዥም የጦርነት ታሪክ ውስጥ በጠላት ጦር ቀጣና ውስጥ ተመትቶ የወደቀ ወታደሯን ፈልጎ በማዳን ስኬት ውስጥ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ሆኖ ይመዘገባል።
ይሁን እንጂ አሁንም ሁለተኛው የተዋጊ ጄቱ ባልደረባ አልተገኘም።
በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ በኢራን ግዛት ውስጥ የሚደረገው ፍለጋ እንደቀጠለ መሆኑን ዘግቧል።
በጦርነት ውስጥ ተመትቶ የወደቀን ፈልጎ የማዳን ተልዕኮ የአሜሪካ እና አጋር ጦር የሚሳተፍበት፣ እጅግ ውስብስብ እና ከጊዜ ጋር ሩጫ የሚካሄድበት ዘመቻ ነው።
በአሜሪካ አየር ኃይል ውስጥ ለዚሁ ተብሎ የሰለጠኑ ልዩ ወታደሮች ያሉ ሲሆን ለቅድመ ጥንቃቄ በሚል ውጊያ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች አስቀድመው ይሰማራሉ።
በውጊያ ወቅት ፈልጎ ማዳን ሲባል ምን ማለት ነው?
በቀላል ቋንቋ ይህ ተልዕኮ በውጊያ ወቅት ተመትቶ የወደቀን አብራሪ ወይንም በጠላት ጦር ተቆርጦ የቀረን ሠራዊት የመፈለግ፣ ድጋፍ የመስጠት እና የማትረፍ ዘመቻ ነው።
ይህ ከተለመደው በሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ወይም በአደጋ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ፈልጎ የማግኘት ጥረት በተቃራኒው ጦርነት በሚካሄድባቸው እና በአወዛጋቢ ስፍራዎች የሚካሄድ ዘመቻ ነው።
አንዳንድ ጊዜ አርብ ዕለት በኢራን ግዛት እንደሆነው ሁሉ ፍለጋው እና በሕይወት የማግኘቱ ሥራ የሚሰራው በጠላት ግዛት ውስጥ ዘልቆ በመግባት ይሆናል።
የፍለጋ እና በሕይወት የማትረፍ ዘመቻው የሚካሄደው በሂሊኮፕተር ሲሆን አብሮም በበረራ ላይ ነዳጅ መሙላት የሚያስችል አውሮፕላን እንዲሁም በመንገድ ላይ ከጠላት ጥቃት ቢገጥም ጥቃት የሚፈጽም እና አካባቢውን የሚቃኝ አውሮፕላን ድጋፍ ለመስጠት ይከተላሉ።
የቀድሞ አዛዥ እና የዚህ ልዩ ኃይል አባል የነበረ ግለሰብ ለሲቢኤስ እንደተናገረው በኢራን ውስጥ እንደተካሄደው የፍለጋ እና በሕይወት የማዳን ተግባር ቢያንስ በብላክ ሆክ ሂሊኮፕተር የሚታገዙ 24 አባላት ይሳተፉበታል።
ይህ የፍለጋ ቡድን አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ከአውሮፕላኑ ላይ ዘሎ የሚወርድ ሲሆን መሬት ካረፈ በኋላም ከጠፋው የአውሮፕላን አብራሪ ጋር ግንኙነት መፍጠር ቀዳሚ ተግባሩ ይሆናል።
የጠፋው የአውሮፕላን አብራሪ ከተገኘ በኋላ አስፈላጊ ከሆነ የሕክምና ድጋፍ መስጠት፣ ከጠላት ዕይታ መሰወር እና አካባቢውን ለቅቀው የሚወጡበት ስፍራ ላይ መገኘት ይኖርባቸዋል ሲል ሲቢኤስ ዘግቧል።
የቀድሞው አዛዥ ለሲቢኤስ "አስፈሪ እና አደገኛ ማለት ሁኔታውን ማቃለል ነው" ሲል ተናግሯል።
አክሎም "በመላው ዓለም ይህንን ለማከናወን ነው የሰለጠኑት። ስዊስ አርሚ ናይቭስ ኦፍ ዘ ኤር ፎርስ (የአየር ኃይሉ የስዊዝ ቢላ) በመባል ነው የሚታወቁት" ብሏል።
አርብ ዕለት ኢራን ውስጥ የተቀረጸ እና ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ ተንቀሳቃሽ ምስል የአሜሪካ ሂሊኮፕተር እና ቢያንስ አንድ ነዳጅ የሚሞላ አውሮፕላን በኢራን ኩህዜስታን አውራጃ ሰማይ ላይ ሲበሩ ታይተዋል።
ተመትቶ የወደቀውን የጦር ጄት አብራሪ የሚፈልገው የአሜሪካ አየር ኃይል ብቻ አይደለም። የኢራን ጦርም ግለሰቡን በቁጥጥር ስር ለማዋል ያለበትን ማሰስ እና ማግኘት ይፈልጋል።
ዘመቻው ጠላት ወደ ስፍራው አብራሪውን ለመፈለግ እና ለማግኘት የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ከጊዜ ጋር ግብግብ የሚገጠምበት ነው።
የቀድሞው የአሜሪካ ባሕር ኃይል ልዩ ዘመቻ ስፔሻሊስት ጆናታን ሃኬት ለቢቢሲ ወርልድ ቱናይት ፕሮግራም እንደተናገረው የፍለጋ ቡድኑ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር በሕይወት መኖሩን ማረጋገጥ ነው።
"ግለሰቡ ለመጨረሻ ጊዜ ነበር ከሚባልበት ስፍራ በመነሳት ፍለጋቸውን ያከናውናሉ፤ ይህ ግን ግለሰቡ በተለያየ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ በአስቸጋሪ መልክዓ ምድር ውስጥ በምን ያህል ፍጥነት መንቀሳቀስ ይችላል የሚለው ላይ ይወሰናል" ሲሉ ሃኬት ተናግሯል።
ሃኬት አክሎም እንዲህ ዓይነቱ በሕይወት የማዳን ተግባር ምናልባት በአካባቢው ያሉ ኃይሎችን የመጠባበቂያ ዕቅድ ለማዘጋጀት በሚል በሕይወት የማዳን ተግባሩ ላይ ድጋፍ እንዲያደርጉ ግንኙነት የሚፈጠርበት "መደበኛ ያልሆነ በድጋፍ የሚደረግ የማዳን ዘመቻ" ሊሆን ይችላል።
ከዚህ ቀደም የተደረጉ በሕይወት የማትረፍ ዘመቻዎች ምን ይመስላሉ?
በጦርነት ወቅት የአሜሪካ አየር ወለዶች የወገን ጦር አባላትን ከአደገኛ ውጊያ መሃል በሕይወት የማውጣት ረዥም ታሪክ አላቸው።
ይህም የአንደኛው የዓለም ጦርነት አብራሪዎች በፈረንሳይ የተከሰከሱ ባልደረቦቻቸውን ለማዳን በድንገት በማረፍ እርምጃ ከወሰዱበት ጊዜ ይጀምራል።
የአሜሪካ ወታደራዊ የፓራሹት ክፍሎች ይህንን ታሪካቸውን የሚመዙት እአአ በ1943 ሁለት የውጊያ ቀዶ ሐኪሞች የቆሰሉ ወታደሮችን ለመርዳት በወቅቱ በርማ በአሁኗ ምያንማር በፓራሹት ወርደው ያካሄዱትን ተልዕኮ ነው።
በዓለም ላይ የመጀመሪያው በሄሊኮፕተር የማዳን ተግባር የተከናወነው ከአንድ ዓመት በኋላ ሲሆን ይህም አንድ የአሜሪካ ሌተናንት ከጃፓን ወታደሮች ጀርባ የወደቁ አራት የአሜሪካን ወታደሮችን ያዳነበት ዘመቻ ነው።
እንደ የስሚዝሶኒያን ኤር ኤንድ ስፔስ መፅሔት ዘገባ ይህ ክስተት ሄሊኮፕተር በጦርነት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለበትን ጊዜም ነበር።
በአሜሪካ ከዚህ ውጊያው በኋላ መደበኛ የፍለጋ እና የማዳን ተልዕኮን የሚወጣ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ተቋቁሟል። ነገር ግን ዘመናዊው የፍለጋ እና የማዳን ዘመቻ የተጀመረው በቬትናም ጦርነት ወቅት ነበር።
ባት 21 በመባል የሚታወቀው አንድ ዘመቻ በሰሜን ቬትናም ወታደሮች የውጊያ ቀጣና ውስጥ ተመትቶ የወደቀን አንድ አውሮፕላን አብራሪ ለማግኘት ሲሞክር በርካታ አውሮፕላኖች እንዲመቱ እና በርካታ አሜሪካውያን እንዲሞቱ አድርጓል።
ይህ ጦርነት በሕይወት ፈልጎ የማዳን ተልዕኮዎችን ዓላማቸውን እና መጠነ ርዕዩን ማግዘፍ አስፈላጊ መሆኑን አሳይቷል።
ጦሩ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ፈልጎ የማዳን ሥራዎችን በሚገባ ለማከናወን የረዱትን ስልቶች እና ሂደቶችን ለማሻሻል ረድቶታል።
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ አየር ኃይል የፍለጋ ልዩ ቡድን
እያንዳንዱ የአሜሪካ ወታደራዊ ክንፍ የራሱ የሆነ ውስን የፍለጋ ቡድን ቢኖረውም፣ የአሜሪካ አየር ኃይል የጦሩ አባላትን ፈልጎ በሕይወት የማዳን ዋና ኃላፊነት አለበት።
ይህ ሥራ በዋናነት የሚካሄደው በወታደራዊው የልዩ ኦፕሬሽን አካል በሆኑት 'ፓራሬስኩ ጃምፐሮች' በመባል በሚታወቁት ነው።
የዚህ ቡድን ዋና መሪ ቃል "እኛ በምናደርገው፣ ሌሎች በሕይወት ሊኖሩ ይችላሉ" የሚል ሲሆን ሥራቸውም የአሜሪካ ጦር አባላትን በጠላት ሰፈር ትቶ ላለመሄድ የሚገቡት ሰፊ ቃል ኪዳን አካል ተደርጎ ይቆጠራል።
እነዚህ ልዩ ኃይሎች በውጊያ እንዲሁም የአደጋ ጊዜ ሕክምና በመስጠትም በሚገባ የሰለጠኑ ናቸው።
የልዩ ኃይል አባላቱ በአሜሪካ ጦር ታሪክ ውስጥ እጅግ ከባድ የሚባለውን የምልመላ እና የስልጠና ሂደት የሚያልፉ ናቸው።
እነዚህ የልዩ ኃይል አባላትን መልምሎ እስከ ማሰልጠን ድረስ ሁለት ዓመት ያህል ሊወስድ ይችላል።
በስልጠናቸው ላይም በፓራሹት መዝለል እንዲሁም በውሃ ውስጥ ስለሚፈጸም ጥቃት፣ በጥቃት ወቅት በሕይወት መትረፍ፣ ችግሮችን መቋቋም እንዲሁም ማምለጥን እና የሕክምና አሰጣጥን ያካተተ ነው።
በውጊያ መካከል ስለሚሰጡ መድሃኒቶች እንዲሁም ውስብስብ ስለሆኑ ዘመቻዎች እና የጦር መሣሪያዎች በቂ ስልጠና ይሰጣቸዋል።
ይህንን ቡድን የሚመሩት ልዩ የውጊያ እና ፈልጎ የማዳን አዛዦች ሲሆኑ በሕይወት የማትረፍ ዘመቻውን ማቀድ፣ ማስተባበር እና የመተግበር ኃላፊነት አለባቸው።
በቅርብ ጊዜ የተከናወኑ በሕይወት የማትረፍ ዘመቻዎች
በጦርነት ቀጣና ውስጥ ተመትተው የወደቁ ወታደሮችን ፈልጎ በሕይወት የማውጣት ተልዕኮን የሚወጡ ቡድኖች በኢራቅ እና አፍጋኒስታን በተደረጉ ጦርነቶች በስፋት ተሰማርተው ነበር።
እነዚህ የልዩ ኃይል አባላት የቆሰሉ ወይም ከውጊያ ቀጣና መውጣት ያለባቸውን የአሜሪካ እና የአጋሮቻቸውን ወታደሮች ለማዳን በሺዎች የሚቆጠሩ ተልእኮዎችን አካሂደዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2005 የአየር ኃይል ልዩ ቡድኖች በአፍጋኒስታን መንደር ውስጥ ጥቃት ከተፈጸመበት እና ሌሎች ሦስት አባላቱ ከተገደሉ በኋላ የቆሰለን የአሜሪካ የባሕር ኃይል አባልን ለማግኘት ተሳትፈዋል። ይህ ክስተት በኋላ ላይ 'ሎን ሰርቫይቨር' በሚል ርዕስ ፊልም ተሰርቷል።
ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ ተመትተው የወደቁ የአሜሪካ አብራሪዎችን ለማግኘት የተደረጉ ዘመቻዎች ጥቂት ናቸው።
እአአ በ1999 በሰርቢያ የኤፍ-117 ተዋጊ አውሮፕላን አብራሪ ተመትቶ ከወደቀ በኋላ ይህ ቡድን ፈልጎ አግኝቶታል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ1995 በቦስኒያ አሜሪካዊው አብራሪ ስኮት ኦግራዲ ተመትቶ ከወደቀ በኋላ ለስድስት ቀናት ራሱን ደብቆ ከቆየ በኋላ የአየር ኃይል እና የባህር ኃይል አባላት ፈልገው ሊያድኑት ችለዋል።
እንዳያመልጥዎ
ከየፈርጁ
በስፋት የተነበቡ
የሚፈልጉት ይዘት የለም