የዋሊያዎቹ ለአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ተስፋ እና የአሠልጣኙ ዕጣ ፈንታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተከላካይ መስመር ተጫዋች ያረዴ ባየህ

አርብ መጋቢት 15/2015 በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ጊኒ ከኢትዮጵያ ምሽት 5 ሰዓት ሲጫወቱ ለማየት በርካታ ኢትዮጵያዊያን ቁጭ ብለው ጠበቁ።

ነገር ግን ውጤቱ ብዙዎችን ተስፋ ያስቆረጠ፤ አንገት ያስደፋ ነበር።

የዋሊያዎቹ የኋላ መስመር መፈረካከስ የተመቸው የጊኒ ካማኖ በ39ኛው ደቂቃ የመጀመሪያዋን ጎል አስቆጠረ።

ከእረፍት በኋላ አዲስ ነገር እናያለን ብሎ የጠበቀው ደጋፊ ተስፋ በ73ኛው ደቂቃ መነመነ፤ የጊኒው ባዮ ከሲላ የተሻገረችለትን ኳስ ከመረብ አገናኝቶ ጨዋታው 2 ለምንም እንዲጠናቀቅ ሆነ።

ሰኞ መጋቢት 18/2015 ምሽት 4 ሰዓት ኢትዮጵያ ከጊኒ የምድቡ አራተኛ ጨዋታ።

በዚህኛው ጨዋታ ዋሊያዎቹ ኳስን እንደልብ እያንሸራሸሩ መጫወት ቢጀምሩም ጊኒ በአምበሏ ናቢ ኬይታ አማካይነት በ4ኛው ደቂቃ የመጀመሪያውን ጎል አስቆጠረች።

በጨዋታው ምርጥ ብቃት ካሳዩ ሦስት ተጫዎች መካከል አንዱ የነበረው ከነዓን ማርክነህ ከቸርነት ጉግሳ ያገኛትን ኳስ ከመረብ በማገናኘት ዋሊያዎቹ በአስደናቂ የቡድን ጎል አቻ እንዲሆኑ አስቻለ።

ከስምንት ደቂቃ በኋላ ጊኒዎች በሞሪባ ካሩማ አማካይነት ሁለተኛ ጎል በመድገም የኢትዮጵያን የማለፍ ተስፋ አመነመኑ።

ጨዋታው በጊኒ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቀቀ። ኢትዮጵያም ከምድብ የማለፍ ተስፋዋም ደቀቀ።

ለመሆኑ ዋሊያዎቹ ውጤት እንዲህ የራቃቸው ለምንድን ነው? ጫና የበረታባቸው አሠልጣኝስ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል?

“ዕድላችን የጠበበ ነው”

ኢትዮጵያ ከ4 ጨዋታዎች ሦስቱን ተሸንፋ፤ አንድ ጨዋታ አሸንፋ በሦስት ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የካፍ ድረ-ገፅ ያሳያል።

በሚመጣው ሰኔ ኢትዮጵያ ከማሊ፤ ወርሃ መስከረም ላይ ደግሞ የመጨረሻ ጨዋታዋን ከግብፅ ታደርጋለች።

ምድቡን ግብፅ በ9 ነጥብ ስትመራ፤ ጊኒ በተመሳሳይ ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

“በእኔ እምነት ኢትዮጵያ የሚቀሯት የመርሃ ግብር ሟሟያ ጨዋታዎች ናቸው” ይላል ጉምቱው የስፖርት ጋዜጠኛ ሰዒድ ኪያር።

እንደ ሰዒድ አስተያየት ምንም እንኳ በሒሳብ ቀመር መሠረት ኢትዮጵያ ልታልፍ ብትችልም “እጅግ በጣም የጠበበ ዕድል ነው።”

“ኢትዮጵያ እንድታልፍ ግብፅ አሊያም ጊኒ ሁለቱንም ጨዋታዎች ተሸንፈው ዋሊያዎቹ ደግሞ ከግብፅ እና ከማላዊ ያላቸውን ግጥሚያ በድል መፈፀም አለባቸው።”

ሰዒድ፤ በእግር ኳስ የሚፈጠረው ስለማይታወቅ ኢትዮጵያ ዕድሏን መሞከሯ መልካም ነው ቢልም፣ የሚቀሯትን ጨዋታዎችን አሸንፋ ሌሎቹ ተሸንፈው ታልፋለች ብሎ ግን አያምንም።

ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን ለብሔራዊ ቡድኑ በመመልመል የሚታወቁት ፋርሃን ሞሐመድ ደግሞ “በውጤቱ ብበሳጭም አልተገረምኩም” ይላሉ።

ባለፈው የቻን ዋንጫ ጨዋታ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተመሳሳይ ስህተቶችን ሲፈጽም እንደተመለከቱ የሚጠቅሱት ፋርሃን በተለይ የተከላካይ መስመሩ ደካማ ነበር ይላሉ።

የሽንፈት ምክንያቶች. . .

ብሔራዊ ቡድኑ ስደተኛ መሆኑ፣ የተጫዋቾች ብቃት፣ የአጥቂዎች በጉዳት አለመሳተፍ፣ ተጫዋቾች ከታች አለማደጋቸው፣ የአሠልጣኙ ስልት...ለብሔራዊ ቡድኑ ውጤት ማጣት እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱ መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

ሰዒድ ኪያር ከሜዳ ውጭ መጫወት የሚለው ምክንያት በፍፁም ከማያሳምናቸው መካከል ነው።

“ሁለቱም በገለልተኛ ሜዳ ነው የተጫወቱት። ጊኒም ሆነ ኢትዮጵያ የሚመጥን ሜዳ የላቸውም” ይላል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ኩባንያን እንዲሁም ፌዴሬሽኑን ጠንቅቆ የሚያውቀው ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀን የውስጥ ምንጫችንም እንዲሁ ከሜዳ ውጭ የሚለው ጉዳይ “ብዙም ሚዛን አይደፋም” ባይ ነው።

“በሌሎች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያዎች በርካታ ቡድኖች ከሜዳቸው ውጭ ተጫውተው ነጥብ ይዘው ሲወጡ ተመልክተናል። ለምሳሌ ናሚቢያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኡጋንዳ ነጥብ ይዘው ወጥተዋል። እኛም ባለፈው ግብፅን ከሜዳችን ውጭ አሸንፈናል።”

ከሜዳችን ውጭ መጫወትን ለምደነዋል የሚለው ውስጥ አዋቂው፣ ለውጤት ቀውሱ ምክንያቱ ይህ አይደለም ይላል።

ሰዒድ፤ ለብሔራዊ ቡድኑ ሽንፈት ምክንያት ነው የሚለው “ብሔራዊ ቡድኑ የተገበረው የጨዋታ መንገድ ለጊኒ ቀላል መሆኑ ነው።”

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ለእግር ፌዴሬሽኑ ቅርብ የሆነው ምነጫችን ሆነ ተጫዋች መልማዩ ፋርሃን ተመሳሳይ ሐሳብ ነው የሚያንጸባርቁት።

ፋርሃን፤ “አሠልጣኙ ከዚህ በላይ ማድረግ የሚችሉት ነገር ይኖራል ብዬ አላስብም። መልቀቅ ያለባቸው ይመስለኛል” ሲሉ ጠንከር ያለ አስተያየት ይሰጣሉ።

“አሠልጣኙ ገና ተጫዋች ሲመልምሉ መከላከልን ዓላማ አድርገው፤ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት እንደሄዱ ከመለመሏቸው ተጫዋቾች መረዳት ይቻላል” የሚለው ምንጫችን ደግሞ በውጤቱ ብዙ እንዳልተደነቀ ይገልጻል።

ለፋርሃን የጊኒ ብሔራዊ ቡድን ከባድ የሚባል አይደለም። ባይሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚሠራቸው ስህተቶች፣ የቴክኒክ እና የታክቲክ ችግር እንዲሁም የአስተዳደር ጉዳይ ናቸው በሁለቱ ጨዋታ ውጤት እንዳይገኝ ምክንያት የሆኑት።

አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከሁለቱ ጨዋታዎች በፊት ከጊኒ ከተቻለ 6 ነጥብ ካልሆነ ደግሞ 4 ነጥብ ለማግኘት እንዳሰቡ ተናግረው ነበር።

“አሠልጣኙ ይህን ያሉት ከሜዳችን ውጭ እንደምንጫወት እያወቁ ነው፤ ስለዚህ ከሜዳ ውጭ የሚለው ምክንያት አይሆንም። ከጨዋታ በፊት ያልተነሳ ምክንያት ከጨዋታ በኋላ ምክንያት ሊሆን አይችልም” ይላል ሰዒድ።

ጋዜጠኛው፤ የኢትዮጵያ ሜዳ ጭቃ ነው፣ አሊያም ከታች ያደጉ ተጫዋቾች የሉም፣ የፌዴሬሽኑ አደረጃጀት...የሚሉ ችግሮች በተደጋጋሚ ቢሰማም እነዚህ ጉዳዮች አዲስ አይደሉም ይላል።

“ለምሳሌ በሚመጣው ሰኔ ከግብፅ ጋር ጨዋታ አለን። ሰኔ ላይ የጭቃ ሜዳው አይቀየርም፤ ሰኔ ላይ ከታች የሚደርስ ታዳጊ ተጫዋች አይኖርም፤ አሊያም የፌዴሬሽኑ አደረጃጀት አይቀየርም።”

እንደ ሰዒድ እምነት “አሁን ባለው የተጫዋቾች ስብስብና ብቃት፤ ተጋጣሚውን ተመልክቶ የሚመጥን ዝግጅት አድርጎ መግባት” እንደሚያስፈልግ ይመክራል።

የአሠልጣኙ ስልት

ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈቀደው ውስጥ አዋቂ እና ሰዒድ ኪያር ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ጥሩ ብቃት እንዳላቸው ይስማማሉ።

ሰዒድ “ይህንን ችሎታ ወደ አእምሮ ግንኙነት፤ ወደ 11 ተጫዋቾች ግንኙነት ከፍ አድርጎ እንደ ቡድን መጫወት የሚያስችል የጨዋታ መንገድ ኢትዮጵያ የላትም። ወይም ኢትዮጵያውያን አሠልጣኞች ያንን አልተገበሩም” የሚል እምነት አለው።

“የጨዋታ ሐሳብ፣ የጨዋታ መንገድ፣ የጨዋታ ፍልስፍና እንጂ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሌላ ምንም ዓይነት ችግር የለበትም።”

ምንጫችን፤ ዋሊያዎቹ በተለይ በመጀመሪያው ጨዋታ በመከላከልም ሆነ በማጥቃት ደካማ ሆነው መታየታቸው የአሠልጣኙ ስልት ውጤታማ እንዳልነበር ማሳያ ነው ይላል።

ቁጥሮች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከጊኒ አቻው አንፃር ኳስን በማንሸራሸር የተሻለ እንደሆነ ያሳያሉ። ይህ ግን ለምንጫችን የሚዋጥ አይደለም።

“በተሳካ ቅብብል የተሻልን ልንሆን እንችላለን፣ ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ ወደ ጎን እና ወደ ኋላ በራሳችን ክልል ነው የምንጫወተው።”

ፋርሃን፤ ኢትዮጵያ ልክ እንደሌሎች የአፍሪካ አገራት ውጭ አገር ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን መጥራት ካለቻለች ለውጥ ይመጣል ብሎ አያስብም።

እንደ ምሳሌ ሞሮኮን በማንሳት ከ90 በመቶ በላይ ተጫዋቾቿ በአውሮፓ የሚጫወቱ እንደሆኑ እና ውጭ አገር የሚጫወቱ ተጫዋቾች የተለየ አስተሳሰብ [ሜንታሊቲ] እንዳላቸው ይናገራሉ።

መልማዩ በተከታታይ ለተሾመ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን ለማምጣት ቢጥሩም ተቀባይ እንዳላገኙ ይናገራሉ።

“የአሁኑ አሠልጣኝ ብቻ ሳይሆኑ ከዚህ በፊት ያሉትም የውጭ ተጫዋቾች ይምጡ ሲባል አይወዱም። ለምን እንደሆነ አላውቅም። ነገር ግን ማሪያኖ ባሪቶ በነበሩ ጊዜ ሦስት ተጫዋቾች መጥተው ነበር።”

ውስጥ አዋቂው በበኩሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከውጭ ማምጣት የሚባለው ሐሳብን ማንሳት “ትርፉ ጉንጭ ማልፋት ነው” ይላል።

“የፌዴሬሽን ሰዎች የኢትዮጵያ ሕግ ሁለት ፓስፖርት መያዝ ስለማይፈቅድ ሕጉ እንዲቀየር እንጎተጉታለን ሲሉ ብዙ ጊዜ ሰምተናል ግን በተግባር አላየንም።”

የአሠልጣኙ ዕጣ ፈንታ

ምንጫችን እንደሚለው በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው ብሔራዊ ቡድን ዋነኛው ችግሩ “የታክቲክ እና የቴክኒክ ውሳኔ” ነው።

ዋሊያዎቹ በጨዋታ ሲበለጡ አሠልጣኙ በሚያደርጉት የተጫዋች ቅያሪም ላይ ጥያቄ አለው።

“ጨዋታ ማንበብ፣ ጨዋታን መረዳት፣ ለተጋጠሚ የሚመጥን 11 መምረጥ፣ ለብሔራዊ ቡድን የሚሆኑ ተጫዋቾችን መምረጥ ላይ ትልቅ ክፈተት ያለ ይመስለኛል።”

አሠልጣኝ ውበቱ አባተ አዲስ የሁለት ዓመት ውል የፈረሙት ባለፈው መስከረም ነበር።

ውስጥ አዋቂው እንደሚሉት አሠልጣኝ ውበቱ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መልካም ግንኙነት ነው ያላቸው።

አሠልጣኙ ውላቸውን ባራዘሙበት ወቅት ትልቁ ዕቅዳቸው ኢትዮጵያን በኮት ዲቯር ለሚዘጋጀው የ2024 የአፍሪካ ዋንጫ ማሳለፍ እንደሆነ ገልጸው ነበር።

ነገር ግን አሁን ባለው ቀመር መሠረት ኢትዮጵያ የማለፍ ዕድሏ የመነመነ ነው። አሠልጣኙ ይቆያሉ ወይስ አይቆዩም የሚለው መነጋገሪያ ሆኗል።

ፋርሃን፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በጀቱ እንዳለው እርግጠኛ ባይሆኑም የውጭ አገር አሠልጣኝ መምጣት አለበት ብለው ከሚያምኑ መካከል ናቸው።

“ቢያንስ ለሁለት ዓመት ቆይቶ ሁኔታዎችን መቀየር የሚችል አሠልጣኝ መምጣት አለበት። የአገር ውስጥ አሠልጣኞች በተከታታይ ሞክረውት አልተሳካላቸውም። ከዚህ በኋላ ለውጥ ያመጣሉ ብዬ አላሰስብም።”

ምንጫችን እንደሚለው የአሠልጣኝ ውበቱ ዕጣ ፈንታ ምናልባት ከመጨረሻው የምድብ ጨዋታ [ኢትዮጵያ ከማላዊ] በኋላ የሚወሰን ይሆናል።

ለመጨረሻ ጊዜ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ያሠለጠኑት የውጭ አገር አሠልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ እንደሆኑ የሚያስታውሰው ውስጥ አዋቂው፣ ፌዴሬሽኑ ካለበት የገንዘብ እጥረት አንፃር የውጭ አገር አሠልጣኝ የማምጣት ዕድሉ ጠባብ ነው ይላሉ።

“ከዚያ በኋላ ከመጡት አሠልጣኞች ገብረመድኅን ኃይሌ ብቻ ነው ለጥቂት ጊዜ የተሳካ ቆይታ አድርጎ የተሰናበተው። ምናልባት ውበቱ ከሥራው የሚነሳ ከሆነ ከገብረመድኅን ውጭ ጥሩ ብቃት ያለው፤ በፕሪሚዬር ሊጉም የተሰካለት አሠልጣኝ አለ ብዬ አላስብም።”

አክለውም ፌዴሬሽኑ ሁለት አማራጭ ነው ያለው ይላል “ለገብረመድኅን ጊዜ መስጠት፤ አሊያም እንደምንም የውጭ አሠልጣኝ መቅጠር።”