አሜሪካ እየጨመረ የመጣውን የደኅንነት ስጋት በመጥቀስ ዜጎቿ ከሊባኖስ እንዲወጡ አስጠነቀቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ መንግሥት በሊባኖስ የሚገኙ ዜጎቹ አገሪቱን በፍጥነት ለቅቀው እንዲወጡ አሳሰበ።

በቤይሩት የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በሊባኖስ ያለው የጸጥታ ሁኔታ "ተለዋዋጭ እና ሊተነበይ የማይችል" መሆኑን በመጥቀስ ዜጎች አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ አስጠንቅቋል።

በሊባኖስ በደቡብ በቃአ ሸለቆ እና በዋና ከተማዋ አንዳንድ ክፍሎች የአየር ድብደባዎች፣ የድሮን እና የሮኬት ጥቃቶች በተደጋጋሚ እየተሰሙ ነው።

በአካባቢው የሚገኙ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎችም ስጋት ላይ መውደቃቸውን ኤምባሲው አስጠንቅቋል። ኢራን እና ተባባሪ ሚሊሻዎቿ በሊባኖስ የሚገኙ ተቋማትን ዒላማ ሊያደርጉ እንደሚችሉም አክሏል።

የአሜሪካ መንግሥት በሊባኖስ ለሚገኙ ዜጎቹ ያወጣው ይህ ማስጠንቀቂያ የአሜሪካ የጦር አውሮፕላን በኢራን ውስጥ ተመትቶ ከወደቀ በኋላ የተሰጠ ነው።

የእስራኤል መከላከያ በቤይሩት አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሚፈጽመውን ድብደባ አጠናክሮ ቀጥሏል።

አርብ ዕለት በቤይሩት የሚገኘው ኤምባሲ አሜሪካውያን ወደ ሊባኖስ እንዳይጓዙ እና የንግድ በረራዎች ክፍት በሆኑበት በዚህ ወቅት አገሪቱን ለቅቀው መውጣት እንዳለባቸው መክሯል።

ለመቆየት የሚወስኑ ዜጎች የአደጋ ጊዜ ዕቅዶችን እንዲያዘጋጁ እና ሁኔታው ​​ከተባባሰ ደኅንነቱ በተጠበቀ ስፍራ ለመጠለል ዝግጁ እንዲሆኑ አስጠንቅቋል።

ኤምባሲው በደቡብ ሊባኖስ፣ በሶሪያ ድንበር አቅራቢያ፣ በስደተኞች መጠለያዎች እና በቤይሩት ደቡባዊ ዳርቻዎች፣ ዳሂህን የሚኖሩ አሜሪካውያን እነዚህን አካባቢዎች ወዲያውኑ ለቅቀው እንዲወጡ "በጥብቅ" አሳስቧል።

በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ የአሜሪካ መንግሥት ያደረገውን ግምገማ ተከትሎ ወሳኝ ያልሆኑ በቤይሩት የሚገኘው ኤምባሲ ሠራተኞች አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ አዟል።

በወቅቱ ወደ 50 የሚጠጉ የአሜሪካ ኤምባሲ ሠራተኞች እንዲወጡ ታዝዘው ነበር ተብሏል።

ሐሙስ ዕለት አንድ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ በባግዳድ በኢራን በሚደገፍ ታጣቂ ቡድን ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ በኢራቅ የሚገኙ አሜሪካውያን እንዲወጡ ተጠይቀዋል።

በኢራቅ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እንዳስታወቀው ከኢራን ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂ ቡድኖች በሚቀጥሉት 24 እና 48 ሰዓታት ውስጥ በማዕከላዊ ባግዳድ ጥቃት ሊፈጽሙ ይችላሉ።

አርብ ዕለት የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በቴህራን ላይ አዲስ የጥቃት ማዕበል መጀመሩን እና የቤይሩትን አንዳንድ ክፍሎች ዒላማ ማድረግ መጀመሩን አረጋግጧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሊባኖስ ውስጥ "በተባበሩት መንግሥታት ይዞታ ውስጥ" በደረሰ ፍንዳታ ሦስት የመንግሥታቱ የሰላም አስከባሪ ወታደሮች ቆስለዋል ሲል በሊባኖስ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ጊዜያዊ ኃይል (ዩኤንፊል) አርብ ዕለት አስታውቋል።

ከሰላም አስከባሪ ኃይሎች መካከል ሁለቱ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲል ኤጀንሲው አስታውቋል።

ቃል አቀባይ የሆኑት ካንዲስ አርዲኤል እንዳሉት ፍንዳታው የተከሰተው በደቡባዊ ሊባኖስ በሚገኘው ኤል አዴሴ አቅራቢያ ሲሆን የፍንዳታው መነሻ እስካሁን አልታወቀም።