ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በቻይና እና በግዙፍ ፍላጎቶች ላይ ስጋት የደቀነው የኢራን ጦርነት
በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት የፈጠረው ቀውስ ቻይና ደጅ አልደረሰም፤ ቢያንስ እስካሁን። የቀውሱ ስሜት ግን እየጨመረ እንጂ ባለበት የሚገታ አይደለም።
ለአጭር ጊዜ ሲታይ፤ ቻይና ለበርካታ ወራት የሚበቃ ነዳጅ አላት፤ ከቸገረም ደግሞ ወደ ጎረቤቷ ሩሲያ ልታማትር ትችላለች።
ቻይና ግን የዚህን ቀውስ ተጽዕኖ የምታሰለው በረጅም ጊዜ ውስጥ ከሚፈጥረው ሁኔታ አንጻር ነው። ይህ ስሌት መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ያሏትን ኢንቨስትመንቶች ብቻ የሚመለከት አይደለም፤ የወጠነቻቸውን ግዙፍ ትልሞች ጭምር እንጂ።
በዚህ ሳምንት በሺህዎች የሚቆጠሩ የኮሚዩኒስት ፓርቲ ተወካዮች በዓለም ሁለተኛዋ ግዙፍ ኢኮኖሚ ስለሆነችው አገራቸው ፍኖተ ካርታ ለመወያየት ስብሰባ ይቀመጣሉ። ይህ ስብሰባ የሚካሄደው አገሪቱ በአነስተኛ የምርት ፍላጎት፣ በተራዘመ የንብረት ዋጋ ቀውስ እና ግዙፍ የአገር ውስጥ ዕዳ እየተፈተነች ባለበት በዚህ ጊዜ ነው።
በቴክኖሎጂ እና ታዳሽ ኢንዱስትሪዎች ዘርፍ ፈጣን እድገት እየተመዘገበ ቢሆንም፤ የቻይና መንግሥት ከአውሮፓውያኑ 1991 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢኮኖሚ እድገት ትንበያውን ዝቅ አድርጎ አስቀምጧል።
ምናልባት ቻይና የገባችበትን የኢኮኖሚ ችግር ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ እንደምትወጣው ተስፋ ልታደርግ ትችላለች።
ነገር ግን ያለፈውን ዓመት ያሳለፈችው ከአሜሪካ ጋር የንግድ ጦርነት ውስጥ ገብታ ነው። አሁን ደግሞ ዋነኛ የመርከብ መጓጓዣ እና የኃይል አቅርቦት መስመሯ የሆነው መካከለኛው ምሥራቅ የገባበት ውጥንቅት የሚፈጥረው መዘዝ ተጋርጦባታል።
ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር የሚፈጠረው ህመም መጠንከሩ አይቀሬ ነው። በሆርሙዝ ሰርጥ የሚተላለፈው ትራፊክ መዘጋቱ ደግሞ ነገሩን ያባብሰዋል።
በሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት ፊሊፕ ሸትለር-ጆንስ፤ "በመካከለኛው ምሥራቅ የሚፈጠር የተራዘመ ቀውስ እና የደኅንነት እጦት ለቻይና ወሳኝ የሆኑ ሌሎች ቀጣናዎችን ይረብሻል" ይላሉ።
"ለምሳሌ የአፍሪካ ኢኮኖሚዎች ከባሕረ ሰላጤው አገራት የሚመጣው ከፍተኛ እና የተረጋጋ ካፒታል ተጠቃሚ ሆነው ቆይተዋል። ይመጣ የነበረው ኢንቨስትመን የሚሄድ ከሆነ፤ የቻይናን መጠነ ሰፊ እና የረጅም ጊዜ ፍላጎት ላይ ስጋት የሚደቅን ሰፊ የአለመረጋጋት አደጋ ያመጣል" ሲሉ ያብራራሉ።
ይህ ከተፈጠረ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሻራዋን ያሳረፈችው ቻይና ከመካለኛው ምሥራቅ ባሻገር ያሏት ኢንቨስትመንቶች እና ገበያዎች በተራዘመ ጦርነት ምክንያት ተጋላጭነታቸው ይጨምራል። ልክ እንደሌሎች አገራት ሁሉ ቻይና ይህ ያልተጠበቀ ክስተት የሚፈጥረውን ሁኔታ በጥንቃቄ መመልከቷ አይቀሬ ነው።
በለንደን ኪንግስ ኮሌጅ ፕሮፌሰር የሆኑት ኬሪ ብራውን "ቻይና እንደ ሁሉም አገራት እያሰበች ይመስለኛል" ይላሉ። "የጨዋታው ዕቅድ ምንድነው? በእርግጠኝነት አሜሪካዎቹ ያለ ዕቅድ ወደዚህ አልገቡም" ሲሉም ይጠይቃሉ።
አክለውም ግን "ምናልባት እንደሌሎቹ ሁሉ 'የእውነትም ያለ አንዳችም ዕቅድ ነው የገቡበት። ወደ ሌሎች ጉዳዮች ተጎትተን መግባት እንደማንፈልገው ሁሉ ወደዚህም ተስበን መግባት አልፈልግም። ነገር ግን የሆነ ነገር ማድረግ አለብን' ብለውም ሊያስቡ ይችላሉ" ብለዋል።
እምብዛም ያልጠነከረው ወዳጅነት
በበርካታ ምዕራባውያን ዘንድ ሁልጊዜም ኢራን የቻይና "አጋር" ተደርጋ ትፈረጃለች።
በእርግጥም እጅግ ተወዳጅተው ቆይተዋል። የኢራን ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኑ በአውሮፓውያኑ 1989 ለመጨረሻ ጊዜ ባደረጉት የውጭ ጉዞ የጎበኙት ቤይጂንግን ነበር።
በመካከላቸው ያለው አጋርነት ይበልጥ የጠበቀው በ2016 የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ቴህራንን ሲጎበኙ ነው። ሁለቱ አገራት በ2021 ደግሞ ለ25 ዓመታት የሚዘልቅ የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነት ተፈራርመዋል።
ቻይና በእነዚህ 25 ዓመታት ውስጥ ኢራን ውስጥ 400 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ለማድረግ ቃል ገብታለች። ኢራን ደግሞ በምላሹ ነዳጇን ወደ ቻይና ትልካለች።
ተንታኞች እንደሚገምቱት ግን ቃል ከተገባው ገንዘብ ውስጥ ለኢራን የደረሰው ሽርፍራፊው ነው። ነዳጁ ግን መጓጓዙን ቀጥሏል።
የ'ሴንተር ኦን ግሎባል ኢነርጂ ፖሊሲ' መረጃ እንደሚያሳየው፤ ቻይና 2025 ውስጥ በየቀኑ 1.38 ሚሊዮን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ከኢራን አስገብታለች። ቻይና ካስገባችው ጠቅላላ ድፍድፍ ነዳጅ ውስጥ 12 በመቶው እንደማለት ነው። የአብዛኛውን ነዳጅ መነሻ ለመደበቅ ሲባል በማሌዢያ ስም እንደተጓጓዙ ይነገራል።
የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ማዕከል ባውጣው ሪፖርት፤ እስያ ውስጥ ባሕር ላይ ባሉ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች የተጠራቀመ 46 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ እንዳለ ገልጿል።
የኢራን ብሔራዊ የነዳጅ ኩባንያ ታንከሮችን በሚከራይባቸው የቻይናዎቹ ዳሊያን እና ዦሻን ወደቦች ውስጥ የጉምሩክ ይለፍ ያላገኘው ክምች ደግሞ ከዚህም እንደሚበልጥ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
በሁለቱ አገራት መካከል የጦር መሣሪያ ሽያጭ ስምምነት እንዳለም ይነገራል። ቻይና፤ ፀረ መርከብ ክሩዝ ሚሳዔሎችን ለኢራን ሽጣለች መባሉን አስተባብላለች።
የአሜሪካ የስለላ ተቋም ግን ቻይና ኢንጂነሮችን በማሠልጠን እና የመሣሪያ አካላትን በማቅረብ የኢራንን የባለስቲክ ሚሳዔል ፕሮግራም እያገዘች ነው ሲል ይከስሳል።
የኢራን መንግሥት በሚቃውሙት እና በሚተቹት ላይ የሚወሰደቸው አስከፊ አፈና የሚከናወነው ቤይጂንግ ለቴህራን ባጋራችው የፊት መለያ እና የክትትል ቴክኖሎጂ እንደሆነ የመብት ተሟጋች ቡድኖች ይናገራሉ።
እነዚህ ጉዳዮች የሁለቱ አገራት ወዳጅነት ጥብቅ እንደሆነ ያስመስላሉ።
ክስተቶቹ አንዳንድ ጊዜ ጋዜጦች ቻይና እና ኢራንን ከሰሜን ኮሪያ እና ሩሲያ ጋር በማድረግ "የቀውስ ተጣማጆች" የሚል ስያሜ እንዲሰጧቸው አድርጓል።
አራቱም አገራት የሚፈልጉት አሜሪካ መር የሆነውን የዓለም ሥርዓት መገዳደር ነው፤ እንደ እውነቱ ግን ግንኙነታቸው ሰጥቶ መቀበል ላይ የተመሠረተ ነው።
ፕሮፌሰር ብራውን "ቻይና ከኢራን ጋር እንድትጣመር የሚያደርጋት አንድም እውነተኛ ርዕዮተ ዓለማዊ ወይም ባህላዊ ምክንያት የለም" ይላሉ።
"አንዳንድ ጊዜ ኢራን ለአሜሪካ የማታቋርጥ ራስ ምታት መሆኗ 'ከፋፍለህ ግዛ' ተብሎ ሊገለጽ የሚችለውን የቻይና ስትራቴጂን አሳክቷል። ስለዚህ ቻይና ከኢራን ጋር ግንኙነት እንዲኖራት የምትፈልግበት ምክንያት ከአዎንታዊ ይልቅ አሉታዊነቱ ያመዝናል" በማለት ያስረዳሉ።
አክለውም፤ "ይሄ ግንኙነትን ለመመሥረት እጅግ ደካማ የሆነ እሳቤ ነው፤ በተወሰነ መልኩ ሠርቷል። እርግ የጠለቀ ግንኙነት ግን አልነበረም" ብለዋል።
ቻይና "አጋርነቶቿን" የምትመለከተው ከምዕራቡ ዓለም ጋር ተመሳሳይ በሆነ መነጽር አይደለም። የሁለትዮሽ የመከላከያ ስምምነቶችን አትፈራረምም፤ ለአጋሯ ድጋፍ ለመስጠትም ቀድማ አትገኝም።
ይልቁንም ቻይና ከየትኛውም ግጭት ራሷን ማራቅን ትመርጣለች።
መሪነቱን መቆጣጠር
ይህ ማለት ግን ቻይና መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ በተፈጠረው ነገር በእጅጉ አትረበሽም ማለት አይደለም። ቤይጂንግ ተጠባቂ እና ጎልህ ያልሆነ ውግዘት አሰምታለች፤ የተኩስ አቁም እንዲደረግም ጥሪ አቅርባለች።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪን፤ "አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት መክፈታቸው... ይባስ ብሎም የሉዓላዊ አገር መሪን በግልጽ መግደል እና የመንግሥት ለውጥን መቀስቀስ ተቀባይነት የለውም" ብለዋል።
እውነታው ግን፤ አሜሪካ በታኅሣሥ መጨረሻ በቬንዙዌላ የወሰደችው እርምጃ፤ አሁን ደግሞ በኢራን ላይ የከፈተችው ጥቃት እነዚህ አገራት ከቻይና ጋር ያላቸው አጋርነት የተገደበ እንደሆነ አሳይቷል።
በሁለቱም ሁኔታዎች ገለል የተደረገችው ቤይጂንግ ከታዛቢነት በዘለለ ማገዝ የምትችል አልነበረችም።
ቻይና ከአሜሪካ አንጻር ያለች "ኃላፊነት የሚሰማት አማራጭ ኃይል" አድርጋ ራሷን ለማቅረብ እየሞከረች እንደሆነ በሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት ፊሊፕ ሸትለር-ጆንስ ይገልጻሉ።
ነገር ግን "ከወታደራዊ ሚዛን አንጻር አሜሪካ፤ ልዕለ ኃያል መሆን በትክክል ምን እንደሆነ እያሳየች ነው" ይላሉ። ተመራማሪው ቻይና ኢኮኖሚዋ ግዙፍ ቢሆንም "እኩል ደረጃ ያላት ልዕለ ኃያል" አይደለም በማለት ይከራከራሉ።
"ብትፍልግም እንኳ ወዳጆቿን ከእንደዚህ ዓይነቱ እርምጃ ለመታደግ የሚያስችል አቅም አልታጠቀችም" ሲሉ ያስረዳሉ።
ይህን ስጋት ለመጻረር የሚፈልጉት የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ፤ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ሲነጻጸሩ የተረጋጉ እና ተገማች የሆኑ የዓለም መሪ አድርገው ራሳቸውን ማቅረባቸውን ቀጥለዋል።
በቻይና ኢንስቲትዩት የእስያ እና አፍሪካ ጥናት ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ስቲቭ ሳንግ፤ ቻይና የፕሬዝዳንት ትራምፕን እርምጃ "ስለ ነጻ ዓለም አቀፍ ሥርዓት የሚያወራው" የምዕራቡ ዓለም "ያለበትን ግብዝነት" እንደሚያሳይ በመጥቀስ መከራከሪያ እንደምታቀርብ ይናገራሉ።
በጦርነቱ ምክንያት የተፈጠረው የኢነርጂ አቅርቦት እና የጉዞ መስተጓጎል "ከምዕራቡ ዓለም ይልቅ በደቡቡ የዓለም ክፍል ላይ እጅግ የከፋ ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ" እንደሚያሳድር ይገልጻሉ።
በደቡቡ የዓለም ክፍል ያሉ "የተወሰኑ አገራት በጥቂት ወራት ውስጥ የምግብ እጥረት ያጋጥማቸዋል። ዩናይትድ ኪንግደም እና ስፔን ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ተነጥለው መታየታቸውን ተከትሎ አሁንም ቢሆን የምዕራባውያን ጥምረት ያጋጠመውን ክፍተት እየተመለከትን ነው" ብለዋል።
ቻይና ከሌሎች አገራት ጋር ንግግሮች እንዲጀመሩ ማድረግ የምትችልበት ዕድል እንዳለ ልታይ ትችላለች። የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ከኦማን እና ከፈረንሳይ አቻዎቻቸው ጋር ተነጋግረዋል። በተጨማሪም ቻይና ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ልዩ ልዑክ እንደምትልክ አስታውቃለች።
እየተቃረበ ያለው የትራምፕ ጉብኝት
አሁንም ቢሆን ቻይና በጥንቃቄ እየተጓዘች ነው። ምክንያቱም አንዱ ትልቅ ስሌት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በዚህ ወር መጨረሻ ያደርጉታል ተብሎ በጉጉት እየተጠበቀ ያለው የቻይና ጉብኝት ነው።
ቻይን የአሜሪካን እና እስራኤልን ጥቃት በተመለከተ ካሰማቻቸው ወቀሳዎች አንዱም ፕሬዝዳንት ትራምፕን ቀጥታ የሚተች አይደለም። ይህ እርምጃዋ የሁለቱ አገራት መሪዎች እጅ የመጨባበጣቸውን ነገር አይቀሬነት ያጠናክራል።
አንዳንዶች የፕሬዝዳንቱ ጉዞ የመካሄዱ ነገር ላይ ጥርጣሬያቸውን አሰምተዋል። እስካሁን ያሉት ምልክቶች የሚያሳዩት ግን የቤይጂንጉ ጉዞ እንዳልቀረ ነው። የሁለቱ አገራት ባለሥልጣናት ስለ ጉዞው ሊወያዩ እንደሆነ ሮይተርስ ዘግቧል።
ቻይና ይህንን አጋጣሚ ትራምፕ እንደ ታይዋን ባሉ ሌሎች የውጥረት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ምን ዓይነት ምላሽ ሊሰጡ እንደሚችሉ ለመረዳት የሚያስችላትን "ፍንጭ ለመፈለግ" ልትጠቀምበት እንደምትችል ተመራማሪው ፊሊፕ ሸትለር-ጆንስ ይናገራሉ።
"ይህ ጦርነት ተቀባይነት የሌለው እየሆነ በመጣ ቁጥር፤ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ እን የደኅንነት ፖሊሲ ውስጥ እየተዘወተረ የመጣውን 'የመታቀብ' አዝማሚያ እንዲጠናከር አስተዋጾ ሊያደርግ ይችላል።
[ይህ ዓይነቱ ፖሊሲ] ወደፊት በሚመጣው አስተዳደር የሚተገበር ከሆነ ቻይና በቀጣናዋ እና በሰፊው ዓለም ፍላጎቷን ለማሳካት የተሻለ ነጻነት እንዲኖራት ያደርጋታል" በማለት ያብራራሉ።
በመካከለኛው ምሥራቅ የተፈጠረው ቀውስ ቻይና አሜሪካን ጦር ሰባቂ አድርጋ እንድትስል የተወሰነ ዕድል ይሰጣታል።
ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት "የማይገመት እና በአግባቡ የማይሠራ ተዋናይ" መኖሩ ለቤይጂንግ የጭንቀት ምንጭ ሊሆንባት እንደሚችል ፕሮፌሰር ብራውን ይናገራሉ።
"ቻይን የአሜሪካ የበላይነት የተረጋገጠበት ዓለምን የምትፈልግ አይመስለኝም፤ ነገር ግን አሜሪካ እንዲህ ያልተረጋጋች ተዋናይ የሆነችበት ዓለምንም አትፈልግም" ሲሉ ምልከታቸውን አጋርተዋል።