11 የአርሰናል ተጫዋቾች ለአገራቸው ብሔራዊ ቡድኖች የማይጫወቱት በጉዳት ወይስ ለጥንቃቄ?
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አስራ አንድ የአርሰናል ተጫዋቾች ራሳቸውን ከብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ውጪ አድርገዋል። ተጫዋቾቹ እውን ተጎድተው ነው? ወይስ ዘንድሮ ለቡድናቸው ስኬት ሲሉ ያደረጉት ጥንቃቄ የሚል ጥያቄ አስነስቷል።
ከ20ዎቹ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ቡድኖች 228 ተጫዋቾች ለብሔራዊ ቡድኖቻቸው ተመርጠዋል። ከእነዚህ መካከል 23 ተጫዋቾች በጉዳት ከብሔራዊ ቡድኖቻቸው ውጪ ሆነዋል። ግማሽ የሚያህሉት የአርሰናል ተጫዋቾች ናቸው።
በካራባኦ ዋንጫ በማንቸስተር ሲቲ ከደረሰባቸው ሽንፈት በኋላ ተከላካዩ ዊሊያም ሳሊባ በደረሰበት የቁርጭምጭሚት ጉዳት ከፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ውጪ መሆኑ ተረጋግጧል።
የኋላ መስመር አጋሩ ጋብርኤልም በጉልበት ጉዳት ምክንያት ከብራዚል ብሔራዊ ቡድን ውጪ ሆኗል።
የእንግሊዙ አጥቂ ኤቤሬቺ ኢዜ፣ የኖርዌይ አማካይ ማርቲን ኦዴጋርድ እና የኔዘርላንድሱ ተከላካይ ጁሪየን ቲምበር በጉዳት ምክንያት የዌምብሌዩ የዋንጫ ጨዋታ ያመለጣቸው ተጫዋቾች ናቸው። የቤልጂየሙ አጥቂ ሊያንድሮ ትሮሳርድ ጉዳት አስተናግዷል።
ተጫዋቾቹ ብሔራዊ ቡድኖቻቸውን ከተቀላቀሉ በኋላ ደግሞ አምስት የአርሰናል ተጫዋቾች ጉዳት ማስተናገዳቸው ተነግሯል። የእንግሊዞቹ ዴክላን ራይስ፣ ቡካዮ ሳካ እና ኖኒ ማዱዌኬ በተጨማሪም የስፔኑ ማርቲን ዙቢሜንዲ እና የኢኳዶሩ ፒዬሮ ሂንካፒ ናቸው።
ለመሆኑ አርሰናል የጉዳት ቀውስ እያስተናገደ ነው ወይስ ተጫዋቾቻቸውን ብቃት ለመጠበቅ የተወሰዱ የጥንቃቄ እርምጃዎች ናቸው?
ራይስ እና ሳካን ላለማመን 'ምንም ምክንያት የለም' - ቱኽል
ተጫዋቾቹ ከብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ውጪ መሆን ከ22 ዓመታት በኋላ ለማሳካት የሚጥሩለትን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ጨምሮ መድፈኞቹ በሦስት አቅጣጫ ከሚያደርጉት የዋንጫ ጉዞ ጋር ተገናኝቷል።
መድፈኞቹ በፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ በዘጠኝ ነጥብ በልጠው በሊጉ አናት ላይ ተቀምጠዋል። ሊጉ ሊጠናቀቅ ሰባት ጨዋታዎች ቢቀሩትም የፔፕ ጋርዲዮላ ቡድን ተጨማሪ አንድ ጨዋታ ይቀረዋል።
ተጫዋቾች ከብሔራዊ ቡድን ግዴታቸው ሲመለሱ መድፈኞቹ በኤፍኤ ካፕ ከሳውዝሃምፕተን ጋር ከሚያደርጉት ጨዋታ በኋላ በሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ወደ ፖርቱጋል በማቅናት ስፖርቲንግ ሊዝበንን ይገጥማሉ።
የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ቶማስ ቱኽል በርካታ የአርሰናል ተጫዋቾች ከጨዋታ ውጪ መሆናቸውን በተመለከተ ያለውን ጥርጣሬ "እንደሚረዱ" ተናግረዋል። ራይስ እና ሳካን በተመለከተ ግን እውነቱን እንዳልተናገሩ "ለማመን ምንም ምክንያት እንደሌላቸው" አጥብቀው ተናግረዋል።
ሁለቱም ተጫዋቾች ከጃፓን ጋር በሚደረገው የወዳጅነት ጨዋታ ላይ ለመሳተፍ "በከፍተኛ ፍላጎት" እንደነበራቸው ጀርመናዊው አሠልጣኝ ተናግረዋል። ነገር ግን ጉዳታቸው የመባባስ አደጋው "በጣም ትልቅ" እንደሆነ በብሔራዊ ቡድኑ የሕክምና ቡድን መገምገሙን ጠቅሰዋል።
ቱኽል አክለውም "ሁኔታውን ተረድቻለሁ። በቡካዮ እና በዴክላን ሐቀኝነት ላይ 100 በመቶ እምነት አለኝ። የሕክምና ምርመራን አድርገናል፤ አይቻቸዋለሁ።"
"ዴክላን ለልምምድ ወደ ሜዳ ወጥቶ ነበር። 'ጓዶች፣ ተጎድቻለሁ' ብሎ አልተናገረም።"
በዚህ የውድድር ዘመን በዓለም አቀፍ ጨዋታዎች ወቅት የማይክል አርቴታ ቡድን ተደጋጋሚ ጉዳት ደርሶበታል። አምበሉ ኦዴጋርድ፣ ጋብርኤል፣ ቲምበር እና የጣሊያኑ ሪካርዶ ካላፊዮሪ ጉዳት ያስተናገዱ ተጫዋቾች ናቸው።
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
'የወዳጅነት ጨዋታ ጊዜ ማባከን ነው'
እንደ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ የበላይ አካል ፊፋ ሕግ ከሆነ ተጫዋቾች ለብሔራዊ ቡድናቸው ከተጠሩ ሪፖርት ማድረግ አለባቸው።
ብሔራዊ ቡድኖች ጉዳት ያለባቸውን ተጫዋቾች የጉዳት መጠን ለማረጋገጥ በተጫዋቾች ላይ የራሳቸውን የሕክምና ምርመራ ለማድረግ መጠየቅ ይችላሉ። ቀላል ጉዳት ያለባቸውን ተጫዋቾች በተመለከተ ከብሔራዊ ቡድኖች ጋር ስምምነት ላይ መድረስ ይቻላል።
የአስቶን ቪላው አሠልጣኝ ኡናይ ኤምሬ ከሁለት ወራት ጉዳት በኋላ አገግሞ ለ23 ደቂቃዎች ብቻ የተጫወተው አማካዩ ዩሪ ቲሌማንስ ለብሔራዊ ቡድኑ ለመጫወት መወሰኑን በጸጋ ተቀብለዋል።
"ብሔራዊ ቡድኑ በጣም አስፈላጊ ነው። ለእኛ ጋር ያለው ቁርጠኝነት ትልቅ ጉዳይ ቢሆንም ግን ለብሔራዊ ቡድኑ የመሄድ ዕድል ልሰጠው ፈልጌ ነበር። ይኼ ለእሱ በጣም አስፈላጊ ነው" ብለዋል።
ሁሉም አሠልጣኞች ግን እንደዚያ አይሰማቸውም።
ታዋቂው የቀድሞ የማንቸስተር ዩናይትድ አሠልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በአንድ ወቅት ዓለም አቀፍ የወዳጅነት ጨዋታዎችን "ጊዜ ማባከን" ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
የቀድሞው አማካያቸው ኒኪ በት ቢያንስ አንድ ጊዜ ከእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ውጪ እንዲሆን በአሠልጣኙ እንደተከለከለ ተናግሯል።
"አንድ ጊዜም በውሸት ጉዳት እንዳለብኝ እንድናገር ነግሮኝ አያውቅም። 'የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን የወዳጅነት ጨዋታ አለህ ግን አትሄድም' ብቻ ይለኝ ነበር። ይኸው ነው።"
'አርቴታ በጥንቃቄው ደስተኛ ይሆናል'
የአሁኑ የብሔራዊ ቡድን የወዳጅነት ጨዋታዎች ራሳቸው ያገለሉ የአርሰናል ተጫዋቾች መብዛት ብዙ መላ ምቶችን ፈጥሯል ሲል የእግር ኳስ ተንታኙ አሌክስ ሃውል ጽፏል። ነገር ግን ሁሉም ተጫዋቾች የራሳቸው ምክንያት ብቻ ሳይሆን ምርመራ ያደርጋሉ ብሏል።
አንዳንዶቹ በጉዳዩ ዙሪያ ጥርጣሬ ሊኖራቸው ይችላል። ከስዊድን ጋር ከሚገኘው ከአጥቂው ቪክቶር ጂዮኬሬስ ውጪ ራሳቸውን ከብሔራዊ ቡድናቸው ያገለሉት ዘጠኝ ተጫዋቾች በዘንድሮው የውድድር ዓመት ለበርካታ ደቂቃዎች ቡድናቸውን ካገለገሉ 10 ተጫዋቾች መካከል ናቸው።
በቀደሙት ዓለም አቀፍ የወዳጅነት ጨዋታዎች ወቅት ቁልፍ ተጫዋቾችን በጉዳት ያጣው ሚኬል አርቴታ በዚህ ወሳኝ የውድድር ወቅት ከኮከቦቹ ባሳዩት ጥንቃቄ ደስተኛ ይሆናል ብሏል ሃውል።
እንዳያመልጥዎ
ከየፈርጁ
በስፋት የተነበቡ
የሚፈልጉት ይዘት የለም