ጠፈርተኞችን ከ50 ዓመታት በኋላ ወደ ጨረቃ የሚወስደው 'አርቴሚስ 2' መንኮራኩር ወደ ሕዋ መጠቀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የአርቴሚስ 2 መንኮራኩር ወደ ሕዋ መጠቀ።

ከፍሎሪዳ የተነሳው መንኮራኩር ለቀጣይ 24 ሰዓታት በምሕዋር ዙሪያ ሲሽከረከር ቆይቶ ወደ ጨረቃ የሚጓዝ ይሆናል።

የአርቴሚስ 2 ተልዕኮ (Artemis II mission) የሰው ልጆችን ከአፖሎ 17 (Apollo 17) ወዲህ ወደ ጨርቃ መልሶ በመውሰድ ታሪካዊ ጉዞ ተብሏል።

አራት የናሳ ጠፈርተኞችን የያዘው መንኮራኩር ከፍሎሪዳ ሲነሳ አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ አገራት በርካታ ሰዎች ተከታትለውታል።

መንኮራኩሩ ከመነሳቱ አስቀድሞ የተወሰኑ የቴክኒክ ችግሮች ቢገጥሙትም በስተመጨረሻ ከመሬት መነሳት ችሏል።

ጠፈርተኞቹ "ደኅና ናቸው። ጥሩ መንፈስ ላይም ይገኛሉ" ሲል ናሳ አስታውቋል።

በ10 ቀናት ቆይታቸው ጨረቃ ላይ ባያርፉም ጨረቃን ይዞራሉ። ከዚህ ቀደም የትኛውም የሰው ልጅ ከምድር ርቆ ከሄደበት ርቀት በላይ ይጓዛሉ።

ከ50 ዓመታት በፊት በአፖሎ 17 ጠፈርተኞች ወደ ጨረቃ ሲጓዙ ከነበረው አንጻር አርቴሚስ 2 የተለየ መሆኑን ባለሙያዎች ተናግረዋል።

መንኮራኩሩ የላቀ ቴክኖሎጂ ቢኖረውም ጠፈርተኞቹ የሚያከናውኑት ሥራ ከዓመታት በፊት ከነበረው ጋር ተቀራራቢ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, አራት የናሳ ጠፈርተኞችን የያዘው መንኮራኩር ከፍሎሪዳ ሲነሳ አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ አገራት በርካታ ሰዎች ሲከታተሉ ነበር

በአርቲሚስ 2 የመንኮራኩሩ መጸዳጃ ቤት አገልግሎት ለመስጠት አስቸግሮ ቢቆይም ማስተካል እንደተቻለ ናሳ አስታውቋል።

የአርቴሚስ ተልዕኮ የረዥም ጊዜ ዕቅድ ጠፈርተኞች ጨረቃን ከተሽከረከሩ በኋላ እዚያው አርፈው እንዲቆዩ ማድረግ ነው።

ጨረቃ ላይ የጠፈር ተመራማሪዎች ለወራት እንዲቆዩ ማስቻል ከዚህ ቀደም አልተሞከረም ነበር።

አቧራማ እና አየር አልባ በሆነችው ጨረቃ ላይ ለመቆየት ከቴክኒክ ብቃት ባሻገር ትዕግስት እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የአርቴሚስ ተልዕኮ አካል የሆነው የአውሮፓ የሕዋ ምርምር ባለሙያ የሆኑት ሰርጊ ቫኩር አሩጆ "ሁሉንም መስፈርት የሚያሟሉ ጠፈርተኞች ማግኘት ቀላል አይደለም። ልዕለ ኃያል ሰዎች የመፈለግ ያህል ነው" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, NASA/PA Wire

የምስሉ መግለጫ, ጉዞው በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የአርቴሚስ 2 መንኮራኩር አራት ጠፈርተኞች
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "አራቱ ጀግና ጠፈርተኞቻችንን እግዚአብሔር ይባርካቸው። ተልዕኮው አስገራሚ ነው" ብለዋል።

ጠፈርተኞቹ በቀጣይ 24 ሰዓታት ውስጥ መሬትን ሁለት ጊዜ ይዞራሉ። መንኮራኩሩ ውስጥ ሳሉ የጨረቃ ግርዶሽ መመልከት ይችላሉ።

በሕዋ አሰሳ በዋነኛነት አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ሕንድ እና ሌሎችም አገራት ፉክክር ያደርጋሉ።

የናሳ ኃላፊ ጃሬድ አይሳክማን እንደተናገሩት ጨረቃ ላይ ማረፍ ከባድ ከሆነባቸው ምክንያቶች አንዱ የፋይናንስ ውስንነት ነው።

ቻይና በአውሮፓውያኑ 2030 መንኮራኩሯን ጨረቃ ላይ እንደምታሳርፍ አስታውቃለች።

መንኮራኩሩ ከመጠቀ በኋላ መግለጫ የሰጡት የናሳ ኃላፊ "ከ54 ዓመት በኋላ ናሳ ወደ ጨረቃ ጠፈርተኞችን ልኳል። ይሄ ተልዕኮ የጠፈርተኞቹ ብቻ ሳይሆን የናንተም ነው" ብለዋል።

በቀጣይ 10 ቀናት ውስጥ ጠፈርተኞቹ በኦራየን የሕዋ መንኮራኩር (Orion spacecraft) ወደ ጨረቃ ዙሪያ ይጓዛሉ።

መሬትን ለአንድ ቀን ከዞሩ በኋላ ወደ ጥልቅ የሕዋ ክፍል ይጓዛሉ። ከምድር ዙሪያ ወደ ጨረቃ የሚያደርጉት ጉዞ (trans lunar injection) ኦራየን የሕዋ መንኮራኩርን ወደ ጨረቃ ክበብ የሚገፋ ነው።

በዚህ ጉዞ ወቅት አንዳች ችግር ቢከሰት ጠፈርተኞቹ መመለስ የሚችሉበት መንገድ ተመቻችቷል።

ወደ ጨረቃ የሚያደርጉት ጉዞ አራት ቀናት ይወስሳል። በእነዚህ አራት ቀናት ውስጥ ጠፈርተኞቹ ለጨረራ ማዕበል (solar radiation storm) ይዘጋጃሉ።

ጉዟቸው ከመሬት 230,000 ማይል ይወስዳቸዋል። ይህም ከጨረቃ ሩቅ ክልል (far side of the Moon) ያደርሳቸዋል።

ከአራት ቀናት በኋላ ኦራየን የሕዋ መንኮራኩር ወደ መሬት ጉዞ ይጀምራል። በላይኛው ከባቢ አየር በፍጥነት ከተጓዘ በኋላ በፓራሹት በመታገዝ መንኮራኩሩ ሰላማዊ ውቅያኖስ ላይ ያርፋል።

በስተመጨረሻም መንኮራኩሩን እና ጠፈርተኞቹን በውቅያኖሱ ላይ የሚቀበሏቸው የአሜሪካ የባሕር ኃይል መርከቦች ይሆናሉ።