የሞሐመድ ሳላህ ቀጣይ መዳረሻ የት ይሆን? ሳዑዲ፣ አሜሪካ ወይስ አውሮፓ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ግብጻዊው ኮከብ በርካታ ስኬቶችን ካስመዘገበበት ሊቨርፑል ጋር በዚህ የውድድር ዓመት መጨረሻ እንደሚለያይ ይፋ አድርጓል። የሞሐመድ ሳላህ ቀጣይ መዳረሻው የት ይሆን? የሚለው እስካሁን አልታወቀም።

ለዘጠኝ ዓመታት ከነገሰበት ሊቨርፑል ጋር በይፋ እንደሚለያይ ከተነገረ በኋላ የሳላህን መዳረሻ በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው። ፍላጎት ያሳዩ አገራትን፣ ለሳላህ ምቹ የሚሆኑ አገራትን እና ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የ33 ዓመቱ ኮከብ ቀጣይ ዓመት የት አገር ልናየው እንችላለን? የሚለውን ቢቢሲ ዳሰሳ አድርጓል።

ሳዑዲ አረቢያ

ሳዑዲ አረቢያ ያለጥርጥር የሞሐመድ ሳላህ ቀዳሚ መዳረሻ ልትሆን ትችላለች።

ሞሐመድ ሳላህ እስከዛሬ ባስመዘገባቸው ስኬቶች ምክንያት በመካከለኛው ምስራቅ እና በአጠቃላይ በአረቡ ዓለም ትልቅ ስም እና ተወዳጅነትን ያገኘ ተጫዋች በመሆኑ ከአገራቱ እግር ኳስ አፍቃሪያን ጋር ከፍተኛ የሆነ ቁርኝት አለው።

ሙስሊም የእግር ኳስ ኮከብ በመሆኑ በሳዑዲ ዓይን ሞሐመድ ሳላህ ቅድሚያ የሚሰጠው ተጫዋች ነው።

በ2023 አል ኢቲሃድ ሞሐመድ ሳላህን ለማዘዋወር 150 ሚሊዮን ፓውንድ ዋጋ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም ሊቨርፑል ግን ጥያቄውን ውድቅ አድርጎበታል።

ይህ ጥያቄ የቀረበው በየርገን ክሎፕ ዘመን ነው። በቀጣዩ ዓመት ከአዲሱ የሊቨርፑል አሰልጣኝ አርን ስሎት ጋር ድንቅ የውድድር ዘመን በማሳለፍ ሳላህ ሊቨርፑል የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ እንዲያነሳ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርጓል።

አሁን ወደ ሳዑዲ የሚያመራ ከሆነ ያሉት ምርጫዎች የትኞቹ ናቸው?

በተለምዶ አራቱ ትልልቅ ክለቦች የሚባሉት እና በአገሪቱ ፐብሊክ ኢንቨስት መንነት ፈንድ የሚተዳደሩት አል አህሊ፣ አል ኢቲሃድ እና አል ናስር ሳላህን ዒላማ ሊያደርጉት ይችላሉ።

ከእነዚህ ክለቦች በተጨማሪ በቀድሞው የሊቨርፑል አሰልጣኝ ብሬንዳን ሮጀርስ የሚሰለጥነው አል ቃድሲያህም ሞሃመድ ሳላህን የማስፈረም ዕድል ይኖረዋል።

የ33 ዓመቱ ሳላህ በውድድር ዓመቱ በነጻ የሚዘዋወር በመሆኑ የሳዑዲ ክለቦች ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየታቸው አይቀርም። እርሱን አስፈርመው ከክርስቲያኖ ሮናልዶ ጋር በማጫወት የሊጋቸውን ተፈላጊነት ማሳደግ ይፈልጋሉ። ነገር ግን የሳዑዲ ሊግ ሳላህን ማስተናገድ ይችላል?

የእግር ኳስ የፋይናንስ ባለሙያ የሆነው ኬራን ማጓየር "ያለምንም ጥርጥር የሳዑዲ ሊግ ሳላህን ማስተናገድ ይችላል" ይላል። "ለክርስቲያኖ ሮናልዶ በዓመት 170 ሚሊዮን ፓውንድ እየከፈሉ ነው። ሳላህ አሁን የሚከፈለው በዓመት 20 ሚሊዮን ፓውንድ አካባቢ ነው። ስለዚህ የክፍያ ጉዳይ አጀንዳ ሊሆን አይችልም"

"ዋናው ነገር ሳላህ ውሳኔውን ትክክል አድርጎ ይወስደዋል ወይ የሚለው ነው። በተለይ መካከለኛው ምስራቅ አሁን ካለበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ምን ሊሰማው ይችላል? የሚለው መታየት አለበት። "ሁኔታዎች እስከ ክረምቱ ሊረግቡ ይችላሉ፤ ነገር ግን ከዚያ በኋላም ተጽዕኗቸው ሙሉ በሙሉ አይጠፋም።

አሜሪካ [ኤምኤልኤስ]

ሞሐመድ ሳላህ የሊዮኔል ሜሲን ፈለግ ተከትሎ ወደ አሜሪካ ሊያመራ ይችላል?

ደመወዙ የሳዑዲ አረቢያ ክለቦች እንደሚያቀርቡት ረብጣ ገንዘብ አማላይ ላይሆን ይችላል።

ነገር ግን ክለቦች ከዋክብትን እንዲያስፈርሙ የሚያስችል በተለምዶ ዴቪድ ቤካም ህግ ተብሎ የሚጠራ ሕግ አላቸው። እንደ ቤካም፣ ሜሲ እና ስዋሬዝ የመሳሰሉትን ተጫዋቾች ያስፈረሙበት ሕግ ነው።

ሜሲ በኢንተር ሚያሚ የሚከፈለው ደመወዝ በዓመት 20 ሚሊዮን ዶላር ነው። ነገር ግን የባለቤትነት ድርሻን ታሳቢ ካደረግን ወደ ካዝናው የሚያስገባው የገንዘብ መጠን በዓመት ከ70 እስከ 80 ሚሊዮን ዶላር ይደርሳል።

ባለፈው ታህሳስ የኤምኤልኤስ ኮሚሽነር ሳላህ ወደ አሜሪካ እንዲመጣ ግብዣ አድርገውለታል። "እጃችንን ዘርግተን እንቀበለዋለን" ብለው ነበር።

"ሊዮኔል ሜሲን፣ ቶማስ ሙለርን የመሳሰሉ ተጫዋቾችን በመጠየቅ ምን ያክል እንደተደሰቱ፣ ሊጉን ግርማ እንደሰጡት እና እንደተሳካላቸው መጠየቅ ይችላል ብዬ አስባለሁ" ብለዋል ኮሚሽነሩ።

በኤምኤልኤስ ትልቅ ደመወዝ የሚከፍለው ኢንተር ሚያሚ ነው። 48.98 ሚሊዮን ዶላር በዓመት ይከፍላል።

ሞሐመድ ሳላህን ማግኘት ከገበያ እና የሊጉን ክብር ከፍ ከማድረግ አኳያ ለኤምኤልኤስ ትልቅ ዕድል ነው የሚሆነው።

የሜሲ ዝውውር እንደ አዲዳስ እና አፕል ካሉ ኩባንያዎች ጋር በተደረገ ስምምነት ጭምር የተደረገ ዝውውር ነው። የሆነ ሆኖ ለሳላህ ከሳዑዲም መጣ ከአሜሪካ አዋጭ ፕሮጀክት ከቀረበለት ሊቀበለው ይችላል ይላል የፋይናንስ ሙያተኛው ማጓየር።

በአውሮፓ መቆየት?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሞሐመድ ሳላህ ካለው አቅም እና ችሎታ አንጻር ደካማ የውድድር ዓመት ነው እያሳለፈ ያለው። እንዲያም ሆኖ ግን በውድድር ዓመቱ በሁሉም ውድድሮች 10 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን 9 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል።

ይህንን ስኬት ባለፈው ዓመት ካየነው ሳላህ ጋር ካነጻጸርነው ግን የወረደ አቋም ላይ እንደሆነ ያሳያል።

ዋናው ነገር ሳላህ አሁንም አቅሙ እንዳለ መገንዘቡ ነው። እንደሻምፒዮንስ ሊግ ያሉ መድረኮች ላይም በአውሮፓ አስተዋጽዖ ማድረግ ይችላል።

ለምሳሌ የባየርን ሙኒኩ ሃሪ ኬን ከሳላህ በአንድ ዓመት ነው የሚያንሰው። ነገር ግን በቡንደስሊጋውም በሻምፒዮንስ ሊጉም ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያደረገ ነው።

እንዲያም ሆኖ ግን ሳላህ ወደ ሌላ ትልቅ የፕሪሚየር ሊግ ክለብ ሊሄድ ይችላል ብሎ ማሰብ በጣም ከባድ ነው። ኒውካስል በሳኡዲ ባለሃብቶች የሚተዳደር ነው፤ ነገር ግን አሁን ካለበት የፋይናንስ ቀውስ እና አለመረጋጋት አንጻር ሳላህን የማዘዋወሩ ዕድል አናሳ ነው።

ማጓየር እንደሚለው የሳላህን ደመወዝ መክፈል የሚችሉት በጣም ጥቂት የአውሮፓ ክለቦች ናቸው። አውሮፓ ውስጥ መቆየት የሚፈልግ ከሆነ ሳላህ ምርጫዎቹ ሊሆኑ የሚችሉት ፓሪስ ሴይንት ጄርሜን፣ ባየርን ሙኒክ፣ ሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና ናቸው። ነገር ግን የሚቀርብለት ፕሮጀክት አማላይ መሆን አለበት።

በኳታር ከበርቴዎች የሚመራው ፓሪስ ሴይንት ጄርሜን ለሳላህ በቂ ደመወዝ መክፈል ይችላል። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ክለቡ ከዋክብትን የማስፈረም ልምዱን ቀንሷል።

ባርሴሎና ውስጥ ሳላህ በሚጫወትበት ቦታ ላይ ታዳጊው ኮከብ ላሚን ያማል አለ። ማድሪድም በዚያ ቦታ በቂ ተጫዋች ያለው ይመስላል።

ስለዚህ አሁን ባለው ሁኔታ ሁሉም ትንተናዎች የሚያሳዩት ለሞሐመድ ሳላህ የቀረበው ከአውሮፓ እና ከኤምአልኤስ ይልቅ ሳዑዲ አረቢያ ነው። እነዚህን ሁኔታዎች መነሻ በማድረግ ሞሐመድ ሳላህ በሚቀጥለው ዓመት በሳዑዲ ሊግ የመታየት ዕድሉ የሰፋ ነው።