በደቡብ ጎንደር ዞን የፋኖ ኃይሎች በፈጸሙት ጥቃት ባለሥልጣናት መገደላቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ
የፎቶው ባለመብት, Wogeda City Comm.
የፋኖ ኃይሎች በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ስር በሚገኙ "የሥራ ኃላፊዎች እና የፀጥታ መዋቅር" ላይ በፈጸሙት ጥቃት ቁጥራቸው ያልተገለጸ ባለሥልጣናት መገደላቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ የደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደር ምንጭ፤ የወረዳ ዋና አስተዳዳሪዎችን ጨምሮ ቢያንስ አምስት የአካባቢው ባለሥልጣናት እንደተገደሉ ገልጸዋል።
ከአንድ ወር በፊት በዋና ከተማው ደብረ ታቦር የሚገኙ የመንግሥት ተቋማትን ያወደመ ጥቃት ያስተናገደው የደቡብ ጎንደር ዞን፤ በመዋቅሮቹ ላይ ጥቃት የተፈጸመው ረቡዕ መጋቢት 09/2018 ዓ.ም. እንደሆነ ገልጿል።
ዞን አስተዳደሩ ትናንት አርብ መጋቢት 11/2018 ዓ.ም. ምሽት ላይ ባወጣው መግለጫ "የጥፋት ኃይሎች" በሚል የገለጻቸው ታጣቂ ቡድኖች "ነፋስ መውጫ እና ሐሙሲት ከተማ ላይ ግጭት" መፍጠራቸውን አስረድቷል።
የታጣቂዎቹ ጥቃት "በሥራ ላይ" በነበሩት የላይ ጋይንት፣ ወገዳ እና ደራ ወረዳዎች እንዲሁም የሁለቱን ከተሞች "የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና የፀጥታ መዋቅር ላይ ያነጣጠረ" እንደነበርም አስታውቋል። ታጣቂዎቹ ጥቃቱን የፈጸሙት "ከተለያየ አካባቢ በመጠራራት እና በመሰባሰብ" እንደሆነ ጠቅሷል።
አንድ የዞን አስተዳደሩ ምንጭ ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ በዕለቱ ጥቃት መፈጸም የጀመረው ከንጋት 12 ሰዓት ገደማ አንስቶ ነው።
ካለፈው ወር አንስቶ የመከላከያ ሠራዊት በዞኑ የሚገኙ አካባቢዎችን ለቅቆ መውጣቱን ያስታወሱት ምንጩ፤ በስፍራው የነበሩት የፀጥታ ኃይሎች የክልሉ አድማ በታኝ፣ ፖሊስ እና ሚሊሻ እንደሆኑ አስረድተዋል።
የመከላከያ ሠራዊት አባላት "ስላልነበሩ [ታጣቂዎቹ] ሌላው የፀጥታ አካላት ላይ ጉዳት አድርሰው ወጥተዋል" ብለዋል።
የፋኖ ኃይሎች "ታች ጋይንት እና ስማዳ" ወረዳዎች ውስጥ እንደሚንቀሳቀሱ የሚናገሩት ምንጩ፤ በአሁኑ ጥቃት ታጣቂዎቹ "ጠንከር ያለ ፀጥታ ኃይል አለ" ወደተባለባቸው ንፋስ መውጫ እና ሐሙሲት ከተማዎች መንቀሳቀሳቸውን ገልጸዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን አስተደዳር ባወጣው መግለጫ "ጀግኖቻችን 'ለባንዳ እና ተላላኪ እጅ አንሰጥም፤ ሕዝባቸውንም ጥለን አንሸሽም' በማለት የአፄ ቴዎድሮስን ፅዋ ተቀብለዋል" ሲል የተገደሉ ባለ ሥልጣናት መኖራቸውን አመልክቷል።
ባለሥልጣናቱ "በሕዝብ ፊት የገቡት ቃልኪዳን እና ታማኝነት ለሕዝብ ታምነው እንደቆሙ ክብራቸውን ጠብቀው አልፈዋል" ሲልም አክሏል። የዞኑ መግለጫ ምን ያህል እና በየትኛው ደረጃ ላይ ያሉ አመራሮች ሕይወት እንዳለፈ አልጠቀሰም።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዞኑ ምንጭ በበኩላቸው በዚህ ሳምንት በተፈጸመው ጥቃት ቢያንስ አምስት አመራሮች መገደላቸውን እንደሚያውቁ ገልጸዋል።
የደራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እስቲበል ጓዴ፣ የደራ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈንታሁን ድረስ እንዲሁም የወረዳው የፖሊስ አዛዥ መገደላቸውን ተናግረዋል። የስማዳ ወረዳ አስተዳዳሪ እና የሐሙሲት ከተማ ከንቲባም ከተገደሉት መከካል ተጠቅሰዋል።
ቢቢሲ እነዚህን ባለሥልጣናት መገደል በገለልተኝነት አላጣራም። ከደቡብ ጎንደር ዞን እና ወረዳ አስተዳደሮች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የተደረጉ ጥረቶች አልተሳኩም።
ወደ ከተሞቹ የገቡት ታጣቂዎች ጥቃቱን ካደረሱ በኋላ መውጣታቸውን የሚናገሩት ምንጩ፤ ቆይቶም የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወደ ላይ ጋይንት ወረዳ አካባቢዎች መሠማራታቸውን ገልጸዋል።
የስማዳ፣ ላይ ጋይንት፣ ታች ጋይንት፣ ደራ እብናት እና መቀጠዋ ወረዳዎች እንዲሁም የሐሙሲት ከተማ አመራሮች በታጣቂዎች እንቅስቃሴ ምክንያት በአሁኑ ሰዓት በዞኑ ዋና ከተማ "ደብረ ታቦር ውስጥ እንደሚገኙም" ተናግረዋል።
ደቡብ ጎንደር ዞን ውስጥ "ወደ ሰባት ከተሞች እና 13 ወረዳዎች አሉ፤ ከእነሱ ውስጥ የመንግሥት የፀጥታ ኃይል ያለው ፎገራ፣ ወረታ፣ ሊቦ ከምከም፣ አዲስ ዘመን ላይ ነው። ጋይንት ወረዳ ንፋስ መውጫም መከላከያ ገብቷል" ብለዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደር በትናንቱ መግለጫው፤ ታጣቂዎቹ "ንፁሀንን በማገት እና በመግደል እንዲሁም ሕዝቡ መሪ እንዳይኖረውና ሥርዓት አልበኝነት እንዲነግስ አስበው እየሰሩ" ነው ሲል ከስሷል።
የአካባቢዎቹን "ሰላም ወደነበረበት ለመመለስ እና አካባቢውን ከፀረ-ሰላም ቡድኖች ለማውጣት ጠንካራ ሕግ የማስከበር ሥራ እንደሚሠራም" አስታውቋል።
የሰሞኑን ክስተት በተመለከተ ቢቢሲ ትክክለኝነታቸውን ማረጋገጥ ያልቻላቸው ተንቀሳቃሽ ምሥሎች እና ፎቶግራፎች ሲወጡ ነበር።
አማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ ነፋስ መውጫ፣ ክምር ድንጋይ፣ ጋሳኝ እና ሐሙሲት ከተሞች ውስጥ በፈጸመው ጥቃት በርካታ ከባድ እና ቀላል መሣሪያዎችን እንዲሁም ተሽከርካሪዎችን መማረኩን እንዲሁም በርካታ የአካባቢዎቹን የፀጥታ አካላትን መግደሉን እና መማረኩንም አስታውቋል።
ነገር ግን የአካባቢው አስተዳደር አመራሮች ከመገደላቸው ውጪ ታጣቂ ቡድኑ ያለውን ጉዳት በተመለከተ ከመንግሥት በኩል የተሰጠ ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ የለም።
በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱት የፋኖ ኃይሎች ባለፈው የካቲት ላይም በዞኑ ዋና ከተማ ደብረ ታቦር ውስጥ በፈጸሙት ጥቃት "ከሐምሌ 2015 ዓ. ም. ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ የመንግሥት ተቋማት ውድመት" አድርሰዋል።
በዚህ ጥቃት ከቀበሌ አስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች እስከ ዞን መምሪያዎች ድረስ ያሉ 20 የሚደርሱ ተቋማት እና ተሽከርካሪዎች መውደማቸውን ቢቢሲ ያሰባሰባቸው መረጃዎች አሳይተዋል።
እንዳያመልጥዎ
ከየፈርጁ
በስፋት የተነበቡ
የሚፈልጉት ይዘት የለም