ፌደራል ፖሊስ የፊንቴክ መስራችን እና "ጥቅም በመጋራት" የተጠረጠሩ ታዋቂ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ
የፎቶው ባለመብት, sm
የፊንቴክ ኢንቨስትመንት ድርጅትን "ባልተገባ" እና "በተጋነነ መልኩ" አስተዋውቀዋል እንዲሁም በሕገወጥ መንገድ ከተሰበሰበው ገንዘብ "ተጋሪ" በመሆን ተጠርጥረዋል የተባሉ ታዋቂ ግለሰቦች እና የማስታወቂያ ባለሙያዎች በቁጥጥር ስር አውሎ ፍርድ ቤት ማቅረቡን የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዛሬ በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ ከ1200 በላይ ዜጎችን አጭበርብረው የ1.7 ቢሊዮን ብር ጉዳት አድርሰዋል ያላቸውን የፊንቴክ ኢንቨስትመንት መስራች እና ባለቤቶች ላይ ምርመራ አጣርቶ አቃቤ ሕግ ክስ መመስረቱን ገልጿል።
የፊንቴክ ባለቤቶች እና መስራቾች በ19 ዓይነት የተለያዩ ወንጀሎች ምርመራ እንደተጣራባቸው እና ክስ እንደተመሰረተባቸው የፌደራል ፖሊስ መግለጫ ያስረዳል።
ፖሊስ እነዚህ ተጠርጣሪዎች ከ1200 በላይ ተጎጅዎችን አጭበርብረው በመመዝገብ "95 ሺህ ብር ቅድመ ክፍያ፤ 285 ሺህ ብር የመንግስት ታክስ እንዲሁም 130 ሺህ ብር ለኤክትሪክ መኪና ቻርጀር ለማሰራትና ለባለሙያ በሚል ከእያንዳንዳቸው 1 ሚሊየን 365 ሺህ ብር መቀበላቸውን" ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ጨምሮ በ19 የወንጀል ጉዳዮች በተጠረጠሩ ናቸው ያላቸው የፊንቴክ ኢንቨስትመንት ድርጅት መስራቾች እና ባለቤቶች ላይ ክስ መመስረቱን አስታውቋል።
ከዚህ በተጨማሪ ያላቸውን "ዕውቅና እና ተቀባይነት በመጠቀም ሆነ ብለው የተጋነነ ማስታወቂያ በመንገር" እንዲሁም በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያ "የሐሰት መረጃዎችን ለኅብረተሰቡ በማሰራጨት" ግሰለቦች እንዲጭበረበሩ አድርገዋል ያላቸውን ታዋቂ ሰዎችም በቁጥጥር ስር አውሏል።
ፖሊስ፤ በቁጥጥር ስር የሚገኙት ታዋቂ ግለሰቦቹ እና የማስታወቂያ ባለሙያዎቹ በሕገወጥ መንገድ ከተገኘው ገንዘብ "አሁን ባለው የገበያ ዋጋ ስምንት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቢ.ዋይ.ዲ ሶንግ ፕላስ የመኪና ስጦታ" መቀበላቸውን ገልጿል።
በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ እና በዜጎች ላይ ከ1.7 ቢሊየን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ ወንጀል ታዋቂ ግለሰቦቹ ላይ ምርመራ እያደረገ መሆኑንም አስታውቋል።
የፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር ካዋላቸው ታዋቂ ሰዎች መካከል አርቲስቶቹ ሰለሞን ቦጋለ፣ ሰራዊት ፍቅሬ፣ ዳንኤል ተገኝ እና ይገረም ደጀኔ ይገኙበታል። የማስታወቂያ ባለሙያ አብርሃም ግዛው፣ መንሱር ጀማል እና ካሊድ ናስርም በፌደራል ፖሊስ መግለጫው ላይ ተጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እነዚህን ታዋቂ አርቲስቶች እና የማስታወቂያ ባለሙያዎች በቁጥጥር ሥር አውሎ ፍርድ ቤት ማቅረቡን ገልጿል። እስከ መጋቢት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ በፍርድ ቤት እንደተፈቀደለት ገልጿል።
ፊንቴክ ኢንቨስትመንት የግል ድርጅት መስራች እና ባለቤቶች የሆኑት ዳንኤል ዮሃንስ ኢየሱስ እና ግርማይ ገ/ሚካኤል ይህደጎ ላይ መጀመርያ ክስ የተመሰረተው በአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ እንደነበር ተገልጿል።
የተፈጸመው ወንጀል "ውስብስብ" እንዲሁም "ድንበር ተሻጋሪ" መሆኑን የገለጸው የፌደራል ፖሊስ መግለጫ ጉዳዩን የፌደራል ፖሊስ ተረክቦ መመልከት መጀመሩን አስታውቋል።
የፊንቴክ መስራቾች ከሆኑት መካከል አቶ ዳንኤል ዮሃንስ የተባሉት ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል።
ተጠርጣሪ ግርማይ ገ/ሚካኤልን ደግሞ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ክትትል እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በመግለጫው ላይ አመልክቷል።
አቶ ግርማይ ገ/ሚካኤል ከዚህ ቀደም እአአ በ2010 የደቡብ አፍሪካ የዓለም የእግር ኳስ ሻምፒዮና ወቅት 'አስካሉካን' በተባለ ድርጅት ስም ወደ ደቡብ አፍሪካ ሄዳችሁ የዓለም ዋንጫ እንድትመለከቱ አደርጋለሁ በማለት ዜጎችን "በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ አጭበርብሮ ከአገር ወጥቷል" ተብሏል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ግለሰቡን በቁጥጥር ስር ለማዋል ከኢንተርፖል ጋር በመስራት ወደ አገር ማስመጣቱን እና በሕግ አግባብ ተጠያቂ እንዲሆን ማድረጉን ፌደራል ፖሊስ አብራርቷል።
የፎቶው ባለመብት, sm
የፊንቴክ ኢንቨስትመንት መስራቾች የኤሌክትሪክ መኪና መግዛት ከሚፈልጉ ግለሰቦች 50 በመቶ ቅድመ ክፍያ 950 ሺህ ብር በማስከፈል "በ90 ቀናት ውስጥ የመኪና ባለቤት እንደሚያደርጓቸው" መግለጻቸውን የፌደራል ፖሊስ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
ፊንቴክ የኤሌክትሪ መኪናውን ቀሪ ዋጋ 950 ሺህ ብር ደግሞ "ያለወለድ በ5 ዓመት ተከፍሎ የሚያልቅ የባንክ ብድር እንደሚያመቻች" በመግለጽ ዜጎችን አጭበርብረው ክፍያ እንዲፈጽሙ አድርገዋል ሲል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገልጿል።
በወቅቱ ተጠርጣሪዎቹ 148 መኪኖች ከጅቡቲ ማስገባታቸው እና 100 መኪኖች ለተወሰኑ ግለሰቦች ማከፋፈላቸው ተገልጿል።
ቀሪዎቹ 48 መኪኖችን ደግሞ " በድብቅ" መሸጣቸው በመግለጫው ላይ ተመልክቷል።
የድርጅቱ ባለቤቶች "ወደ አገር ውስጥ ስለመግባታቸው ምንም ዓይነት መረጃና ማስረጃ ሳይኖር 350 መኪኖችን ከውጭ እንዳስገቡ በማስመሰል ኅብረተሰቡን ሲያጭበረብሩ" እንደነበር ፖሊስ በምርመራ ማረጋገጡን ጠቅሷል፡፡
በተጨማሪም በጅቡቲ ወደብ ምንም ዓይነት መኪና ሳይኖር "400 መኪኖች ጅቡቲ ወደብ ላይ እንደቆሙና ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት በሂደት ላይ እንዳሉ በማስመሰል ለተጎጂዎች ሐሰተኛ መረጃ" መስጠታቸውን ፖሊስ ማረጋገጡን አስታውቋል።
በመስቀል አደባባይ ከተለያዩ ቦታዎች መኪኖችን በውሰት በማሰባሰብ ሕዝብን ማሳሳታቸውንም ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል።
የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ከሆነው ቢዋይዲ ከተባለ የቻይና ካምፓኒ ጋር ምንም ዓይነት ውል ሳይኖራቸው ውል እንዳላቸው አድርገው የማጭበርበር ወንጀል ፈጽመዋል ያለው ፖሊስ፤ ጅቡቲ "አልፋቲዞ" በሚል ስም ባቋቋሙት ድርጅት የ336 መኪኖች 90 በመቶ ቀሪ ክፍያ አለመፈጸማቸውንም አመልክቷል።
እንዳያመልጥዎ
ከየፈርጁ
በስፋት የተነበቡ
የሚፈልጉት ይዘት የለም