ቢል ኮዝቢ ከ50 ዓመት በፊት ፈጽሞታል በተባለው ወሲባዊ ጥቃት 19 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈል ተፈረደበት

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ታዋቂው ተዋናይ ቢል ኮዝቢ በቀድሞዋ የምግብ ቤት አስተናጋጅ ላይ በአውሮፓውያኑ 1972 ፈጽሟል በተባለው ጥቃት ምክንያት ከ19 ሚሊዮን ዶላር በላይ ካሳ እንዲከፍል ተወሰነበት።

ካሊፎርኒያ ውስጥ የተሰየሙት ዳኞች አስተናጋጇ ያለፈቃዷ ወሲባዊ ጥቃት እንደተፈጸመባት ማረጋገጡን ተከትሎ ነው ውሳኔውን ያስተላለፈው።

ዶና ሞሲንገር የተባለችው ተበዳይ ከአምስት አስርት ዓመታት በፊት የቀድሞው ኮከብ ተዋናይ ወይን በማጠጣት እና መድኃኒት በመስጠት ራሷን እንድትስታ ካደረገ በኋላ ከቤቷ እንደወሰዳት ተናግራለች።

የ88 ዓመቱ ኮዝቢ፣ ዶና እና ሌሎች ሴቶች ያቀረቡትን ተመሳሳይ ፆታዊ ጥቃት አለመፈጸሙን አስተባብሏል።

ኮዝቢ በፆታዊ ጥቃት ተከሶ ሦስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ከታሰረ በኋላ ከእስር የተፈታው በ2021 ነበር።

የኮዝቢ ጠበቃ ጄኒፈር ቦንጂን ደንበኛዋ የተበየነበትን ውሳኔ ይግባኝ እንደሚጠይቅ ለአሜሪካ መገናኛ ቡዙኃን ተናግራለች።

ሳንታ ሞኒካ ውስጥ የተሰየመው ዳኝነት ለተበዳይዋ የሞራል ካሳ ተጨማሪ ቅጣትም ሊወስን ይችላል። ትክክለኛ መጠኑ ግን እስካሁን አልታወቀም።

አሁን 84 ዓመት የሆናት ዶና ሞሲንገር ጥቃቱ ሲፈጸምባት ፍራንሲስኮ አቅራቢያ 'ትሪደንት ኢን ሳውሳሊቶ' የተባለ ሬስቶራንት ውስጥ አስተናጋጅ የነበረች ሲሆን፣ ሬስቶራንቱም ኮዝቢን ጨምሮ የዝነኞች መሰባሰቢያ ነበር።

ሞሲንገር በክሷ ላይ እንዳስቀመጠችው በወቅቶ ኮዝቢ ስታንዳፕ ኮሜዲውን እንድትታደም ከጋበዛት በኋላ ክኒን እንደሰጣት እና አስፕሪን መስሏት እንደወሰደችው ገልጻለች።

"ከዚያ በኋላ ራሷን ሳተች" ይላል የክስ መዝገቡ። "ሞሲንገር የምታስታውሰው የመጨረሻው ነገር የብርሃን ብልጭታ ነው።"

ክሱ እንደሚያስረዳው ሞሲንገር ቤቷ ውስጥ ስትነቃ ከውስጥ ሱሪዋ ውጭ እርቃኗን ሆና ነበር ራሷን ያገኘችው "በዚህም በቢል ኮዝቢ እንደተደፈረች ተረዳች" ይላል።

ጉዳዩን በተመለከተ የኮዝቢ ቃል አቀባይ እና ጠበቃ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም። ኮሜዲያኑ በ1980ዎቹ እና 90ዎቹ 'ዘ ኮዝቢ ሾው' በተሰኘው ሲትኮም ዝነኛ ነበር።

ነገር ግን ከ1960 ጀምሮ በርካታ ሴቶች ኮዝቢ ፈጽሞብናል የሚሏቸው ወሲባዊ ጥቃቶች፣ የመድፈር ወንጀሎች እና ተያያዥ ክሶች ምክንያት ዝናው እየተሸረሸረ መጥቷል። ሁሉም ድርጊቶች የተፈጸሙት በፈቃደኝነት መሆኑን ኮዝቢ ለማስረዳት ሞክሯል።