ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ በሌላ አገር የተመረቱ የኢንተርኔት ራውተሮችን በደህንነት ስጋት ምክንያት አገደች
አሜሪካ በብሔራዊ ደህንነት ስጋት ምክንያት አዳዲስ በውጭ አገር የተመረቱ የኢንተርኔት ራውተሮችን አገደች።
የፌዴራል ኮሙኒኬሽን ኮሚሽን (ኤፍሲሲ) ሰኞ ዕለት ለአጠቃቀም ደህንነታቸው በበቂ ያልተረጋገጠ እንደሆነ በሚታሰቡ የመሣሪያዎች ዝርዝር ላይ ባወጣው ማሻሻያ ከአሜሪካ ውጭ የተመረቱ ራውተሮችን አግዷል።
ኮምፒውተሮችን፣ ስልኮችን፣ ቴሌቪዥኖችን እና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን ከኢንተርኔት ጋር ለማገናኘት በቤት እና በንግድ ተቋማት ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉትን ራውተሮችን አግዷል።
ኮሚሽኑ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ በውጭ አገራት የተመረቱ ድሮኖችን ማገዱ ይታወሳል።
"እኩይ ተግባር የሚፈጽሙ አካላት በውጭ አገር በተሰሩ ራውተሮች ላይ ያለውን የደህንነት ክፍተት በመጠቀም የአሜሪካ ቤተሰቦችን ለማጥቃት፣ ኢንተርኔቶችን ለማወክ፣ ለመሰለል እና የአእምሯዊ ንብረት ስርቆትን ለማመቻቸት ተጠቅመዋል" ሲል ኤፍሲሲ ተናግሯል።
ሰዎች በባለቤትነት ይዘዋቸው የሚገኙ በውጭ አገራት የተመረቱ ራውተሮች መጠቀም ቢችሉም፣ እገዳው በሁሉም "አዳዲስ በሚገቡ ሞዴሎች" ላይ ተፈጻሚ ይሆናል።
እገዳው የመጣው ባለፈው ዓመት ራውተሮች እኩይ ተግባር ለሚፈጽሙ አካላት በቀላሉ ተደራሽ መሆናቸውን በሚመለከት ያለው ስጋት እየጨመረ በመምጣቱ ነው።
ቲፒ-ሊንክ የተባለው በቻይና የተሰራ እና በአማዞን ላይ በብዛት የሚሸጥ ራውተር ባለፈው ዓመት በርካታ የሳይበር ጥቃቶች ከተከሰቱ በኋላ የአሜሪካ ፖለቲከኞች ራስ ምታት ሆኗል።
ከአሜሪካ ውጭ የተመረተ ማንኛውም አዲስ ራውተር ወደ አገር ከመግባቱ፣ ከመተዋወቁ ወይም ከመሸጡ በፊት በኤፍሲሲ መጽደቅ አለበት።
ይህንን ፈቃድ ለማግኘት በቅድሚያ ከአሜሪካ ውጭ የሚመረቱ ራውተሮችን የሚያመርቱ ኩባንያዎች ወይንም ባለሃብቶቹ እነማን አንደሆኑ ማሳወቅ እንደ ግዴታ ተቀምጧል።
የተወሰኑ ራውተሮች በመከላከያ ሚኒስቴር ወይም በአገር ውስጥ ደህንነት ቢሮ ተቀባይነት ካላቸው ከእገዳው ውስጥ ሊወጡ ይችላሉ ሲል ኤፍሲሲ አስታውቋል።
ኤፍሲሲ እርምጃውን የወሰደው አርብ ዕለት በብሔራዊ ደህንነት ላይ የሚሰሩ የመንግሥት ኤጀንሲዎች በውጭ አገራት የሚመረቱ የኢንተርኔት ራውተሮች "ተቀባይነት የሌላቸውን አደጋዎች" እንዳስከተሉ መናገራቸውን ተከትሎ ነው።
የአሜሪካ መንግሥት ራውተሮችን በመጠቀም የተፈጸሙ ጥቃቶች ላይ ባደረገው ምርመራ የቻይና መንግሥት ወይም በእሱ ስም የሚሠሩ አካላትን ተጠያቂ አድርጓል።
አብዛኛዎቹ የኢንተርኔት ራውተሮች ከአሜሪካ ውጭ ታይዋን ወይንም ቻይና ውስጥ ይገጣጠማሉ ወይም ይመረታሉ።
የኤፍሲሲ እገዳ ራውተሩ በአሜሪካ ውስጥ ዲዛይን ተደርጎ በውጭ አገር ከተመረተ ተፈጻሚ ይሆናል።