አንትሮፒክ የተሰኘ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኩባንያ ተጠቃሚዎቹን ለመቆጣጠር የጦር መሳሪያ ባለሙያ ሊቀጥር ነው

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

አንትሮፒክ የተሰኘው የአሜሪካው የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ኩባንያ፤ ሶፍትዌሩ "በአደገኛ ሁኔታ ጥቅም ላይ እንዳይውል" ለመከላከል የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች እና ፈንጂ ባለሙያ ሊቀጥር ነው።

ኩባንያው የቅጥር እንቅስቃሴውን የጀመረው፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎቱን በመጠቀም የኬሚካል ወይም የራዲዮአክቲቭ መሳሪያዎችን እንዴት መሥራት እንደሚቻል ለማወቅ የሚጥሩ ተጠቃሚዎች ሊኖሩ ይችላሉ በሚል እንደሆነ ታውቋል።

ኩባንያው 'ሊንክዲን' ላይ ባወጣው የሥራ ቅጥር ማስታወቂያ፤ አመልካቾች ቢያንስ የአምስት ዓመታት "የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች እና/ወይም ፈንጂዎች መከላከያ" እንዲሁም "የራዲዮሎጂካል መሳሪያዎች" ወይም ቦምቦች እውቀት ሊኖራቸው እንደሚገባ ገልጿል።

ድርጅቱ ለቢቢሲ እንደተናገረው ሥራው ቀደም ሲል ካወጣቸው ሌሎች ወሳኝ የሥራ መደቦች ጋር ተመሳሳይ ነው።

አንትሮፒክ ይህንን ስትራቴጂ የተከተለው ብቸኛው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኩባንያ አይደለም።

የቻትጂፒቲ ባለቤት የሆነው 'ኦፕንኤአይ'ም ተመሳሳይ የሥራ ቅጥር ይፋ አድርጓል። ኦፕንኤአይ "የባዮሎጂካል እና ኬሚካል ስጋት" ተመራማሪ ለመቅጠር ያቀረበው 455 ሺህ ዶላር የሚደርስ ደመወዝ አንትሮፒክ ሊከፍል ካቀደው በእጥፍ ገደማ ይበልጣል።

ዓላማው ተጠቃሚዎችን ለመቆጣጠር ቢሆንም አንዳንድ ባለሙያዎች ግን ይህ አካሄድ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ስለ ጦር መሳሪያዎቹ መረጃ እንዲያገኝ ድጋፍ ያደርጋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የቴክኖሎጂ ተመራማሪው ዶ/ር ስቴፋኒ ሃሬ፤ "ቦምቦችን እና ሌሎች የራዲዮሎጂ መሳሪያዎችን ጨምሮ ሚስጥራዊ ኬሚካሎችን እና የፈንጂ መረጃዎችን ለመቆጣጠር የሰው ሠራሽ አስተውሎት ስርዓቶችን መጠቀም ደኅንነቱ የተጠበቀ ነውን?" ሲሉ ጠይቀዋል።

"ለዚህ አይነት ሥራ እና ከእነዚህ አይነት መሳሪያዎች ጋር የተያያዘ የሰው ሠራሽ አስተውሎት አጠቃቀም ዓለም አቀፍ ስምምነት ወይም ሌላ ደንብ የለም። ይህ ሁሉ ከቁጥጥር ውጭ እየተካሄደ ነው" ብለዋል።

የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንዱስትሪው በቴክኖሎጂው ምክንያት ሊከሰቱ ስለሚችሉ የህልውና ስጋቶች በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም ቴክኖሎጂው የሚያድግበትን ፍጥነት ለማዘግየት ምንም አይነት ሙከራ አልተደረገም።

የአሜሪካ መንግስት የኢራን ጦርነት እና የቬንዙዌላ ወታደራዊ ዘመቻዎች ሲከፍት ለሰው ሠራሽ አስተውሎት ኩባንያዎችን ጥሪ ማቅረቡ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል።

የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር የአቅርቦት ሰንሰለት ስጋት ይፈጥራል በሚል አንትሮፒክን ማገዱን ተከትሉ ኩባንያው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶታል።

ኩባንያው፤ የኤአይ ስርዓቶቹ ያለ ሰው ክትትል ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን ችለው ለሚንቀሳቀሱ የጦር መሳሪያዎች ወይም በአሜሪካውያን ላይ ለሚደረግ የጅምላ ክትትል ጥቅም ላይ መዋል እንደሌለባቸው ደጋግሞ ገልጿል።

የአንትሮፒክ ተባባሪ መሥራች ዳሪዮ አሞዴይ፤ ቴክኖሎጂው እስካሁን አጥጋቢ ደረጃ ላይ ባመለድረሱ ለእነዚህ ዓላማዎች ጥቅም ላይ መዋል እንደሌለበት የካቲት ላይ ጽፈዋል።

ዋይት ሃውስ በበኩሉ የአሜሪካ ጦር በቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እንደማይመራ አስታውቋል።

የአሜሪካ መንግሥት አንትሮፒክ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ኩባንያው በብሔራዊ ደኅንነት ጉዳዮች ላይ በጥቁር መዝገብ ውስጥ ከተካተተው የቻይናው የቴሌኮም ኩባንያ ሁዋዌ ጋር ተመሳሳይ ምድብ ውስጥ አስገብቶታል።

ከአንትሮፒክ አቋም ጋር እንደሚስማማ የገለጸው ኦፕንኤአይ፤ በግሉ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር ድርድር እንደሚያደርግ አስታውቋል።