ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካ ይዞታዎች ላይ በፈጸመችው ጥቃት የ800 ሚሊዮን ዶላር ጉዳት አደረሰች
ኢራን በጦርነቱ የመጀመሪያ ሁለት ሳምንታት በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ አሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ በፈጸመችው ጥቃት 800 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ጉዳት ማድረሷን አንድ ትንታኔ አመለከተ።
አብዛኛው ጉዳት የደረሰው አሜሪካ እና እስራኤል ጦርነቱን በከፈቱበት ሳምንት ውስጥ ኢራን በፈጸመችው የመጀመሪያ አጸፋዊ ጥቃት እንደሆነ የስትራቴጂክ እና ዓለም አቀፍ ጥናት ማዕከል (ሲኤስአይኤስ) ሪፖርት እና የቢቢሲ ትንታኔ አመልክቷል።
ይሁን እንጂ ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ የአሜሪካ ይዞታዎች ላይ ያደረሰችው ጉዳት ሙሉ በሙሉ ግልጽ አይደለም።
በአሜሪካ ወታደራዊ መሠረተ ልማት ላይ ደርሷል የተባለው የ800 ሚሊዮን ዶላር ግምታዊ ጉዳት፤ ከዚህ ቀደም በሌሎች ዘገባዎች ከተጠቀሰው አሃዝ ከፍ ያለ ነው። ግጭቱ እየገፋ ሲሄድ አሜሪካ ላይ ምን ያህል ከፍተኛ ወጪ እንደሚወድቅ ማሳያ እንደሚሆን ተገልጿል።።
የሲኤስአይኤስ ከፍተኛ አማካሪ እና የሪፖርቱ ተባባሪ አዘጋጅ የሆኑት ማርክ ካንቺያን "በቀጣው በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ የደረሰው ጉዳት ከተገቢው በታች ነው ሪፖርት የተደረገው" ብለዋል።
"ምንም እንኳን [የአሁኑ ቁጥር] ሰፊ ቢመስልም ተጨማሪ መረጃ እስካልተገኘ ድረስ ሙሉ መጠኑ አይታወቅም" ሲሉም አክለዋል።
በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ከበቢሲ ጥያቄ የቀረበለት ጥያቄ የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር ጦርነቱን እየመራ ወዳለው ማዕከላዊ ዕዝ ጥያቄ ቢመራውም ባለሥልጣናቱ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።
የኢራን የአጸፋ ጥቃት በዮርዳኖስ፣ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ ሌሎች አገራት ውስጥ በሚገኙ የአሜሪካ የአየር መከላከያ እና የሳተላይት መገናኛ ዘዴዎችን እንዲሁም ሌሎች ንብረቶችን ላይ ያነጣጠሩ ናቸው።
ከፍተኛው ጉዳት የደረሰው በዮርዳኖስ በሚገኘው የአየር ኃይል ሰፈር በአሜሪካ የታድ የሚሳዔል መከላከያ ሥርዓት ራዳር ላይ ነው።
በሲኤስኤይኤስ የመከላከያ ክፍል የበጀት መረጃ ግምገማ መሠረት የራዳር ሥርዓቱ ወደ 485 ሚሊዮን ዶላር ያስወጣል። ይህ የአየር መከላከያ ሥርዓት ባለስቲክ ሚሳዔሎችን ከረጅም ርቀት በመለየት ለማምከን የሚያገለግል ነው።
የኢራን ጥቃት 310 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ጉዳት አድርሷል ተብሎ የሚገመተው የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች እና በቀጣናው በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ሕንጻዎች፣ መገልገያዎች እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ላይ ነው።
ኢራን ቢያንስ ሦስት የአየር ኃይል ሰፈሮችን ከአንድ ጊዜ በላይ እንደመታች ቢቢሲ ቬሪፋይ በሳተላይት ምሥሎች ላይ ያደረገው ምርመራ ያሳያል። ተደጋጋሚው ጥቃት ኢራን የተወሰኑ የአሜሪካ ይዞታዎችን ዒላማ ለማድረግ ያደረገችውን ጥረት አጉልቶ ያሳያል። እንዲሁም ሩሲያ በአካባቢው ስላለው የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል መረጃ ለኢራን እንዳጋራች ተዘግቧል።
የሳተላይት ምሥሎች በኩዌት አሊ አል-ሳሊም፣ በኳታር አል-ኡዴይድ እና በሳውዲ አረቢያ ልዑል ሱልጣን በተባሉት ሦስቱን የአየር ኃይል ሰፈሮች ላይ በጦነርቱ የተለያዩ ጊዜያት ወቅት አዳዲስ ጥሰቶች እንደተፈጸሙባቸው አሳይተዋል።
ይህ በኢራን የአጸፋ ጥቃት ምክንያት በአሜሪካ ላይ የደረሰው ጉዳት በአጠቃላይ ለጦርነቱ ካወጣችው ገንዘብ ጋር ሲነጻጸር በጣም ትንሽ ነው።
የአሜሪካ መከላከያ ባለሥልጣናት ለአሜሪካ ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ላይ በጦርነቱ የመጀመሪያ ስድስት ቀናት ውስጥ 11.3 ቢሊዮን ዶላር የወጣ ሲሆን፣ በ12 ቀናት ውስጥ ደግሞ 16.5 ቢሊዮን ዶላር እንዳስወጣ የሲኤስአይኤስ መረጃ ያመለክታል።
የመከላከያ ሚኒስቴሩ ጦርነቱን ለማካሄድ የ200 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ በጀት እየጠየቀ ነው። ሚኒስትሩ ፔት ሄግሴት ሐሙስ እለት እንደተናገሩት የተጠየቀው ገንዘብ መጠን "ሊጨምር ይችላል" ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ እስራኤል የካቲት 21/2018 ዓ.ም. በጀመረችው ጥቃት ውስጥ ተሳታፊ ከሆነች በኋላ 13 የአሜሪካ ወታደሮች ተገድለዋል።
መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የኢራን የሰብአዊ መብት አክቲቪስቶች የዜና ማዕከል እንደሚለው ሦስተኛ ሳምንቱን ባጠናቀቀው ጦርነት እስካሁን ኢራን ውስጥ በአጠቃላይ 3,200 ሰዎች ተገድለዋል። ከእነዚህም ውስጥ 1,400 ያህሉ ሰላማዊ ሰዎች መሆናቸውን ዘግቧል።
ትራምፕ አገራቸው የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር ለማጥፋት፣ መደበኛ ወታደራዊ ኃይሏን ለማዳከም እና አገዛዙ በአካባቢው ላሉ ቡድኖች የሚሰጠውን ድጋፍ ለማቆም ያቀዱትን ግብ ለማሳካት መቃረቡን ተናግረዋል።
ነገር ግን የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ ከፍተኛ የነዳጅ ምርት የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ በዓለም ምጣኔ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጫና የፈጠረ ሲሆን፣ ጦርነቱ እስከ መቼ እንደሚቆይ አለመታወቁ እና ትራምፕ ወታደሮችን የሚያሰማሩ ከሆነ ቀውሱን ያባብሰዋል የሚል ስጋት ፈጥሯል።