ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያ የተለዩ የተሽከርካሪ የሠሌዳ ቁጥሮችን ለሚፈልጉ የጨረታ ጥሪ ቀረበ
በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች አዲስ የመለያ ሠሌዳ ቁጥር ለመስጠት የተዘጋጀው የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የተለዩ የሠሌዳ ቁጥሮችን በጨረታ ሊሰጥ ነው።
ሚኒስቴሩ በመላው አገሪቱ የተሽከርካሪዎች የሠሌዳ ቁጥርን ለውጥ ለማድረግ የሚያስፈልገውን ዝግጅት ማጠናቀቁን እና በቅርቡም አዲሱን የሠሌዳ መለያ ቁጥር (ታርጋ) መስጠት እንደሚጀምር እስታውቋል።
ባለፈው ዓመት በጸደቀው የአዲስ ታርጋ ለውጥ መመሪያ መሠረት በኢትዮጵያ የሚመዘገቡ ሁሉም ተሽከርካሪዎች በአሁኑ ወቅት ያላቸውን የተለያዩ ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮችን መለያ ፊደላትን በመተው በወጥነት 'ኢት' በሚል የሚተካ ይሆናል።
በተጨማሪም መመሪያው የተለያዩ አዲስ የተሽከርካሪ የመለያ ሠሌዳ ቁጥር አሠራሮችን ያካተተ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት "ልዩ መግለጫ ያለው የተለየ የመለያ ቁጥር ሠሌዳ" የሚፈልጉ ግለሰቦች በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት "እንደ ሁኔታው በልዩ ሁኔታ ሊሰጣቸው" እንደሚችል አመልክቷል።
ይህንንም መሠረት በማድረግ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የተሽከርካሪዎች የሠሌዳ ቁጥር ለውጥን ከመጀመሩ በፊት ግለሰቦች ወይም ተቋማት የሚፈልጓቸውን የሰሌዳ ቁጥሮች አጫርቶ ለአሸናፊዎች ለመስጠት ጥሪ አቅርቧል።
ሚኒስቴሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ ባወጣው ማስታወቂያ ላይ ፍላጎቱ ያላቸው ወገኖች በአንድ ሳምንት ውስጥ እንዲመዘገቡ ከማሳወቅ ውጪ ለጨረታው የሚያስፈልገውን ነገር በዝርዝር አልገለጸም።
ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር በኢትዮጵያ የተሽከርካሪዎች የመለያ ቁጥር ሰሌዳ ዓይነቶች እና ምልክቶች መወሰኛ እና የአገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ 1050/2017 ሰነድ ላይ በአገሪቱ ያሉ ተሽከርካሪዎች የመለያ ቁጥር ሠሌዳ እንደሚቀየር እና ሌሎችም ዝርዝር ጉዳዮች ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
በወቅቱ የተሽከርካሪዎች መለያ ቁጥር ሠሌዳን መለወጥ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሠረት እንዲያደርጉ እንዲሁም ሌሎች ችግሮችን ለመቆጣጠር እና ለማስወገድ መሆኑ ተገልጿል።
በዚህም መሠረት በመላው ኢትዮጵያ አገልግሎት ላይ የሚውሉት የሠሌዳ ቁጥሮች ተመሳሳይ መለያ እንዲኖራቸው እንደሚደረግ ተደንግጓል።
በዚህም ሁሉም የተሽከርካሪ መለያ ቁጥር ሠሌዳዎች በእንግሊዝኛ "ETH" እና በግዕዝ ፊደላት "ኢት" የሚሉ ኢትዮጵያን የሚያመለክት አጭር ጽሑፍ እና የአገሪቱ ካርታ ይኖራቸዋል ተብሏል።
በተጨማሪም የተሽከርካሪዎች የመለያ ቁጥር ሠሌዳዎች የቀለም ኅብር፣ ፊደላት በተጨማሪ የመለያ ቁጥር ሠሌዳዎቹ ሲመረት ለቁጥጥር እና ለምዝገባ ዓላማ የሚያገለግሉ መረጃዎችን የሚሰጡ ምሥጢራዊ ምልክቶች በሠሌዳዎቹ ላይ እንደሚኖር ተገልጿል።
አዲሱ የመለያ ቁጥር ሠሌዳዎቹ የተሽከርካሪዎችን ባለቤት፣ የሚሠጡትን አገልግሎት እና የኃይል አጠቃቀምን የሚያመለክቱ ቀለማት እንዲሁም ሌሎች መለያዎች እንደሚኖራቸው ባለፈው ዓመት የወጣው መመሪያው ላይ ተጠቅሷል።
በዚህም መሠረት በኤሌክትሪክ ወይም በታዳሽ ኃይሎች የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ሰሌዳ ከሌሎች በተለየ መልኩ "አረንጓዴ ትራንስፖርት (Green Transport)" የሚል የጽሁፍ መለያ እንደሚይዙ ተመልክቷል።
ከዚህም በተጨማሪም የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አሁን እንዳቀረበው ጥሪ "ልዩ መግለጫ ያለው የተለየ የመለያ ቁጥር ሠሌዳ" የሚፈልጉ ግለሰቦች በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት "በልዩ ሁኔታ ሊሰጣቸው" እንደሚችል ተገልጿል።
በሌሎች አገራት እንደሚሠራው ግለሰቦች እና ተቋማት ለተሽከርካሪዎቻቸው የሚሆኑ የሠሌዳ መለያዎችን በሚፈልጉት ዓይነት በተለየ ከፍያ ያገኛሉ።
በኢትዮጵያ አዲስ በሚጀመረው በዚህ አሠራር የተለየ የተሽከርካሪ መለያ ሠሌዳ ለሚፈልጉ ወገኖች አገለግሎቱ የሚሰጥበት ሁኔታ እና የክፍያ መጠንን በተመለከተ አስካሁን በይፋ የተገለጸ ነገር የለም።