ትራምፕ የአገሪቱን የመከላከያ በጀት ወደ 1.5 ትሪሊዮን ዶላር ሊያሳድጉ ነው
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዋይት ሐውስ ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት ወዲህ ግዙፍ ወታደራዊ ወጪ ነው የተባለውን የመከላከያ በጀት ወደ 1.5 ትሪሊዮን ዶላር ለማሳደግ ሊጠይቅ ነው።
ይህ ገንዘብ የትራምፕ አስተዳደር ላቀረበው የጎልደን ዶም ሚሳኤል መከላከያ ሥርዓት የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍን እንዲሁም 'ትራምፕ ክላስ' የተባለ ተዋጊ የጦር መርከቦችን ጨምሮ አዳዲስ የባሕር ኃይል መርከቦችን በአገር ውስጥ ለማምረት ይውላል ተብሏል።
አስተዳደሩ የታቀደውን የበጀት ጭማሪ በአገር ውስጥ ኤጀንሲዎች ላይ የሚደረጉ ቅነሳዎችን ጨምሮ የአየር ንብረት፣ የመኖሪያ ቤት እና የትምህርት ፕሮግራሞችን በማጠፍ እንደሚካካስ ገልጿል።
የቀረበው ጥያቄ በአሜሪካ ኮንግረስ መጽደቅ የሚያስፈልገው ሲሆን ፔንታጎን በኢራን ለሚካሄደው ጦርነት ከጠየቀው 200 ቢሊዮን ዶላር የተለየ ነው።
በኦንላይን ላይ የተጋራው የበጀት ማጠቃለያ እንደሚያሳየው ቅነሳው የሚሳካው "አላስፈላጊ እና ብክነትን የሚያስከትሉ ፕሮግራሞችን በመቀነስ ወይም በማስወገድ እና ኃላፊነቶችን ለሚመለከተው የአካባቢ አስተዳደር በመስጠት" ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመከላከያ በጀትን ለማሳደግ እና በአገር ውስጥ የሚሰሩ የመከላከያ መሣሪያዎችን ለመጨመር ፍላጎት እንዳላቸው ለረጅም ጊዜ ሲገልጹ ቆይተዋል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በዋይት ሐውስ በተካሄደ ዝግጅት ላይ ትራምፕ ለወደፊት ወታደራዊ ወጪ አገራዊ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ መሆን እንዳለበት ሲናገሩ ተደምጠዋል።
"ዴይኬር፣ ሜዲኬይድ፣ ሜዲኬር የመሳሰሉ የግል ጉዳዮችን መንከባከብ አንችልም፤ በግዛቶቻቸው ደረጃ ሊያደርጉት ይችላሉ" ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ተናግረው፣ "በወታደራዊ ጥበቃ" ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት አክለዋል።
በታቀደው በጀት ውስጥ ከመከላከያ ጋር ያልተያያዘ ወጪ በ10 በመቶ ወይም ወደ 73 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ብሏል።
በትራምፕ የቀረበው በጀት ካለፈው የበጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ42 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ይህም በአጠቃላይ 445 ቢሊዮን ዶላር ነው።
ከጠቅላላው ውስጥ ወደ 1.1 ትሪሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወጪ ለፔንታጎን የሚውል ሲሆን ይህም በታሪክ ከፍተኛው ነው።
ለኢንዱስትሪ መከላከያ ጦር ሰፈር ተጨማሪ 350 ቢሊዮን ዶላር የሚገኘው በጀት ማስታረቅ በመባል ከሚታወቀው ሂደት ይሆናል።
ይህም አንዳንድ ሕጎች በ51 አብላጫ ድምጽ ሴኔቱን እንዲያፀድቅ የሚያስችል የአሰራር አቋራጭ መንገድ ነው።
በጀቱ ለወታደሮች የደመወዝ ጭማሪ እና 65.8 ቢሊዮን ዶላር የመርከብ ግንባታ ገንዘብ እንዲጨመር ይጠይቃል። ይህም ትራምፕ የቀጣይ ትውልድ "ወርቃማ የጦር መርከቦች" ብለው የጠሯቸውን የሚጨምር ነው።
እነዚህም በታሕሳስ ወር ይፋ የተደረጉትን ከባድ የጦር መሣሪያ የሚታጠቁ የትራምፕ ክላስ የጦር መርከቦችን ያካትታሉ።
ትራምፕ የጦር መርከቧን ይፋ ባደረጉበት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የመጀመሪያው መርከብ የሆነው ዩኤስኤስ ዲፊያንት ግንባታ በቅርቡ እንደሚጀመር እና የመጀመሪያዎቹ መርከቦች በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ሥራ ላይ እንደሚውሉ ተናግረዋል።
የአስተዳደር ባለሥልጣናት አሜሪካ በአሁኑ ጊዜ በመርከብ ግንባታ አቅምም ሆነ በአጠቃላይ ምርት ረገድ ከቻይና ወደ ኋላ ቀርታለች ሲሉ በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል።
በተጨማሪም በጀቱ 185 ቢሊዮን ዶላር ለጎልደን ዶም ግንባታ የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍን ያካትታል። ነገር ግን ባለሥልጣናቱ ይህንን የመከላከያ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስፈልገው ገንዘብ በትክክል አይታወቅም።
ሥርዓቱ የቀጣዩ ትውልድ ሚሳኤሎችና ድሮኖች ለመጠበቅ በመሬት፣ በባሕር እና በጠፈር ላይ ለመጠበቅ፣ ለመለየት እና አስቀድሞ ለማስቆም የሚያስችሉ ሴንሰሮች ይኖሩታል ተብሏል።
ጎልደን ዶም፣ ከአይረን ዶም በብዙ እጥፍ ይለያል የተባለ ሲሆን፣ ከድምጽ ፍጥነት በላይ የሚምዘገዘጉ ሃይፐርሶኒክ ጦር መሳሪያዎችን እና ፎብስ (FOBS ) በመባል የሚታወቀውን እና ወደ ዒላማው ለመወንጨፍ ዝቅተኛ የምድር ምህዋርን የሚጠቀመውን የጦር መሣርያ ሥርዓት ጨምሮ የተለያዩ ስጋቶችን ለመመከት የተነደፈ መሆኑ ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ የሚሳዔል አረርን ከጠፈር ሊልክ የሚችል አቅም እንደሚኖረው ተገልጿል።
እንዳያመልጥዎ
ከየፈርጁ
በስፋት የተነበቡ
የሚፈልጉት ይዘት የለም