አሜሪካ በኢራኗ ኻርግ ደሴት ላይ የፈጸመችው ጥቃት በጦርነቱ ሂደት ላይ ምን ውጤት ይኖረዋል?
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ኃይሎች ቅዳሜ ዕለት በኢራን ኻርግ ደሴት ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን አስታውቀዋል።
የአሜሪካ መከላከያ ጥቃት ያደረሰበት አነስተኛው ኻርግ ደሴት የኢራን ምጣኔ ሃብት ዋልታ እና ማገር እንደሆነ ይነገርለታል።
በኻርግ ደሴት ላይ የሚገኘው የነዳጅ ማከማቻ በኢራን ምጣኔ ሃብት ጉልህ ሥፍራ ያለው ነው።
ትራምፕ በደሴቱ ላይ ያሉ የነዳጅ ተቋማ ባይመቱም ደሴቱ ያለው የኢራን ወታደራዊ አቅም "ሙሉ በሙሉ ወድሟል" ብለዋል።
ነገር ግን በደሴቱ የሚገኙ የነዳጅ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ሊወስኑ እንደሚችሉ ትራምፕ አስጠንቅቀዋል።
ኢራን ወይም ሌሎች በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚተላለፉ መርከቦችን የሚያስተጓጉሉ ከሆነ በዚህ ደሴት የሚገኙ የነዳጅ መሠረተ ልማቶች ላይ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።
በኻርግ ደሴት የነዳጅ መሠረተ ልማት ላይ አሜሪካ ጥቃት ካደረሰች ኢራን በምላሹ በቀጣናው የሚገኙ ከአሜሪካ ኩባንያዎችን ጋር ግንኙነት ያላቸውን ተቋማ ት"እንደምታወድም" አስጠንቅቃለች።
ኻርግ ደሴት ለኢራን ያለው ጠቀሜታ
ኻርግ ደሴት ከኢራን ባሕር ዳርቻ 24 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። መጠኑ አነስተኛ ቢሆንም በኢራን የነዳጅ እና የጋዝ አቅርቦት ቁልፍ ቦታ የሚሰጠው ነው።
ለኢራን ቁልፍ የሆነው እዚህ ደሴት ላይ የደረሰው ጥቃት የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት ክፉኛ ያናጋል።
በዚህ ደሴት በኩል በየቀኑ 1.3 ሚሊዮን በርሜል የተጣራ ድፍድፍ ነዳጅ ይተላለፋል። ነዳጅ የሚተላለፈው ከውሃ በታች በሚገኝ ትቦ ሲሆን፣ ወደ ሦስት ዋነኛ የኢራን የባሕር ዳርቻ መዳረሻዎች ይዘዋወራል።
እነዚህ መዳረሻዎች አቦዛር፣ ፎሮውዛን እና ዶሮድ ናቸው። 18 ሚሊዮን በርሜል ማከማቸት የሚችል ቦታም አለው። ይህን ያህል ነዳጅ ከ10 እስከ 12 በሚደርሱ ቀናት ወደ ውጭ አገራት ይተላለፋል።
85 ሚሊዮን ጋሎን ነዳጅ መያዝ የሚችሉ ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ወደ ደሴቱ ዳርቻ በመጓዝ ይጭናሉ። የደሴቱ ዳርቻ ወደ ጥልቅ የውሃ አካል ቅርብ በመሆኑ ለመርከቦች እንቅስቃሴ አመቺ ነው።
ታንከሮቹ ነዳጁን ይዘው ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ ከዚያም ወደ ቻይና ይጓዛሉ። ቻይና የኢራንን ነዳጅ በዋነኛነት የምትሸምት አገር ናት።
የኢራን ነዳጅ ዋነኛ መተላለፊያ የሆነው ደሴት የእስላማዊ አብዮታዊ ዘቡ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ነው።
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ ለምን የነዳጅ መሠረተ ልማት ላይ ጥቃት አልፈጸመችም?
ትራምፕ ባለፈው አርብ ባደረጉት ንግግር የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ "በመካከለኛው ምሥራቅ ኃይለኛውን ድብደባ ፈጽሞ በኢራን ወሳኝ ኻርግ ደሴት ላይ የሚገኙ ወታደራዊ ዒላማዎችን ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ አድርጓል" ብለዋል።
ትራምፕ አክለውም "ጨዋ ለመሆን ሲባል የደሴቱ የነዳጅ መሠረተ ልማት ላይ ጥቃት ላለማድረስ መርጠናል" ሲሉ ተናግረዋል።
የኢራን መገናኛ ብዙኃንም የደሴቱ የነዳጅ መሠረተ ልማት ላይ ጉዳት አለመድረሱን ዘግበዋል።
የአሜሪካ ጥቃት ዒላማ ያደረገው የአየር እና ባሕር ኃይል መቀመጫዎችን መሆኑ ተገልጿል። በተጨማሪም የአውሮፕላን መቆጣጠሪያ እና የሄሊኮፕተር ማረፊያ ዒላማ ተደርገዋል።
ኢራን በደሴቱ የሚገኙ "የኃይል አቅርቦት መሠረተ ልማቶች" ላይ ጉዳት የሚደርስ ከሆነ ንብረትነታቸው የአሜሪካ ኩባንያዎች የሆኑ የነዳጅ እና ኃይል ኩባንያች ላይ ጥቃት እንደምትፈጽም አስጠንቅቃለች።
የደሴቱ መሠረተ ልማት ላይ ጥቃት ቢደርስ ኢራንን በእጅጉ የሚጎዳ ይሆናል። ግጭቱንም የበለጠ ያባብሳል።
በተጨማሪም የነዳጅ ዋጋ አሁን ካለውም በላይ እንዲጨምር ያደርጋል። ኢራን በአጸፋ እርምጃ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የነዳጅ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ልትፈጽም ትችላለች።
ሦስተኛ ሳምንቱን በያዘው የኢራን ጦርነት ቴህራን በባሕረ ሰላጤው አገራት እና በቀጣናው በሚዘዋወሩ መርከቦች ላይ ጥቃት ማድረሷን ቀጥላለች።
በኢራን ደሴት ላይ ጥቃት ቢፈጸም የአጸፋ እርምጃው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚገለገሉባቸው የውሃ አቅርቦቶችን ሊያካትትም ይችላል።
የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ጦር ኃላፊ እና ወታደራዊ ተንታኝ ጀስተን ክራምፕ እንደሚሉት፤ አሜሪካ በደሴቱ ላይ የወሰደችው ጥቃት ዓላማው ኢራን ግጭቱን እንዳታስፋፋ ማገድ ነው።
"ትራምፕ ለአሁኑ ይቅር ባይ እንደሆኑ ለማሳየት ቢሞክሩም በእስላማዊ አብዮታዊ ዘቡ ላይ የከፋ እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ" ይላሉ ተንታኙ።
የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብን ሊጎዳ የሚችለው የነዳጅ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ይሆናል።
ትራምፕ የጦርነቱ አላማ ኢራናውያን መንግሥት እንዲቀይሩ ማስቻል መሆኑን ከዚህ ቀደም ተናግረዋል። አሁን ግን ጦርነቱ ሌሎችም ግቦች እንዳሉት እየገለጹ ነው።
ወታደራዊ ተንታኙ ጀስተን እንደሚናገሩት፤ የኢራን ኻርግ ደሴት ላይ የሚደርስ ጥቃት የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት ለረዥም ጊዜ የሚያዳክም ነው።
ከዚህ ቀደም በኢራን-ኢራቅ ጦርነት ወቅት የቴህራን የነዳጅ መሠረተ ልማት እንደተጎዳ እና መልሶ ለማገገም ጊዜ እንደወሰደ በመጥቀስ፤ ዳግመኛ ጥቃት የሚደረስ ከሆነ "ለኢራናውን የወደፊት ዕጣ ፈንታ አይበጅም" ሲሉ ያስረዳሉ።
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ ደሴቱን መቆጣጠር ትችላለች?
የአሜሪካ መከላከያ የኢራን ኻርግ ደሴትን ሊቆጣጠር ይችላል የሚል ስጋት ከዚህ በፊትም ነበር።
አሜሪካ ይሄንን ደሴት ብትቆጣጠር በኢራን የነዳጅ ሽያጭ ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል። አሜሪካ ከዚህ ደሴት ወደ ቴህራን ጥቃት መፈጸምም ትችላለች።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃኝ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት፤ ወደ አምስት ሺህ የሚሆኑ የባሕር ኃይል ወታደሮችን የያዙ የጦር መርከቦች ወደ ባሕረ ሰላጤው እየተጓዙ ነው።
ይህም አሜሪካ ደሴቱን ልትቆጣጠር ትችላለች የሚለውን ስጋት አጠናክሯል።
ደሴቱ በአሜሪካ እጅ ቢወድቅ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የገቢ ምንጩን ያጣል። ይህም ጦርነቱን የመቀጠል አቅሙን እንደሚያዳክመው የቢቢሲ የደኅንነት ተንታኝ ሚኪ ኬይ ይናገራል።
ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ከነበረው የፐርሺያ ሥርወ መንግሥት አንስቶ ኻርግ ደሴት በባሕረ ሰላጤው ቁልፍ ስትራቴጂያዊ ቦታ ያለው ሥፍራ ነው።
በ16ኛው እና 17ኛው ክፍለ ዘመን በፖርቹጋሎች እና ደቾች ቁጥጥር ሥር ነበር።
በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ መባቻ ላይ ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግባቸው እስረኞች ማቆያም ነበር።
በ1950ዎቹ ሻህ መሐመድ ሬዛ ፓህላቪ ሥልጣን ላይ ሳሉ የሃይድሮካንቦን ማከማቻ እና ማከፋፈያ ግንባታ ተጀመረ። ከዚያም ደሴቱ የኢራን ዋነኛ የውጭ ንግድ ማዕከል ሆነ።
ስፋቱ 24 ስኩዌር ሜትር የሚሸፍነው ይህ ደሴት ከ1960ዎቹ ወዲህ በኢራን የነዳጅ ንግድ ዋነኛ ማዕከል ሆኖ ቀጥሏል።
የአሜሪካው ነዳጅ አምራች አሞኮም በግንባታው ተሳታፊ ነበር። በ1979 የኢራን አብዮት እስከሚነሳ ድረስ አብዛኛው የደሴቱ መሠረተ ልማት በአሜሪካ ተቋማት ይዞታ ሥር ቆይቷል።
እንዳያመልጥዎ
ከየፈርጁ
በስፋት የተነበቡ
የሚፈልጉት ይዘት የለም